እነ ዮሐንስ ዳንኤል የሽብር ወንጀል ምርመራ ሊከፈትባቸው አይገባም ሲሉ ጠበቃቸው ተከራከሩ

የፎቶው ባለመብት, ETH Federal Police
ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ አምባጓሮ ፈጥረው የሽብር ወንጀል ምርመራ የተከፈተባቸው ስድስት ግለሰቦች የሽብር ወንጀል ምርመራ ሊከፈትባቸው አይገባም ሲሉ ጠበቃቸው ተከራከሩ።
ጠበቃ ጀሚላ መስፍን መከራከሪያቸው ያቀረቡት በዮሐንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል) መዝገብ ስር የተካተቱ 6 ግለሰቦች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ተረኛ ችሎት በቀረቡ ወቅት ነው።
ከቀናት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ ለመብረር በዝግጅት ላይ በነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ አምባጓሮ በፈጠሩ ስድስት ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ መክፈቱን ፌደራል ፖሊስ አስታውቆ ነበር።
በዕለቱ አውሮፕላኑ በአካባቢ በነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ መብረር እንደማይችል ቢገለጽም፤ አውሮፕላን ላይ ተሳፍረው የነበሩት ግለሰቦች ከአውሮፕላን “አንወርድም” በማለት ከአየር መንገዱ ሠራተኞች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ታይተዋል።
ከፍርድ ቤት ውሎ በኋላ ጠበቃ ጀሚላ ለቢቢሲ ሲናገሩ ደንበኞቻቸው ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ መከፈት የለበትም በማለት የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጭምር መከራከራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ደንበኞቻችን በሽብር ወንጀል ሊጠየቁ አይገባም። በአዋጅ ቁጥር 1197/2012 አንቀጽ 3 መሠረት አንደ ሰው የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ተሰባሰበ የሚባለው ተመሳሳይ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኃይማኖታዊ እና የርዮተ ዓለም ዓላማ ለማሳካ አስቦ እና አልሞ ሲንቀሳቀስ ከሆነ ነው። በዚህ ጉዳይ ግን ደንበኞቻችን የተገናኙት በራሳቸው የተለያየ ጉዳይ ወደ መቀለ ለመብረር ሲሰናዱ ነው” ብለዋል።
ደንበኞቻቸው አየር መንገዱ የተለያየ ምክንያት እየሰጣቸው በረራቸውን አዘግይቶባቸው እንጂ የስድስቱ ሰዎች የበረራ ሰዓት የተለያየ እንደነበረ ጠበቃዋ ጨምረው ተናግረዋል።
“ስሜታዊ ሆነው አንወርድም ማለታቸው የዲስፕሊን ጥፋት ነው” ያሉት ጠበቃዋ፤ ይህ ጥፋት ፈጽሞ በሽብር ሕጉ መታየት የለበትም ብለዋል።
“ውረዱ ሲባሉ ‘በእህት ኩባንያው (የአየር መንገዱ) ስካይ ላይት ሆቴል አሳድሩን ወይም ቲኬታችን ይስተካከልልን በዚህ ምሽት የትም መሄድ አንችልም አንወርድም’ ነው ያሉት። . . . ይህ የሚያርፈው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 440 የመንግሥት አካል የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ አለመቀበል በሚል ነው” ብለዋል።
ጠበቃዋ እንዳሉት ከሆነ በትናንቱ የችሎት ውሎ ደንበኞቻቸው መጠየቅ ያለባቸው “ትዕዛዝ አለመቀበል” በሚለው ድንጋጌ መሆን አለበት ብለው መከራከራቸውን ገልጸው፤ “ይህ ድንጋጌ የሚያስቀጣው እስከ 1 ዓመት ድረስ ነው። እስከ አንድ ዓመት ለሚያስቀጣ ወንጀል ደግሞ ዋስትና አያስከለክልም” ብለዋል።
ጠበቃ ጀሚላ ደንበኞቻቸው ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው፣ በዋስ ቢወጡ የሚያሸሹት መረጃ አለመኖሩን በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው መጠበቅ አለበት ብለው መከራከራቸውን ገልጸዋል።
ጠበቃ ጀሚላ ደንበኞቻቸው ማሕበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ የመጠቀም ታሪክ አላቸው ሲሉ ለፍርድ ቤት ማስረዳታቸውን ጨምረው ይናገራሉ። “ዮሐንስ ዳንኤል ከዚህ ቀደም ቦረና እና ጎፋ የተቸገሩትን ሲረዳ ነበር። እንደውም ማሕበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ ሲጠቀም መቆየቱን ለችሎት በአጽንኦት አስረድተናል” ብለዋል።
ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ ለጉዞ በተዘጋጀ አውሮፕላን የሲቪል አቪዬሽን ሕግና አሰራር በመጣስ፣ የአየር መንገዱን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል፣ የደህንነት ባለሙያዎችን በመቅረጽ አየር መንገዱ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር ብሏል።
ይህን ተከትሎም ችሎቱ ዛሬ ፌደራል ፖሊስ በዮሐንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን ፣ ኤልያስ ድሪባ ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ በተባሉ ግለሰቦች የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል።












