ከ10 በላይ ዋሻዎችን ያቆራረጠው የአዋሽ ወልዲያ የባቡር ሃዲድ

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
ኢትዮጵያ የባቡር ግንባታን ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ እንደገና ስትጀምር ከተጠነሰሱ ፕሮጀክቶች አንዱ መነሻውን አዋሽ አድርጎ መዳረሻውን ሃራ ገበያ [ወልዲያ] ያደረገው የባቡር መንገድ ነው።
የባቡር መንገዱ አጠቃላይ ርዝመቱ 392 ኪሎ ሜትር ሲሆን ግንባታው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተከናወነ ይገኛል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ የሚደርስ ሲሆን 270 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነው። ከኮምቦልቻ ሃራ ገበያ ያለው ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 122 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።
ግንባታው በሁለት ምዕራፍ እንዲከፈል የተደረገበት ምክንያት በወቅቱ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን ሙሉ በጀት ባለመገኘቱ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር አብዱልከሪም ሞሐመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የባቡር መንገዱን ግንባታ ለማከናወን በ2012 [እአአ] ስምምነት ተደርሶ በ2014 ደግሞ የምዕራፍ አንዱ ግንባታ ተጀመረ። 1.235 ቢሊዮን ዶላር የተያዘለት በጀት ነበር።
የዚህ የባቡር መንገድ ግንባታ [ምዕራፍ አንድ] በአሁኑ ወቅት 99 በመቶ ሥራው ተጠናቅቆ አገልግሎት ለመስጠት የኃይል አቅርቦት ብቻ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ሁለተኛው ምዕራፍ ዘግይቶ ፋይናንሱ ስለተገኘለት በቅርቡ የተጀመረ ነው። ከዚያም ባለፈ በኮሮናቫይረስ፣ በወሰን ማስከበርና በተለያዩ ምክንያቶች ተስተጓጉሏል።
በአሁኑ ወቅት ግንባታው 82 በመቶ መድረሱን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። በፍጥነት አጠናቅቆ አገልግሎቱን ለማስጀመር እየተሰራ ቢሆንም "ነገር ግን አሁንም የኃይል አቅርቦት ይዘገያል ብለን እንሰጋለን" ይላሉ ኢንጂነር አብዱልከሪም።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
ባቡር ፍሬን ስለሌለው ይጨርሰናል. . .
ግንባታው ከመጀመሩ በፊት ትልቁ ፈተና የአካባቢው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ነበር። ከአዋሽ ሃራ ገበያ ያለው አካባቢ ተራራማና ለባቡር ሃዲድ ግንባታ አመች ስላልነበር ዲዛይኑን በየቦታው እየሄዱ ማስተካከሉ ፈታኝ ሥራ ነበር ይላሉ ሥራ አስኪያጁ።
እነዚህን ተራራማ አካባቢዎች በአፈር ቆረጣ፣ በዋሻ እና በድልድይ ማስተካከል ዋነኛ የፕሮጀክቱ የትኩረት ነጥቦች ነበሩ።
በአካባቢው የባቡር መንገድ ግንባታ ሲከናወን ይህ የመጀመሪያ ነው። በዚህም ምክንያት ሕብረተሰቡ ስለባቡር መንገድ ግንባታና አገልግሎት እውቀት አልነበረውም።
እናም የሚናፈሱ ማናቸውንም አሉባልታዎች እንደወረዱ እውነት አድርጎ የመቀበል ችግር እንደነበርም ኢንጂነር አብዱልከሪም ያስታውሳሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አንደኛውና አስቸጋሪ የነበረው አሉባልታ "ባቡር ፍሬን የለውም፤ ወደእዚህ ከመጣ ሕዝቡን ይጨርሳል" የሚለው ነበር።
ሕብረተሰቡ በቂ መረጃ ስላልነበረው የተነገረውን ሁሉ እውነት አድርጎ ይወስድ ስለነበር የዚህን መረጃ ስህተትነት ለማስገንዘብ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱን ስራ አስኪያጁ ነግረውናል።
ሌላኛው፤ ምናልባትም በሁሉም ግንባታው በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ያጋጥም የነበረው የወሰን ማስከበርና የካሳ ችግር ነው። ባቡሩ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የሚሄድ ስለነበር ሁኔታውን በጣም አስቸጋሪ አድርጎታል።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
በአሁኑ ወቅት የምዕራፍ አንድ ሥራውና የካሳው ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል። አንዳንድ ለአፈር መድፊያና ለተለያዩ ሥራዎች ሲያገለግሉ የነበሩ ቦታዎችን ወደነበሩበት መመለስና ለሕብረተሰቡ መልሶ የማስረከብ ሥራ እየተሰራ ነው።
በምዕራፍ ሁለት ግን የካሳ ሁኔታው መቋጫ ያገኘው በቅርቡ ነው።
የኮሮናቫይረስን መከሰት ተከትሎ ሥራው ለተወሰነ ጊዜ ቁሞ ስለነበር ከካሳ ጋር ተያይዞ በተለይ ተሁለደሬ ወረዳ አካባቢ ከፍተኛ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር ኢንጅነር አብዱልከሪም ይናገራሉ።
ካሳ አንሶናል በሚል ከ2 ዓመት በፊት የተነሳ ቅሬታ ነበር። ካሳው ከተከፈለ በኋላ ቅሬታው በመነሳቱ ውሳኔ ለማሰጠት ረዥም ጊዜ ወስዷል።
በቅርቡ ግን በትራንስፖርት ሚንስትርና በክልሉ ፕሬዛዳንት [የአማራ ክልል] አማካኝነት ልዩ ውሳኔ ተሰጥቶ የካሳው ሁኔታ መስተካከሉን ገልጸዋል። ነገር ግን ከዚያ በፊት በካሳው ምክንያት ለረዥም ጊዜ የ55 ኪሎ ሜትር ሥራውን ማከናወን ሳይቻል ቆይቷል።
"እነዚህን ችግሮች ከቀረፍን በኋላ ግን የሕብረተሰቡ ተሳትፎና በፕሮጀክቱ ላይ ያሳደረው የእኔነት ስሜት ሥራችንን እንድናሳልጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቶልናል" የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ መጀመሪያ አካባቢ በማሕበረሰቡ ዘንድ ስለባቡር መንገዱ ግንባታ የነበረው ብዥታም ሆነ የካሳ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ መስተካከሉን ይገልጻሉ።
10 ኪሎ ሜትር ዋሻዎች እና70 ድልድዮች. . .
በአገራችን እስካሁን የዋሻ ቁፋሮ ሥራ ብዙም የተለመደ አይደለም። በተለይ ለትራንስፖርት በጣም አስፈሪ የነበረና ለመገንባትም ልዩ ክህሎትና ልምድ የሚፈልግ ነበር።
በእዚህ ፕሮጀክት ግን በተለየ ሁኔታ የዋሻና የድልድይ ሥራዎች የፕሮጀክቱ ልዩ ገጽታ በመሆን ተከናውነዋል። በፕሮጀክቱ ድልድዮች፣ ወንዝን ለማሻገር ብቻ ሳይሆን ተራራን ከተራራ ጋር ለማገናኘትም ተገንብተዋል። ይህ ሲደረግም እስከ 53 ሜትር የሚረዝሙ ድልድዩን የሚሸከሙ ምሰሶዎች ተገንብተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
ድልድዮቹና ዋሻዎቹ በርካታ ቴክኖሎጅዎችን በማጠናቀር የተገነቡ ናቸው ያሉት ኢንጅነር አብዱልከሪም፤ በተለይ ካራቆሬ አካባቢ የተገነቡት ድልድዮች በአካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ ይነሳል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ በአሰራር፣ በባሕሪና በቴክኖሎጅ አጠቃቀምም ከፍተኛና ልዩ ክህሎት የታከለባቸው ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ 12 ዋሻዎችን ያካተተ ሲሆን ረዥሙ የሚገኘው ከፕሮጅክቱ መዳረሻ ሃራ ገበያ [ወልዲያ] ትንሽ ቀደም ብሎ ነው። 2 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው።
በአጠቃላይ የአስራ ሁለቱም ዋሻዎች ርዝመት ሲደመር ደግሞ ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሆነ ኢንጅነር አብዱልከሪም ገልጸዋል። ይህም አካባቢው ምን ያክል ለባቡር መንገድ ግንባታ አስቸጋሪ እንደነበርና የታለፈበት ሂደት ውስብስብ መሆኑን የሚያሳይ ነውም ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
በተለይ ከ1.5 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ዋሻዎች ልዩ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ታክሎባቸው የተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ በአጋጣሚ በእነዚህ ዋሻዎች ውስጥ ባቡሩ ብልሽት ቢገጥመው ሰዎች ራሳቸውን ማዳን የሚችሉባቸው ሌሎች የተለዩ ዋሻዎች በዋናው ዋሻ ውስጥ እንደተሰሩ አብራርተዋል።
በፕሮጀክቱ ከ70 በላይ ድልድዮች ተገንብተዋል። በአጠቃላይ ከ6 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝሙ ናቸው። ትልቁ የግንባታው ድልድይ ካራቆሬ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፤ 1 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ድልድዩ የተሰራበት ምሰሶ ከፍታም 53 ሜትር የሚረዝም ነው።
ፕሮጀክቱን በበላይነት ኮንትራት ወስዶ የሚያከናውነው ያፒ መርከዚ የተባለ የቱርክ ኩባንያ ነው።
ኢትዮጵያውያን ንዑስ ተቋራጮች እና ሞያተኞችም በግንባታው ተሳታፊ ናቸው። በፕሮጀክቱ ከ6 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሞያተኞች በተለያዩ ጊዜዎችና የሥራ ዘርፎች ተሳትፈዋል

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
በተለይ በባቡር ምህንድስና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተማሩ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ሙያዊና ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች መሳተፋቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ከፍተኛ ልምድ የቀሰሙበት ሂደት ስለነበር ነገ ኢትዮጵያ በራሷ ተመሳሳይ ፕሮጀክት መገንባት ብትጀምር እነዚህ ሞያተኞች ከፍተኛውን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችል ክህሎት አዳብረዋል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ መጓተት. . .
ምዕራፍ አንድ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁን ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ። ነገር ግን የኃይል አቅርቦት ስላልተሟላ አገልግሎት መስጠት አልጀመረም።
በፈረንጆቹ 2012 የመጀመሪያው ኮንትራት ሲፈረም በጀቱ ወዲያው የሚገኝ ከሆነ ሙሉ ፕሮጀክቱ [392 ኪ/ሜ] በ42 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ ኮንትራት ተፈርሞ ነበር።
ነገር ግን የምዕራፍ ሁለት በጀቱ በወቅቱ ባለመገኘቱ ምክንያት የጊዜ ገደቡ እንደገና ተከልሶ በ72 ወራት ለማጠናቀቅ እቅድ ተቀምጦለታል። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሰሩ መሆናቸውን የሚገልጹት ኢንጅነር አብዱልከሪም፤ እንዲያም ሆኖ የኃይል አቅርቦት በጊዜው ስለመሟላቱ እርግጠኛ አይደሉም።
"ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ኃይል እንዲለቀቅ ጥያቄ አቅርበን ነበር" የሚሉት ኢንጅነር አብዱልከሪም፤ በተለይ የምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ አንድ ዓመት ስላለፈው "በተደጋጋሚ ጥያቄውን አቅርበናል፤ የባለቤትነት ችግር ነበር" ብለዋል።
የኃይል አቅርቦቱን ማን ያቅርብ? የሚለው ኃላፊነት የተሰጠው አካል አልነበረም፤ በመሆኑም ከብዙ ውይይት በኋላ መንግሥት ጣልቃ በመግባት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃይል እንዲያቀርብ ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚሁ መሰረትም ኃይል ለማቅረብ ኮንትራት ተሰጥቷል። በቅርቡ ኃይል ሲቀርብ የባቡር አገልግሎቱ ወዲያውኑ ይጀመራል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
የዋሻ ሥራውን አቁሙ. . .
ፕሮጀክቱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከባቡር ግንባታው ባሻገር ሌሎች የተለያዩ ሥራዎች ይካሄዳሉ።
በፕሮጀክቱ ምክንያት በተለይ ማሳቸው ከ25 በመቶ በላይ የተወሰደባቸው አርሶ አደሮች የተሰጣቸውን ካሳ ወደ አዋጭ ቢዝነስ እንዲቀይሩ ስልጠና መስጠታቸውን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ የተሠሩ 400 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ የማሳለጫ መንገዶች እና በከተማ ውስጥ የተሠሩ 70 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በመሥራት ለማሕበረሱቡ ማስረከባቸውንም ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ የሥራ ጉዞ ተሁለደሬ ላይ ተቢሳ የምትባል ቀበሌ ውስጥ የማይረሱት ገጠመኝ ማስተናገዳቸውን ኢንጅነር አብዱልከሪም ያስታውሳሉ።
በአካባቢው የዋሻ ቁፋሮ ሥራ ያከናውናሉ። ዋሻው 1.9 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። አካባቢው ከፍተኛ የውሃ ችግር ያለበት በመሆኑ ለፕሮጀክቱ ሠራተኞች ውሃ የሚመጣው ከሌላ ቦታ ነበር።
በውሃ እጥረት ምክንያትም ግማሹ ነዋሪ አካባቢውን ለቆ ወደ ሌላ ቦታ የሚሄድበት ቀሪው ደግሞ እስከ 10 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ውሃ የሚያመጣበት አካባቢ ነው ይላሉ ሥራ አስኪያጁ።
የዋሻ ቁፋሮ በሚሠራበት ወቅት ግን ያልተጠበቀ ነገር ተፈጠረ፤ ውሃ መፍሰስ ጀመረ።
ይህንን ተከትሎም ትልቅ የውሃ ጋን እንዳለ ተረዳን ያሉት ኢንጅነሩ "ተጨማሪ ጥናቶችን አካሂደን ውሃውን በማውጣት ስንለቀው፣ ሕብረተሰቡ ላይ የተፈጠረው ደስታ ልዩ ነበር" ይላሉ።
ነገር ግን ሕብረተሰቡ ውሃውን ከተመለከተ በኋላ ያልተጠበቀ ምላሽ ሰጠ፤ "የዋሻ ሥራውን አቁሙልን ውሃችንን ያጠፋብናል" የሚል ነበር።
ውሃው የማይቆም መሆኑን በማስረዳት ከነዋሪው ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ውሃውም እንዲወጣ ዋሻውም እንዲገነባ በመስማማት ሥራው ቀጠለ።
አሁን የዋሻ ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል። የአካባቢው ነዋሪም ለዘመናት ችግር ሆኖበት የነበረው የውሃ አቅርቦት በዋሻ ግንባታው ሳቢያ እንደተቀረፈለት ሥራ አስኪያጁ ገልጸውልናል።
ከጀማሪ ሲቪል መሃንዲስ ወደ የባቡር ፕሮጀክት ሃላፊ. . .
ኢንጅነር አብዱልከሪም ሞሐመድ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የተመረቁት በሲቪል ምህንድስና ነው። ሥራ የጀመሩት ደግሞ በአማራ ትራንስፖርት ባለስልጣን ውስጥ ነበር።
የመጀመሪያ ሥራቸው ከመተማ ገለጎ [ቋራ] በሚሰራው የጠጠር መንገድ ግንባታ ላይ በመሃንዲስነት ነበር። በዚሁ የምህንድስና ሙያ ለተወሰነ ጊዜ ካገለገሉ በኋላ የፕሮጀክቱ ማናጀር መሆናቸውን ይገልጻሉ።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ወደ ወሎ ገጠር መንገድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሃላፊነት ተመድበው ሠርተዋል። የተወሰነ ከሠሩ በኋላ ወደ ባህር ዳር በመመለስ የአማራ ክልል መንገዶች ባላስልጣን ምክትል ሃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
በሥራ ዘመናቸው በተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ ነበሩ። በመጨረሻም የክልሉ መንግሥት በሰጣቸው ሃላፊነት መሰረት "የአማራ መንገድ ስራዎች ድርጅት" የተባለ ተቋም መስርተዋል።
በ2003 ዓ. ም የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣይ ለሚገነቡ የባቡር መንገዶች ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሃንዲሶችን ወደ ውጭ አገር ልኮ ለማሰልጠን ምልመላ አካሄደ።
በብዙ የመንገድ ሥራዎች ላይ አሻራቸውን ያሳለፉት ኢንጅነር አብዱልከሪም ከተመረጡት 18 መሃንዲሶች መካከል አንዱ በመሆን ወደ ሩሲያ፣ ሴይንት ፒተርስበርግ ትራንስፖርት ዩኒቨርሲቲ ተልከው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በባቡር ምህንድስና ለሦስት ዓመታት ተከታትለው ተመልሰዋል።
በፈረንጆቹ 2014 የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ሥራ ሲጀመር ፕሮጀክቱን በሃላፊነት እንዲመሩ ተመደቡ። ሃላፊነቱን ሲረከቡ ሦስት ነገሮችን ለማሳካት አቅደው እንደነበር ያስታውሳሉ። ፕሮጀክቱን በሚፈለገው ጥራት ማከናወን፣ በተያዘለት በጀት ማጠናቀቅና በታቀደው ጊዜ ፕሮጀክቱን ለፍጻሜ ማብቃት።
ከእነዚህ እቅዶች መካከል የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ሙሉ በሙሉ የተሳኩ መሆናቸውን የሚገልጹት ኢንጂነር አብዱልከሪም፤ በተለያዩ ምክንያቶች የፕሮጀክቱ መጠናቀቂያ ጊዜ ግን መራዘሙን ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
የባቡር መንገዱ ሥራ ሲጀምር. . .
ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የባቡር መንገዱ 26 ባቡሮችን ያስተናግዳል። 20ዎቹ ባቡሮች የእቃ ማጓጓዣዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ስድስቱ ደግሞ የሰው ማጓጓዣዎች ናቸው።
ሁሉም ባቡሮች በቀን ቢሰሩ ከ4300 በላይ ሰዎችን ከአዲስ አበባ ወይም ከወልዲያ ጂቡቲ ማመላለስ ይችላሉ።
አንድ ባቡር እስከ 1 ሺህ 350 ቶን የመጫን አቅም አለው። በቀን ሁሉም ባቡሮች ሥራ ላይ ቢውሉ እስከ 27 ሺህ ቶን እቃ ማጓጓዝ ይችላሉ።
በአጭር ሰዓትና በአንድ ጊዜ ወደቦች ላይ የሚገኙ እቃዎችን የማንሳትና ወደ ወደቦች የማድረስ ሥራን ያሳልጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የባቡር ፕሮጀክቱ ከአዋሽ እስከ ሃራ ገበያ [ወልዲያ] ባለው የ392 ኪሎ ሜትር ርዝመት ውስጥ 4 ዋና እና 6 ንዑስ ጣቢያዎች አሉት።
አዋሽ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ኮምቦልቻ እና ሃራ ገበያ ያሉት ዋና ጣቢያዎቹ ናቸው። ከእዚህ በተጨማሪ የባቡር ብልሽት ቢያጋጥም ጥገና የሚደረግበት በአንድ ጊዜ ብቻ ስምንት ባቡሮችን መጠገን የሚችል ጋራጅ ኮምቦልቻ ላይ ተገንብቷል።

የፎቶው ባለመብት, AKH Railways Project
በቀጣይ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጨማሪ የባቡር መንገድ ፕሮጀክቶችን ሲሰራም ይህ ፕሮጀክት መነሻ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ከታጁራ ወደብ ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀው የባቡር መንገድ ግንባታ መዳረሻው ሃራ ገበያ ነው። በጥናት ላይ ያለው ከወልዲያ ወረታ፣ ከወረታ መተማ የባቡር መንገድም የዚሁ የባቡር መንገድ አካል ነው።













