ቢቢሲ ስለሕንዱ መሪ ሞዲ በሠራው ዘጋቢ ፊልም ምክንያት ደልሂ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ታዘዘ

ፖሊሶች ከቢቢሲ ግቢ ውጭ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቢቢሲ ስለሕንዱ መሪ ናሬንድራ ሞዲ በሠራው ዘጋቢ ፊልም ምክንያት በስም ማጥፋት ደልሂ የሚገኝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ታዟል።

ዘጋቢ ፊልሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈረንጆቹ 2002 በጉጅራት ፀረ-ሙስሊም ጥቃት ላይ የነበራቸውን ሚና የሚዳስስ ሲሆን በወቅቱ ሞዲ የግዛቱ ገዥ ነበሩ።

መቀመጫውን ጉጅራት ያደረገው ክሱን ያቀረበው ጀስቲስ ኦን ትራያል የተሰኘው ቡድን ዘጋቢ ፊልሙ የሕንድን ስም አጥፍቷል ሲል ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግሯል።

ቢቢሲ ስለቀረበበት ክስ መስማቱን ቢገልጥም “በዚህ ወቅት አስተያየት መስጠት ተገቢ አይሆንም” ብሏል።

‘ኢንዲያ፡ ዘ ሞዲ ኩዌስችን’ የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ባለፈው ጥር ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ብቻ ነው የተላለፈው።

ነገር ግን የሕንድ መንግሥት ፊልሙ “ፀብ ጫሪ ፕሮፖጋንዳ እና ፀረ-ሕንድ ግብስባሶ” ነው፤ አልፎም “በቅኝ ገዥ አስተሳሰብ የተቃኘ” ነው በማለት ሰዎች እንዳይጋሩት ሲሞክር ነበር።

ፕሮግራሙ ከተላለፈ ከሳምንታት በኋላ ደልሂ የሚገኘው የቢቢሲ ቢሮ በሕንድ ገቢ ታክስ መኮንኖች ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎበታል።

ባለፈው መጋቢት ደግሞ ቢቢሲ የውጭ ምንዛሪ ሕግ ጥሷል የሚል ምርመራ ተከፍቶበታል።

ዘጋቢ ፊልሙ በጉጅራት ግዛት አመፅ በተነሳ ወቅት የሞዲ አመራር ምን ያደርግ እንደነበር ይቃኛል።

የጉጅራት አመፅ የተነሳው የሂንዱ እምነት ተከታዮች ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አንድ ባቡር እሣት ይዞ በርካቶች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ነው።

ይህን ተከትሎ በተነሳው አመፅ ከ1000 በላይ አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች የሆኑ ግለሰቦች ተገድለዋል።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በአመፁ ምክንያት የሚደርስባቸውን ትችት ሲያጣጥሉ ቆይተዋል፤ ይቅርታም ጠይቀው አያውቁም።

በፈረንጆቹ 2013 ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችል ማስረጃ የለም ብሎ ነበር።

ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ዘጋቢ ፊልሙ “ከብዙ ጥናት” በኋላ የተሠራና “የዓይን እማኞችና ባለሙያዎችን ጨምሮ በርካቶች የተሳተፉበት፤ የተለያዩ ሐሳቦች የተንሸራሸሩበት አልፎም የቢፒጄ ፓርቲ አባላት የተካተቱበት” ነው ማለቱ ይታወሳል።