የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር 43 ሰዎች የሞቱበት የባቡር አደጋ የደረሰው ‘በሰው ስህተት ነው’ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በግሪክ ታሪክ እጅግ አሰቃቂው በተባለው የባቡር አደጋ ምክንያት 43 ሰዎች ሲሞቱ የሃገሪቱ መሪ አደጋው የደረሰው ‘በሰው ስህተት ነው’ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኪርያኮስ ሚትሶታኪስ፤ አደጋው የደረሰበትን ስፍራ ከጎበኙ በኋላ ነው ይህንን ያሉት።
አደጋው የደረሰው ማክሰኞ ምሽት ሲሆን አንድ የመንገደኞች ባቡርና ሌላ የጭነት ባቡር ፊት ለፊት ተጋጭተው ብዙዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የአካባቢው ባቡር ጣቢያ ተቆጣጣሪ በነፍስ ማጥፋት ተሰከዋል፤ አልፎም የግሪክ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሥራቸውን ለቀዋል።
ማክሰኞ እኩለ-ለሊት ገደማ 350 ሰዎችን የያዘ የመንገደኞች ባቡር ከድልድይ ሥር ከሚወጣ የጭነት ባቡር ጋር ፊት ለፊት ተጋጭተዋል።
ሁለቱም ባቡሮች ለምን አንድ መስመር ይዘው ይጓዙ እንደነበር እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የሥፍራው ባቡር ጣቢያ ተቆጣጣሪ ጥፋት እንዳልፈፀሙ ተናግረው አደጋው የደረሰው በቴክኒክ ጉድለት ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለዋል።
የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር የአደጋውን ሥፍራ ከጎበኙ በኋላ “በሰው ስህተት ምክንያት የደረሰ” አደጋ እንደሆነ ሁኔታዎች ያመላክታሉ ብለዋል።
“ፍትሕ ሥራውን ይሠራል” ሲሉ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ስህተት የፈፀሙ ሰዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጠዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ኮስታስ ካራማንሊስ የሥራ መልቀቂያቸውን ይፋ ባደረጉበት “እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ አደጋ ሲደርስ ምንም እንዳልሆነ አስመስሎ ማለፍ ከባድ ነው” ብለዋል።
የንግድ ማሕበራት ጉዳቱ የደረሰው በሰው ኃይል ማነስ፤ በተሰባበሩ ምልክቶችና ጊዜያቸው ባለፈ መሣሪያዎች ምክንያት ነው ይላሉ።
የመንገደኞቹ ባቡር የመጀመሪያዎቹ አራት ፍርጎዎች ከመስመር ሲወጡ ሁለቱ እሣት ይዘዋል።
ባቡሩ ከአቴንስ ወደ ቴሳሎኒኪ እየተጓዘ የነበረው የመንገደኞች ባቡር በርካታ ተማሪዎችን ጭኖ እንደነበር ተነግሯል።
“ሰዎች በድንጋጤ ሲጮሁ ነበር” ሲል አንድ ከአደጋው የተረፈ ሰው አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከአደጋው ከተረፉት መካከል ሌላኛው ያኒስ አንቶኖግሉ አምስተኛው ፉርጎ ውስጥ ሳለ የባቡሩ መስታወት ሲረግፍ መመልከቱን ይናገራል።
የ28 ዓመቱ ስተርጊዮስ ሚኔኒስ በበኩሉ ባቡሩ አደጋ ሲደርስበት እሣት መያዙን ሲመለከት በመስኮት ዘሎ ሕይወቱን ማትረፉን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጧል።
አደጋው የደረሰባት የላሪሳ ከተማ ከንቲባ በአደጋው ምክንያት በአደጋው የሞቱ አንዳንድ ሰዎች በዘረ-መል ቴክኖሎጂ ካልሆነ ማንነታቸውን መለየት ከባድ ነው ብለዋል።
ባቡሩ ውስጥ የነበሩ ዘመድ አዝማዶቻቸውን ያጡ ሰዎች ለምርመራ እንዲሆን የዘር-ቅንጣታቸውን ለከተማዋ ሆስፒታል ሰጥተዋል።












