በሶማሌ ክልል በኤምፖክስ በሽታ የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ ተለይቶ እንዲቆይ መደረጉ ተገለጸ

በኤምፖክስ የተያዘ ግለሰብ እጅ እና እግር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ፤ ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ተብሎ በታወጀው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) በሽታ የተጠረጠረ አንድ ግለሰብ በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲሆን መደረጉን አስታወቀ።

በተላላፊው በሽታ የተጠረጠረው ግለሰብ ናሙና ለተጨማሪ ምርመራ ወደ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መላኩን የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ አያንሌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊው እንደገለጹት የኤምፖክስ ምልክቶች የታዩበት ግለሰብ የተገኘው በክልሉ ፋፈን ዞን ቀብሪበያ ወረዳ ነው። ይሁንና በግለሰቡ ላይ የታየው ምልክት የኤምፖክስ በሽታ ስለመሆኑ እስካሁን ድረስ አለመረጋገጡን አስረድተዋል።

አቶ መሀመድ፤ “አሁን ገና ምልክቶች በዚያ አካባቢው ስላሉ፤ [ግለሰቡ] እንዲለይ ተደርጎ ናሙና እየተወሰደ ነው ያለው። እንጂ ገና ምንም ማረጋገጫ የለም” ሲሉ ጉዳዩ “የተጠረጠረ እንጂ የተረጋገጠ ኬዝ” አለመሆኑን አስረድተዋል።

በሶማሌ ክልል የማህበራዊ ትስስር ገፅ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከኤምፖክስ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት ያለው የቆዳ ቁስሎች ያሉበት ግለሰብ ፎቶ በመዘዋወር ላይ ይገኛል። የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ፤ በክልሉ በበሽታው የተጠረጠረው ግለሰብ በማህበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወረ ያለው ግለሰብ እንደሆነ አቶ መሀመድ ተናግረዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ “የተጠረጠረው በማህበራዊ ሚዲያ ፎቶ ላይ የነበረው [ግለሰብ] ነው። ግን ያው ኬዙ አልተረጋገጠም። ከአሁን በፊትም ሁለት ኬዝ የሚመሳሰል በሽታ ታይቷል። ግን ሌላ በሽታ ነው የሆኑት። የሚመሳሰሉ በሽታዎች ስላሉ ገና እንደዚህ ነው ማለት አንችልም። እንዲለይ (isolate) ተደርጓል ገና እስከሚረጋገጥ እናያለን” ብለዋል።

ከግለሰቡ የተወሰደው ናሙና ለተጨማሪ ምርመራ ወደ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲላክ መደረጉንም አቶ መሀመድ አስረድተዋል።

ምክትል የቢሮ ኃላፊው በበሽታው የተጠረጠው ግለሰብ አንድ እንደሆነ ቢገልጹም የክልሉ ጤና ቢሮ ከትናንት በስቲያ እሁድ ምሽት ባወጣው መግለጫ “የሁለት ሰዎች ናሙና ወደ ብሔራዊ ላብራቶሪ” መላኩን አስታውቆ ነበር።

ቢሮው በመግለጫው፤ በቀብሪበያ ወረዳ ያሰማራቸው የጤና ባለሙያዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ስድስት ግለሰቦች ከሁለት ሳምንት በፊት በአካባቢው “ሱጉርታ” ተብሎ የሚታወቀው የፈንጣጣ (Smallpox) በሽታ ምልክት ታይቶ እንደነበር ሪፖርት ማድረጋቸውን አስታውቋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ምልክቱ የታየባቸው እንዚህ ግለሰቦች ከያዛቸው በሽታ “መዳናቸውንም” መግለጫው ጠቅሷል። ይሁንና ይህ አይነቱ ምልክት አባት እና ልጅ በሆኑ ሁለት ግለሰቦች ላይ በድጋሚ መታየቱን የገለጸው ቢሮው፤ ሁለቱ ግለሰቦች ያሉበት ሁኔታ “እየተሻሻለ” መሆኑን ጠቅሷል።

ከበሽታው ያላገገሙት ሁለት ግለሰቦች ናሙና “ለተጨማሪ ማረጋገጥ” ሲባል ወደ “ብሔራዊ ላብራቶሪ” መላኩን ቢሮው በመግለጫው አስታውቋል።

ቢቢሲ፤ መረጃው ለማረጋገጥ ወደ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ሚኒስቴር ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች ምላሽ አላገኙም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 16/2016 ኤምፖክስን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ “እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተጠረጠረም ሆነ በበሽታዉ የተያዘ ታማሚ እንደሌለ” አስታውቀው ነበር።

የጤና ሚኒስቴር በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ለመቆጣጠር የጎረቤት ሀገር ኬንያ አዋሳኝ በሆኑት በሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ የመውጫ እና መግቢያ ኬላዎች ላይ “የቅኝት እና የልየታ” ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

በሶማሌ ክልል ይህ አይነቱ ተግባር እየተከናወነ ያለው “ከሶማሊላንድ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ድንበሮች” ጋር በተያያዙ የመውጫ እና መግቢያ ኬላዎች ላይ መሆኑን የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊው አቶ መሀመድ ተናግረዋል። በእነዚህ መግቢያዎች የሚተላለፉ ሰዎች አጠራጣሪ ምልክት ከታየባቸው እንዲለዩ ተደርጎ የናሙና ምርመራ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ከሁለት ሳምንት በፊት ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም. ኤምፖክስን ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ብሎ ያወጀው፤ የበሽታው አዲስ ዝርያ በምስራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሀገራት መፍጥነት መዛመት ከጀመረ በኋላ ነበር።

በሽታው ከተገኘባቸው ሀገራት መካከል ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ብሩንዲ የሚገኙ ሲሆን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ከጥር ወር አንስቶ 14 ሺህ ገደማ ሰዎች መያዛቸው ተረጋግጧል። በሀገሪቱ 450 ሰዎች በበሽታው የተነሳ ህይወታቸው አልፏል።

የቆዳ መቆሰልን የሚያስከትለው ኤምፖክስ፤ በበሽታው የተያዘን ሰው ሊገድ የሚችል ነው። በሽታው ከተያዙ ከ100 ሰዎች ውስጥ አራቱ ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል።

ኤምፖክስ፤ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በሚኖር የቆዳ ንክኪ እና የግብረ ስጋ ግንኙነት ይተላለፋል። በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በቅርብ ርቀት ማውራት ወይም መተንፈስም ተጋላጭ ያደርጋል።