እናቱን ‘በልቡ’ ይዞ የሮጠው ቴቦጎ፤ በኦሊምፒክ 200 ሜትር ወርቅ በማምጣት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ

ቦትስዋናዊው ሲሌ ቶቦጎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቦትስዋናዊው ሲሌ ቴቦጎ

በፓሪስ ኦሊምፒክ በ200 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ቦትስዋናዊው ሲሌ ቴቦጎ ወርቅ በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ።

ቴቦጎ ይህን አስደናቂ ድሉን በቅርቡ በሞት ለተለየችው እናቱ መታሰቢያ ማድረጉን ተናግሯል።

ከውድድሩ በኋላ “ወደ ውድድር ትራክ ስገባ እያንዳንዱ እርምጃ የማደርገው እሷን በማሰብ ነው” በማለት ባለፈው ግንቦት በድንገተኛ ሕመም በሞት ስላጣት እናቱ ተናግሯል።

የእናቱን የትውልድ ቀን ጫማው ላይ ጽፎ ወደ መሮጫ መም የገባው ቴቦጎ፤ “እርሷን በልቤ ይዤ መጓዜ ትልቅ መነሳሳት ይሰጠኛል። ከላይ ሆና እየተመለከተችኝ ነው። በጣም በጣም ደስተኛ ነች” በማለት ስሜታዊ ንግግር አድርጓል።

ሐሙስ ምሽት በተደረገው ውድድር ተጠባቂ የነበረው አሜሪካዊው ኖዋህ ላያልስ ነበር። ከቀናት በፊት በ100 ሜትር ወርቅ ያሸነፈው ላያልስ በ200 ሜትር እንዲሁ ድል በማድረግ ከጀማይካዊው ዩዜይን ቦልት ጋር ታሪክ ይጋራል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

አንገቱን ደፍቶ ወደ ሜዳ የገባው ቴቦጎ ግን በብዙ ፈንጠዝያ እና የመነቃቃት ስሜት ወደ ሩጫ መም የመጣውን ላይልንስ በሰፊ ልዩነት ቀድሞታል።

ቴቦጎ በ19.62 ሰከንድ ወርቁን የወሰደው ኬኔዝ ቤንድሬክ እና ኖዋ ላይልስን አስከትሎ ነው።

ከዚህ ውድድር በኋላ ላይልስ በኮቪድ-19 መያዙ ይፋ ተደርጓል።

ባለፈው ዓመት በቡዳፔስት በተደረገው የዓለም ሻምፒዮና በ100 ሜትር ላይልስ ወርቁን ሲያነሳ ቴቦጎ የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ የፓሪስ ኦሊምፒክ ከቀናት በፊት ላይልስ በ100 ሜትር ደምቆ ወርቅ ባጠለቀበት የ100 ሜትር ሩጫ፤ ቴቦጎ የጨረሰው 6ኛ ሆኖ ነበር።

ይሁን እንጂ የ21 ዓመቱ ቦትስዋናዊ ሳይጠበቅ በፓሪሱ 2024 ኦሊምፒክ አስደናቂ ድልን ተጎናጽፏል።

የአትሌቱ እናት ሴራዊታ ቴቦጎ

የፎቶው ባለመብት, Seratiwa Tebogo

የምስሉ መግለጫ, የአትሌቱ እናት ሴራዊታ ቴቦጎ ከልጇ ጋር አብራ እየተጓዘች በማበረታታት ትታወቃለች

ላይልስ ወደ ፓሪስ ያቀናው በ100 ሜትር፣ በ200 ሜትር፣ 4 በ100 ሜትር፣ 4 በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ወርቅ ለመሰብሰብ ነበር።

እስካሁን በ100 ሜትር ወርቅ እና በ200 ሜትር ነሐስ ያገኘው ላይልስ ከህመሙ አገግሞ 4 በ100 ሜትር፣ 4 በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ስለመወዳደሩ እርግጥ አይደለም።