በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በአዲስ አበባ አገረ ስብከት መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, eotc
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ውስጥ አለ በተባለ ብልሹ አሠራር እና ጉቦ ምክንያት የተከሰተው ውዝግብ እና መካሰስ እየተካረረ ሄዷል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በአዲስ አበባ አገረ ስብከት ውስጥ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለመቀጠር ከፍተኛ ገንዘብ እጅ መንሻ እንደሚጠየቅ መዘገቡን ተከትሎ ውዝግብ እና የደብዳቤ ምልልስ ቀጥሏል።
የአዲስ አበባ አገር ስብከት የቀረበውን ክስ “ሐሰተኛ” እና ‘ስም የማጥፋት’ ድርጊት ነው በማለት ያስተባበለ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ መግለጫ የሰጠው ጠቅላይ ቤተ ክህነት አገረ ስብከቱ ለቀረበበት የሙስና ክስ የሰጠው ምላሽ ‘የከለላ መግለጫ’ እንደሆነ ገልጿል።
ጉባኤው የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ለቀረበበት ክስ ከሰጣቸው የማስተባበያ ማስረጃዎች ውስጥ በቅጥር ጉዳይ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር ተናቦ እየሠራ መሆኑን የገለጸው “ሐሰት ነው” በማለት አስተባብሏል።
ጠቅላይ ቤተ ክህነት አገረ ስብከቱ ይታይበታል ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚመረምሩ እና መፍትሔ የሚያመላክቱ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ መስከረም 9/ 2017 ዓ.ም. መሰየሙን አስታውቆ ነበር።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት መስከረም 10/ 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ኮሚቴውን እንደማይቀበለው ገልጿል።
በዚህም ሳቢያ ሁለቱ የቤተክርስቲያኗ አካላት በተከታታይ እያወጧቸው ያሉት መግለጫዎች እና ደብዳቤዎች ውዝግቡ መካረሩን ይፋ ያወጡ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቤተ ክርስቲያኒቱ ከገጠማት ፈተናዎች መካከል የቅርቡ ሆኗል።
ለኮሚቴው መቋቋም የሚያበቃ ማስረጃ እና ቅሬታ የለም ያለው የአዲስ አበባ አገረ ስብከት፤ ውሳኔው “በመላምት ላይ የተንተራሰ ነው” ሲልም አጣጥሏል።
አገረ ስብከቱ እርምጃውን “ክፍፍል” ለመፍጠር የተፈጸመ ነው በማለትም ጉዳዩን በኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ከተፈጠሩ ክስተቶች ጋር አመሳስሎታል።
በአገረ ስብከቱ ውስጥ ችግር ካለም ዋነኛው የችግሩ አካል ጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው ሲል ትችት የሰነዘረ ሲሆን፤ ምርመራ ካስፈለገም ጉዳዩ መታየት ያለበት የሁለቱ አደረጃጀቶች የበላይ በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ ነው ሲል የገለልተኛነት ጥያቄ አንስቷል።
በመግለጫ ጠንከር ያለ መልስ እየተሰጣጡ ያሉት ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ውዝግባቸውን ቀጥለዋል።
ጠቅላይ ቤተ ክህነት አርብ ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ የአገረ ስብከቱን መግለጫ “ከእውነት ያፈነገጠ ነው” ሲል ተቃውሞታል።
ለዚህም ማሳያዎችን የጠቀሰው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አጥኚ ኮሚቴውን የሰየመው ቅሬታ በመቅረቡ እንደሆነ ጠቅሶ፤ “በቅርቡ” 439 ሠራተኞች አስተዳደራዊ በደል ደረሰብን ብለው ቅሬታ ማቅረባቸውን እና 152 ሠራተኞች ደግሞ ከሥራ መባረራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ጠቅላይ ቤተ ክህነት ባወጣው ዘለግ ያለ ምላሽ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት “የአዲስ አበባ አገረ ስብከት 577 የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አገልጋይ ሠራተኞችን” ማባረሩንም ጠቁሟል።
አገረ ስብከቱ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው ሲልም የቤ ክርስቲያኒቱን ሕግ የጠቀሰ ሲሆን፤ ብልሹ አሠራሮች አይጣሩ ማለት ጥፋተኝነትን እንደማረጋገጥ ይቆጠራል ብሏል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቷ እና ምዕመናን ላይ በደረሱ ጥቃቶች እና በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ በተፈጠሩ ክፍፍሎች ፈተና ውስጥ እንደገባች በተደጋጋሚ አስታውቃለች።
በተለይም በ2015 ዓ.ም. ሦስት አባቶች ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቷ ነጥለው ሲመተ ጵጵስና ማድረጋቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ውዝግብ መፈጠሩ እና መንግሥትም በጣልቃ ገብነት መከሰሱ አይዘነጋም።
በትግራይ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ በጦርነቱ ወቅት የቤተክርስቲያኗ መሪዎች 'አብረውን አልቆሙም፤ የተፈጸመውንም አላወገዙም' በሚል በትግራይ የሚገኙ አባቶች ከማዕከላዊው ሲኖዶስ እራሳቸውን መለየታቸውም ይታወቃል።












