ሩሲያ ድንበሯን አልፎ ከገባ ታጣቂ ቡድን ጋር እየተዋጋሁ ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Telegram
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በሚያዋስናት ድንበር በኩል ወደ ግዛቷ የገባ ታጣቂ ቡድን እየተዋጋች መሆኑን አስታወቀች።
ቤልጎሮድ በተባለው የድንበር ግዛት በኩልም በተከሰተው ግጭት በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የሩሲያ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የአካባቢው አስተዳዳሪ ቭያቼስላቭ ግላድኮቭ በድንበር ግዛቷ በኩል ገብተው ጥቃት ያደረሱትንም ታጣቂዎች በመፈለግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የቭላድሚር ፑቲን ቃለ አቀባይ በበኩላቸው ስለ ሁኔታው ለፕሬዚዳንት ፑቲን እንደተናገራቸው አስረድተዋል።
ዩክሬን ከዚህ ጥቃት ጀርባ እጄ የለበትም ያለች ሲሆን ድንበር ተሻግረው የወረሩትም የሩስያ ዜግነት ካላቸው ሁለት ወታደራዊ ቡድኖች የተውጣጡ ታጣቂዎች ናቸው ብላለች።
የአካባቢው አስተዳዳሪ ግላድኮቭ እንደተናገሩት በመንደሯ ላይ በደረሰው ጥቃት ስምንት ሰዎች ሲጎዱ ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ በከባድ መሳሪያ እንዲሁም ሶስት ሰዎች በፍንጣሪዎች በደረሰባቸው ጉዳት ሆስፒታል ገብተዋል።
በግጭቱ ሶስት መኖሪያ ቤቶች እና የአካባቢው የአስተዳደር ህንጻ ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ግላድኮቭ ሁኔታው “እጅግ ውጥረት የበዛበት” ነው ብለዋል።
አስተዳዳሪው በግዛቲቷ "የፀረ-ሽብር ዘመቻ" መጀመሩን ገልጸው የአካባቢው ባለስልጣናት የማንነት ቁጥጥር እና የግንኙነት ክትትል እንዲያደርጉም ልዩ ስልጣን መሰጠቱንም ጨምረው ተናግረዋል።
ቢቢሲ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ የቤልጎሮድ ግዛት ቪዲዮዎችን ሲመረምር ቆይቷል።
ከቤልጎሮድ በስተደቡብ በሚገኝ የድንበር ኬላ አቅራቢያ በርካታ የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን የሚያሳይ ከድሮን የተቀረጸ የሚመስል ቪዲዮ አግኝቷል። በተጨማሪም በግዛቲቷ ውስጥ እየተንሳቀሱ ያሉ ሄሊኮፕተሮችንም ጥቆማ አግኝቷል።
ቪዲዮው የቅርብ ጊዜ ቢሆንም የክስተቶቹን ትክክለኛ ቅደም ተከተል በእርግጠኝነት ለማወቅ ፈታኝ ነው።
ዩክሬን ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያሉት የሩሲያ ሌጌዎን ነጻነት እና የሩስያ በጎ ፈቃደኞች ኮርፕስ የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖች ናቸው ብላለች።
የሩስያ ሌጌዎን ነጻነት መቀመጫውን በዩክሬን አድርጎ የሩስያን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ከስልጣን ለመገርሰስ እየሰራ እንደሆነ የሚገልጽ ሲሆን ኮዚንካ የምትባለውን የድንበር ከተማ ሙሉ በሙሉ ነጻ አውጥቻለሁም ሲል ሰኞ እለት በትዊተር ገጹ አስፍሯል።












