ሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን አሰማራች

ታራሚ የእሳት አደጋ ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በደቡባዊ ካሊፎርኒያ፣ ሎስ አንጀለስ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለውን የሰደድ እሳት ለመግታት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ተሰማሩ።

በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል የተባለውን ይህንን የሰደድ እሳት ለማጥፋት ወደ 939 የሚሆኑ እስረኞች በካሊፎርኒያ የማረሚያ እና መልሶ ማቋቋም መምሪያ (ሲዲሲአር) በሚመራው የበጎ ፈቃድ ፕሮግራም ታቅፈው በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፉ ነው ተብሏል።

ባለፈው ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም. በሎስ አንጀለስ ተቀስቅሶ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለውን የሰደድ እሳት ለማጥፋት እየተሳተፉ ያሉ ታራሚዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል።

ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ከ10 ሺህ በላይ ህንጻዎችን ያወደመው እና 37 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን መሬት ያቃጠለውን ሰደድ እሳት ለመግታት በሺዎች የሚቆጠሩ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተሰማርተዋል።

በሰደድ እሳቱ ት ቢያንስ እስካሁን 11 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ታራሚዎቹ የእሳት አደጋ ተከላካዮች በመንግሥት ከሚተዳደሩ 35 የእሳት አደጋ ካምፖች ሥልጠና የወሰዱ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት እሳቱን በማጥፋት የተሰማሩት ከ900 በላይ የሆኑት ታራሚዎች በዚህ ፕሮግራም ከታቀፉት 1870 ታራሚ የእሳት አደጋ ተከላካዮች መካከል ግማሽ ያህሉን ይይዛሉ።

ታራሚዎቹ የእስር ቤቱን መለያ ብርቱካናማ ቀለም ያለው ሙሉ ቱታ ለብሰው ከካሊፎርኒያ የደን እና የእሳት አደጋ መከላከያ ጥበቃ (ካል ፋየር) ሠራተኞች ጋር እሳቱን እያጠፉ ይገኛሉ።

ታራሚ የእሳት አደጋ ተከላካዮች "የእሳት መዛመትን ለመግታት ሌት ተቀን እየተፋለሙ ነው" ሲል የታራሚዎች መልሶ ማቋቋሚያ መምሪያ ለቢቢሲ በላከው ኢሜይል ገልጿል።

ታራሚዎችን በእሳት አደጋ የማጥፋት ፕሮግራሞች ማሳተፍ ከአውሮፓውያኑ 1946 ጀምሮ ሲካሄድ የነበረ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሮግራሙ ተጋላጭ የሆኑ ታራሚዎችን የሚበዘብዝ ነው በማለት የሚተቹ እንዳሉ ሁሉ ደጋፊዎች በበኩላቸው የተሃድሶው ሂደት የሚያመጣ ለውጥ ነው የሚሉም አልታጡም።

መንግሥት ለታራሚዎች የቀን ደመወዝ ከ5.80 እስከ 10.24 ዶላር የሚከፍል ሲሆን፣ በተጨማሪም በድንገተኛ አገልግሎቶች ሲሰማሩ ተጨማሪ 1 ዶላር በቀን ይከፈላቸዋል።

ይህ ክፍያ ታራሚ ካልሆኑ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ጋር ሲነጻጸር ሽርፍራፊ ነው። በካሊፎርኒያ ያሉ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በየዓመቱ 100 ሺህ ዶላር ይከፈላቸዋል።

"ከሌሎች አጠገባችን ካሉ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ጋር ሲነጻጸር የሚከፈለን በሳንቲም ደረጃ ነው። እኛ ርካሽ ሠራተኞች ነን" ሲል የቀድሞ ታራሚ የእሳት አደጋ ተከላካይ እና ለትርፍ ያልተቋቋመ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ተከላካይ ሠራተኞች ምልመላ ፕሮግራምን የሚመራው ሮያል ራሜይ ይናገራል።

"እሳቱን ለማጥፋት ስትታገል ሕይወትን ካጣህ ምንም ጥቅም አታገኝም" ይላል።

አክሎም "ምንም ዓይነት ሽልማት አታገኝም። በእሳት አደጋ ተከላካይነት እውቅና አታገኝም" የሚለው ሮያል ራሜይ የራስን የሞት የምስክር ወረቀት መፈረም ያህል ነው ሲልም ይተቻል።

ፓሊሳድስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰደድ እሳት በሎስ አንጀለስ የተቀሰቀሰው ማክሰኞ ዕለት ሲሆን፣ በግዛቲቷ ትልቁ ነው።

የፓስፊክ ፓሊሳድስ አካባቢን ጨምሮ ከ17200 ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሰፊ ግዛት አውድሟል። ኢተን የተሰኘው ደግሞ በሰሜናዊ የሎስ አንጀለስ እና አልታዴና ባሉ ከተሞች እየተዛመተ የሚገኝ ሲሆን፣ 10600 ሄክታርን መሬት በመሸፈን በግዛቲቷ ሁለተኛው ትልቁ እሳት ሆኗል።

ሦስተኛው ሰደድ እሳት ኸረስት የሚሰኝ ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት ተከስቶ ከሳን ፈርናንዶ በስተሰሜን በኩል እየተዛመተ ይገኛል። ይህም እሳት 855 ሄክታርን ይሸፍናል።

ሌላኛው ሊዲያ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በሎስ አንጀለስ በስተሰሜን ተራራማዋ አክተን አካባቢ ተቀስቅሶ ወደ 350 ሄክታርን መሬት በመሸፈን ቦታ ላይ ተዛምቷል።