አሜሪካዊው ራፐር ጄይዚ የ13 ዓመት ታዳጊ ከ24 ዓመታት በፊት ደፍሯል በሚል ከዲዲ ጋር ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊው ራፐር ጄይዚ ከሾን ዲዲ ኮምብስ ጋር በመሆን አንዲት የ13 ዓመት ታዳጊን በማደንዘዝ ደፍሯል የሚል ክስ ቀረበበት።
ታዳጊዋ በሁለቱ ራፐሮች የተደፈረችው ከ24 ዓመታት በፊት በነበረ ፓርቲ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ማንነቷ ያልተገለጸው ከሳሽ በኒውዮርክ ከኤምቲቪ የቪዲዮ የሙዚቃ ሽልማት በኋላ በአንድ የቤት ፓርቲ ላይ እንደተደፈረች እና በወቅቱም አንዲት ታዋቂ ሴት በክፍሉ ውስጥ ነበረች ብላለች።
ራፐሩ ጄይዚ ወይም በትክክለኛ ስሙ ሾን ካርተር ክሱን አጣጥሎ "ገንዘብ ለማግኘት የማስፈራራት ሙከራ" ሲል ውድቅ አድርጎታል።
ከጥቂት ወራት በወፊት በህገወጥ በወሲብ ዝውውር እና ሌሎች ወንጀሎች ተከሶ ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ዲዲ የአሁኑን ክስ ውድቅ አድርጎታል።
ክሱ በመጀመሪያ የቀረበው በጥቅምት ወር ላይ ሲሆን ጄይዚን እንደ ሌላ ተጨማሪ ተከሳሽ ለማስገባት ያለፈው እሁድ እለት በድጋሚ ቀርቧል።
ቢቢሲ የጄይዚን ጠበቃ አሌክስ ስፒሮን እንዲሁም የሚዲያ ቃለ አቀባዩን አስተያየት ጠይቋል።
ክሱ የተመሰረተው በኒውዮርክ የጥቃት ሰለባዎች ጥበቃ ስር ሲሆን ያቀረቡትም የህግ ባለሙያው ቶኒ ቡዝቢ ናቸው። የህግ ባለሙያው በቅርብ ወራት ውስጥ በራፐሩ ዲዲ ላይ ወሲባዊ ጥቃቶች እና የመድፈር ወንጀሎች በርካታ ክሶችን አቅርበዋል። የሂፕሆፕ አርቲስቱ ሚያዝያ መጨረሻ ላይ ችሎት ላይ ይቀርባል።
"የእኔ ጠበቃ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ የማስፈራሪያ ደብዳቤ ቶኒ ቡዝቤ ከተባለ የህግ ባለሙያ ደርሶታል" ሲል ራፐሩ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ አትቷል።
"የህግ ባለሙያው ስሌቱ እንዲህ አይነት ክሶች ሊያስከትሉት የሚችለውን መዘዝ በመፍራት በገንዘብ እደራደራለሁ ብሎ ጠብቆ ነበር" ብሏል።
"አልገባህም ! ውጤቱ ተቃራኒ ነው። እንዲያውም አጭበርባሪነትን ለህዝብ በዚህ መልኩ እንዳጋልጥ ነው የገፋፋኝ። አንዲትም ሳንቲም አላቀምስህም" ብሏል።
የዲዲ ጠበቆች በበኩላቸው ይህ የተሻሻለው ክስ "ልክ በዲዲ ላይ እንደተደረገው ታዋቂ ሰዎች በነሱ ላይ ሃሰተኛ ዜናዎች እንዳይሰራጩ በመስጋት ገንዘብ እንዲከፍሉ ለማድረግ የሚሸረብ አሳፋሪ ስራ ነው" ብለዋል።
የፍትህ ሂደቱ ዲዲ ከቀረቡበት ወንጀሎች ነጻ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። ዲዲ ሌሎች 30 ክሶች ቀርበውበታል። በእሁዱ መዝገብ ላይ ስሟ ያልተገለጸው ከሳሽ በአውሮፓውያኑ 2000 ማንሃተን የኤምቲቪ የሽልማት አዳራሽ አንድ ጓደኛዋ እንዳደረሰቻት ተናግራለች።
ወደ ሙዚቃ አዳራሹ ለመግባት ስትሞክር የሊሞዚን አሽከርካሪዎች አገኘች።
አንደኛው ሹፌር የዲዲ ተቀጣሪ እንደሆነ እና "ራፐሩ ለሚፈልገው ነገር ተመራጭ ነሽ" እንዳላት ክሱ ያትታል።
አሽከርካሪው የዚያኑ ዕለት ምሽት ዋይት ሃውስ ወደሚደረግ ፓርቲ ወሰዳት።
ፓርቲው ላይ ስትደርስ አንድ ሰነድ እንድትፈርም አደረጓት። ግለሰቧ ያየችውን ነገር እንዳትገልጽ የሚያስር ስምምነት ነው ብላ ታስባለች። በፓርቲው ላይ በርካታ ታዋቂ ሰዎች እንደነበሩ እና ኮኬይን ጨምሮ የተለያዩ አደንዛዥ ዕጾች ነበሩ ተብሏል።በክሱ መሰረት አንዲት አስተናጋጅ መጠጥ ለታዳጊዋ ሰጠቻት እና ይህም ሞቅ ስላደረጋት ለማረፍ አንድ ክፍል ውስጥ ገባች። ክሱ እንደሚያትተው ከዚያም ዲዲ፣ ጄይዚ እና ሌላ ስሟ ያልተገለጸ ታዋቂ ሴት ወደ ክፍሉ ገቡ። ዲዲ በሚያስደነግጥ እይታ እየተመለከታት ቀርቦ ከያዛት በኋላ "ለመጨፈር ዝግጁ ነሽ" እንዳላት ክሱ አስፍሯል።
በመቀጠል ጄይዚ ያዛት እና ከደፈራት በኋላ ዲዲም እንዲሁ ተከትሎ መድፈሩን እና ይህች ታዋቂ ግለሰብ እየተመለከተች እንደነበር ክሱ ይገልጻል።
ታዳጊዋ በምትደፈርበት ወቅት ስትታገል እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ዲዲ በመገረም ሲተዋትም እንዳመለጠች ያትታል።












