ትራምፕ በተጨማሪ አገራት ላይ የጉዞ እገዳ ጣሉ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዞ እገዳቸው ውስጥ ተጨማሪ አገራት እንዲካተቱ ወሰኑ።

ዋይት ሀውስ እንዳለው እገዳው የተጣለው "የአሜሪካን ደኅንነት ለመጠበቅ ነው"።

እገዳው እአአ ጥር 1/2026 ይጀምራል። አጠቃላይ እገዳ ከተጣለባቸው መካከል ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያ እና ፍልስጤም ይገኙበታል።

ከፊል እገዳ ዝርዝር ውስጥ የነበሩት ላኦስ እና ሴራ ሊዮን አጠቃላይ እገዳ ውስጥ ተካተዋል። ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ እና ዚምባብዌን ጨምሮ ሌሎች አገራት ከፊል እገዳ ተጥሎባቸዋል።

በድጋሚ ሥልጣን የያዙት ትራምፕ ስደተኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል።

ከተለያዩ አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ላይ የሚደረገው ፍተሻ ጠንካራ አይደለም በሚል ትራምፕ ተችተዋል።

የተሰጣቸው ቪዛ ከሚፈቅድላቸው በላይ የሚቆዩ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን እንዲሁም በቪዛ አሰጣጥ ሙስና መንሰራፋቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም ከአሜሪካ የሚባረሩ ሰዎችን አገሮቻቸው እየተቀበሏቸው አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

ሁለት የአሜሪካ ብሔራዊ ዘቦች ላይ አንድ አፍጋኒስታናዊ መተኮሱን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት የትራምፕ አስተዳደር የጉዞ እገዳን ጨምሮ ስደተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ነው።

ትራምፕ የጉዞ እገዳ ሲጥሉ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። እአአ በ2017 ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የጣሉት የጉዞ እገዳ ትችት አስከትሏል። ሆኖም የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕ ውሳኔ እንዲጸና ወስኗል።

ዋይት ሀውስ እንዳለው የጉዞ እገዳው የተጣለባቸው አገራት "ተጨባጭ መሻሻል" እስከሚያሳዩ ድረስ ክልከላው ባለበት የሚቆይ ይሆናል።

መሻሻል ሊታይ ይገባል የተባለው የስደተኞች መረጃ አያያዝ እና መረጃው ለአሜሪካ መንግሥት የሚሰጥበት አሠራር ነው።

በሕጋዊ መንገድ በአሜሪካ ቋሚ መኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ስደተኞች፣ ቪዛ ያላቸው ሰዎች፣ ዲፕሎማቶች እና አትሌቶች በእገዳው አይካተቱም።

የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ጉዞ ከሆነ እንደየአስፈላጊነቱ ፈቃድ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ሙሉ እገዳ የተጣለባቸው አገራት

  • አፍጋኒስታን
  • ቡርኪና ፋሶ
  • በርማ
  • ቻድ
  • ኢኳቶሪያል ጊኒ
  • ኤርትራ
  • ሔይቲ
  • ኢራን
  • ላኦስ
  • ሊቢያ
  • ማሊ
  • ኒጀር
  • ሪፐብሊክ ኦፍ ዘ ኮንጎ
  • ሴራ ሊዮን
  • ሶማሊያ
  • ደቡብ ሱዳን
  • ሱዳን
  • ሶርያ
  • የመን
  • የፍልስጤም የጉዞ ሰነድ ያላቸው

ከፊል እገዳ የተጣለባቸው አገራት

  • አንጎላ
  • አንቲጓ እና ባርቤዶስ
  • ቤኒን
  • ቡሩንዲ
  • ኮት ዲቯር
  • ኩባ
  • ዶምኒካ
  • ጋቦን
  • ዘ ጋምቢያ
  • ማላዊ
  • ሞሪታንያ
  • ናይጄሪያ
  • ሴኔጋል
  • ታንዛኒያ
  • ቶጎ
  • ቶንጋ
  • ቬንዝዌላ
  • ዛምቢያ
  • ዚምባብዌ

በልዩ ሁኔታ የሚታይ- ከቱርክሜኒስታን የሚጓዙ ስደተኞች ላይ የተጣለው እገዳ ባይነሳም ከስደተኞች ውጭ ያሉ ቪዛዎች ላይ የተጣለው ክልከላ ተነስቷል።