የአንድ ቢሊዮን ዶላር ካሳ የተጠየቀበት የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ጉዳይ ከምን ደረሰ?

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ የአገሪቱን ክፍሎች በባቡር መስመሮች ለማገናኘት በያዘው ዕቅድ የተጀመረው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ሥራውን የጀመረው ከአስር ዓመታት በፊት ነበር።
ይህ የባቡር መስመር አጠቃላይ ርዝመቱ 392 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ግንባታው በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ ነበር ሲከናወን የነበረው።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ የሚደርስ እና 270 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን፣ ከኮምቦልቻ ሃራ ገበያ ያለው ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 122 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።
የዚህ የባቡር መስመር ግንባታ በሁለት ምዕራፍ እንዲከፈል የተደረገው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን ሙሉ ገንዘብ ባለመገኘቱ ነበረ።
ያፒ መርከዚ በተባለው የቱርክ ተቋራጭ ግንባታው ሲከናወን የነበረው የባቡር መንገዱ ለመጀመሪያው ዙር ግንባታው ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት ተይዞለት ነበር የተከናወነው።
ከአራት ዓመት በፊት የተጠናቀቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ የባቡር መስመሩ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት ለመስጠት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በመጠባበቅ ላይ እንደነበር የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው እንደነበረ ይታወሳል።
ሁለተኛው ምዕራፍ የባቡሩ መስመር ግንባታን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ገንዘብ ዘግየት ብሎ ተገኝቶ የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ በወሰን ማስከበር እና በሌሎች ምክንያቶች ተስተጓጉሏል።
ከዚያም በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ተስፋፍቶ ወደ አማራ ክልል ከተዛመተ በኋላ ሥራው ከመቋረጡ በተጨማሪ ለአገልግሎት ዝግጁ የነበረው እና በግንባታ ላይ የነበረው የባቡሩ መሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት እና ዝርፊያ አጋጥሞታል።
በ2007 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው የባቡር መስመሩ የቱርኩ ያፒ መርከዚ የተባለ ተቋራጭ እየገነባው የነበረ ቢሆንም በሁለት ዓመቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የደረሰበት ዝርፊያ እና ጉዳት ተከትሎ ሥራው ተስተጓጉሏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የግንባታው ተቋራጭ ድርጅቱ ጥር 2015 ዓ.ም. ለንደን በሚገኘው ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ባቀረበው የይገባኛል ክስ "ከፍተኛ ገንዘብ" ካሳ መጠየቁን የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።
ተቋራጭ ድርጅቱ በዋናነት በጦርነቱ ወቅት ለደረሰበት ጉዳት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ላይ ክስ መሥርቶ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ወይንም በአሁኑ የምንዛሪ ተመን የ131 ቢሊዮን ብር ገደማ የካሳ ይገባኛል ጥያቄ አቅርቧል።
ኩባንያው በዋናነት ከውል ጋር በተያያዘ ያልተከፈሉ ክፍያዎች፣ ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ የካሳ ይገባኛል፣ የመጀመሪያው ምዕራፍን አጠናቅቄ ኤሌክትሪክ ኃይል አልቀረበልኝም፣ አላግባብ ክፍያዎች ተቀነሱብኝ፣ የመያዣ ገንዘቦች አልተከፈሉኝም እንዲሁም ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ ደረሰብኝ ላላቸው ጉዳቶች ካሳ መጠየቁን ቢቢሲ ተረድቷል።
ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ውድመት እና ዝርፊያ እንደደረሰበት የተናገሩት ምንጮች፤ በተለይም የኃይል መስመሩ "ሙሉ ለሙሉ"፣ ማሰሪያ ቡሎኖች እና ሐዲዱ መዘረፉን ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የክስ ሂደት በመሀል ኮርፖሬሽኑ እና ተቋራጭ ድርጅቱ ለድርድር ተቀምጠው ሂደቱ እንደዘገየ ምንጮች ገልፀዋል።
ነገር ግን ተቋራጩ ድርጅት በድርድር የጠየቀው የካሳ ክፍያ ከፍተኛ ሆኖ በመገኘቱ ጉዳዩን መቋጨት እንዳልተቻለ የኮርፖሬሽኑ ምንጮች ተናግረዋል።
"ከሥራ ተቋራጩ ጋር በድርድር ጉዳዩን ፈትቶ ተቋራጩ ወደ ፕሮጀክቱ እንዲመለስ እና ማጠናቀቅ የሚለው እንደ አቋም ተይዞ ነበር። ነገር ግን የተጠየቀው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም" ሲሉ አንድ የቢቢሲ ምንጭ ገልፀዋል።
ይህ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ውዝግብ ውስጥ የገባው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ተቋራጭ ያፒ መርከዚ ባቀረበው የአንድ ቢሊዮን ዶላር የካሳ ይገባኛል ክስ ኮርፖሬሽኑ "በከፊል" ማሸነፉ ተነግሯል።
የክሱ ሂደት ምሥጢራዊነቱ ተይዞ የቆየ ሲሆን፣ ባለፈው ሚያዚያ 10/2017 ዓ.ም. የግልግል ፍርድ ቤቱ ኢትዮጵያን "በከፊል" አሸናፊ ያደረገ ("partial award") ውሳኔ መስጠቱን ምንጮች ተናግረዋል።
ውሳኔው ከቀናት በኋላ ለኮርፖሬሽኑ እና ለፍትህ ሚኒስቴር እንደደረሳቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በአብዛኛው ኮርፖሬሽኑ ነፃ ተብሏል። ከፍተኛ መጠን ባለባቸው ክሶች ላይ ኃላፊነት የለበትም ወይም መከራከሪያው ተቀባይነት አግኝቶ ነፃ ተብሏል" ሲሉ አንድ ምንጭ ገልፀዋል።
በካሳ ይገባኛል ክፍያው ላይ ከቀረበው 80 በመቶ የሚሆን ክፍያ ውድቅ የተረገ ሲሆን፤ 20 በመቶ የሚሆነው ክፍያ ኢትዮጵያ ለመፈጸም ስሌት እና ግመታ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ይህም ስሌት ገለልተኛ በሆኑ ባለሙያዎች በሦስተኛ ወገን እንደሚካሄድ የጠቆሙት ምንጮች፤ ተቋራጩ ባቀረበው ተመን ሳይሆን "ፍትሃዊ" የሆነ ስሌት ይሠራል ብለዋል።
በዚህ ክርክር ኢትዮጵያ የውጭ የሕግ ባለሙያዎችን ሳትቀጥር በኢትዮጵያዊያን የሕግ ባለሙያዎች መወከሏም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ እና የኮርፖሬሽኑ የሕግ ክፍል ኃላፊ አቶ ካሳሁን ሙላት ጉዳዩን መያዛቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ በዓለም አቀፍ ክስ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ሲወከሉ ይህ የመጀመሪያው ጉዳይ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።
ቀጣይ ምዕራፍ የተባለው ስሌቱ ቢያንስ እስከ ስድስት ወር ሊወስድ እንደሚችል ምንጮች ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱን እንዲጠናቀቅ በመንግሥት በኩል አቅጣጫ መያዙን የተናገሩት ምንጮች፤ "ከፍተኛ ስርቆት" እና ሌሎች ጉዳቶች የደረሱበት የፕሮጀክቱ ዕጣ ፈንታ በሚመለከት፤ አጠቃላይ ሁኔታውን በገለልተኛ አካል በመገምገም ተመጣጣኝ የገበያ ዋጋ ላቀረበ ተቋራጭ ፕሮጀክቱ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
አዲስ ጨረታ ማውጣትን ጨምሮ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ አማራጮችን እንደሚያማትር ጠቁመዋል።
የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በአራት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ለ10 ዓመታት ሳይጠናቀቅ ዓለም አቀፍ ውዝግብ ውስጥ ገብቷል።
ፕሮጀክቱ 10 ጣቢያዎች ያሉት እና 12 ዋሻዎች፣ 52 ድልድዮች፣ ስምንት የኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች፣ 12 የራዲዮ መገናኛ ምሰሶዎች እና አንድ የጥገና ማዕከልን የያዘ ነው።
ይህ 1.7 ቢሊዮን ዶላር የተመደበለት የባቡር መስመሩ ማዕከላዊ ኢትዮጵያን ከሰሜን ኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኝ እና 392 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ነው።















