እስራኤል በቤይሩት ላይ የፈጸመችውን አስከፊ ጥቃት ተከትሎ ሄዝቦላህ በርካታ ሮኬቶችን አስወነጨፈ

በሮኬት የወደመ መኖሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እስራኤል በቤይሩት ላይ የፈጸመችውን አስከፊ ጥቃት ተከትሎ ሄዝቦላህ ወደ 250 የሚጠጉ ሮኬቶችን ከሊባኖስ ድንበር በኩል ማስወንጨፉን የእስራኤል ጦር አስታወቀ።

እስራኤል የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ አስከፊ የሚባለውን የአየር ጥቃት በመዲናዋ ቤይሩት ማድረሷን ተከትሎ ነው ሄዝቦላህ ሮኬቶቹን ያስወነጨፈው።

ሄዝቦላህ ባስወነጨፋቸው ሮኬቶች በሰሜን እና በመካከለኛው እስራኤል በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ህንጻዎች መጎዳታቸውን የእስራኤል ፖሊስ አስታውቋል። የተወሰኑት በቴልአቪቭ አቅራቢያ እንደሚገኙም ነው ፖሊስ ያከለው።

እስራኤል ቅዳሜ እለት በማዕከላዊ ቤይሩት ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 29 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

እስራኤል እና ሊባኖስ በኢራን ከሚደገፈው ሄዝቦላህ ጋር የሚደረገውን ውጊያ ለማቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን የእስራኤል ሚዲያዎች እሁድ ዕለት ዘግበዋል።

በሊባኖስ ከባድ የእሳት አደጋ መነሳቱን ተከትሎ በቴልአቪቭ አካባቢ የሮኬት ቁርጥራጮች መውደቃቸውን መረጃዎች እንደደረሰው የእስራኤል ፖሊስ ገልጿል።

በአንድ የመኖሪያ ሰፈር ላይ በቀጥታ የደረሰ ጥቃት “ቤቶች በእሳት መያያዛቸው እና መውደማቸውን” የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታውቋል።

በቴልአቪቭ አቅራቢያ በምትገኘው ፔታ ቲክቫ እና በሰሜናዊዎቹ ሃይፋ፣ ናሃሪያ እና ክፋር ብሉም ሮኬቶች መውደቃቸውን የእስራኤል ሚዲያ ዘግቧል።

በቤይሩት ለሚፈጸሙ ጥቃቶች አጸፋዊ ምላሽ በቴልአቪቭ እንደሚደረግ ቃል የገባው ሄዝቦላህ በከተማዋ እና በአቅራቢያው በሚገኙ ሁለት ወታደራዊ ጣቢያዎችን መትቻለሁ ብሏል።

በኋላም የእስራኤል መከላከያ ኃይል በቤይሩት ደቡባዊ ከተማ ዳርቻ የሄዝቦላህ ምሽግ በሆነችው ዳሂ ውስጥ የሚገኙ የጦሩ ማዘዣ ማዕከላት ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

እስራኤል በማዕከላዊ ቤይሩት ያለምንም ማስጠንቂያ በፈጸመችው የከፋ የአየር ጥቃት የሟቾች ቁጥር ወደ 29 ከፍ ማለቱን እና በአጠቃላይ በአገሪቱ ቅዳሜ ዕለት የተገደሉ ሰዎች 84 መሆኑን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የእስራኤል መከላከያ ቅዳሜ ዕለት የፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ ባይኖርም የእስራኤል ሚዲያዎች የሄዝቦላህ ከፍተኛ ባለስልጣን መሃመድ ሃይዳርን ለመግደል ሙከራ አድርገው እንደነበር ዘግበዋል።

እስራኤል በሊባኖስ ላይ አጠናክራ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ3 ሺህ 670 በላይ ሊባኖሳውያን ተገድለዋል እንዲሁም ቢያንስ 15 ሺህ 400 ሰዎች ቆስለዋል። በተጨማሪም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለስልጣናት ገልጸዋል።