ትራምፕ ለገና በዓል ለወታደሮቻቸው "የጀግና ክፍያ" እንደሚያደርጉ ገለፁ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ 1776 ዶላር "የጀግና ክፍያ" ለማድረግ ቃል ገቡ።

ለ1.45 ሚሊዮን የአሜሪካ ወታደሮች የሚደረገው ክፍያ የተወሰነ ገንዘብ የተገኘው ከታሪፍ መሆኑን አስታውቀዋል።

ረቡዕ ምሽት ለሀገራቸው ሕዝብ በቴሌቪዥን መልዕክት ያስተላለፉት ትራምፕ "ቼኩ ወጥቷል" ብለው ክፍያው ለገና በዓል እንደሚደርስ ተናግረዋል።

ትራምፕ በምጣኔ ሀብት እና በስተደኞች ጉዳይ አሳካሁ ያሉትን የዘረዘሩ ሲሆን ዲሞክራቶችን ደግሞ ክፉኛ ሲነቅፉ ተሰምተዋል።

ጠንከር ያለ ንግግር ያሰሙት ፕሬዝደንቱ አሜሪካ የተሻለ መንገድ ላይ እንዳለች ደጋግመው ሲናገሩ ነበር።

ትራምፕ የሸቀጥ ዋጋ እየቀነሰ ይመጣል ቢሉም አሜሪካዊያን በቤት ዋጋ፣ በሕፃናት ዕቃ እና በጤና ጉዳይ ደስተኛ እንዳልሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለ18 ደቂቃ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ "የጀግና ክፍያ" ያሉት ገንዘብ ጠቅላላ ወጪ 2.57 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ጠቅሰው "በሀገራችን የምስረታ ዓመት 1776 ስም" ይከፋፈላል ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ እንደሚሉት ገንዘቡ የተገኘው ከታሪፍ እና "ግዙፉ እና ውቡ ቢል" ብለው ከጠሩት በጀት ነው።

"ከወታደሮቻችን በላይ ይህ የሚገባው የለም" ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው እምብዛም አዲስ የሚባል ነገር አላሰሙም። አብዛኛው የንግግራቸው ክፍል ግነት እና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን የያዘ ነው።

ምጣኔ ሀብቱን ለማነቃቃት እንዲሁም በቀድሞው ፕሬዝደንት ባይደን የተከሰተ ነው ያሉትን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ የሚያደርጉትን ጥረት ደጋግመው ሲያወሱ ነበር።

ትራምፕ በንግግራቸው የባይደንን ስም ሰባት ጊዜ አንስተዋል።

"አሁን በአዲሱ አስተዳደር የዋጋ ግሽበት በአስደናቂ ፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው። ዲሞክራከት ፖለቲከኞች የሸቀጥ ዋጋ እንዲያሻቅብ ቢያደርጉትም እኛን ይህን ችግር እየፈታን ነው።"

ምንም እንኳ በአሜሪካ የእንቁላል እና የነዳጅ ዋጋ ቢቀንስም የሌሎች የምግብ ዕቃዎች ዋጋ አሁንም የሚነካ አልሆነም።

የመስከረም ወር የምጣኔ ሀብት አሀዞች እንደሚጠቀሙት የዋጋ ግሽበቱ 3 በመቶ ሲሆን ሸማቾች ይህንን ግሽበት መቋቋም እየቻሉ አይመስሉም።

ባለፈው ኅዳር በተለያዩ ግዛቶች በተካሄደ ምርጫ በርካታ ሪፐብሊካኖች መሸነፋቸው ይታወሳል። ትራምፕ ይህ የሆነው በሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብ ምክንያት መሆኑን አምነዋል።

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዋይት ሐውስ ለመዝለቅ የምርጫ ቅስቀሳ ባደረጉበት ወቅት ፈጣን ለውጥ አመጣለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

ፕሬዝደንቱ ሥልጣን ከያዙ 11 ወራት ቢያስቆጥሩም በርካታ አሜሪካዊያን የጓጉለት ፈጣን ለውጥ የመጣ አይመስልም።

ትራምፕ በሚመጣው የአውሮፓውያኑ ዓመት የአሜሪካ 250ኛ የምስረታ በዓል በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ቃል ገብተዋል።