ኢራናዊው ተቃዋሚ እስረኛ ሦስት ጊዜ የምስለ ሞት ፍርድ እንደተፈጸመበት ተነገረ

ግለሰቡ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል በፍርድ ቤት ተከራክሯል

የፎቶው ባለመብት, SAHAND NOORMOHAMMADZADEH

በኢራን መንግሥትን በመቃወም ከሚደረጉ ሰልፎች ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ውለው የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው ስድስት ሰዎች መካከል አንዱ፣ በእስር ቤት ሦስት ጊዜ የምስለ የሞት ቅጣት እንደተፈፀመበት ምንጮች ለቢቢሲ ፋርስ ተናገሩ።

በቴህራን የሚገኘው አብዮታዊ ፍርድ ቤት የ27 ዓመቱን ሳሃንድ ኑር መሐመድ ዛዴህ “በፈጣሪ ላይ በሚፈጸም ጠላትነት’’ ወንጀል ነበር ባለፈው ወር ጥፋተኛ ያለው።

የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ በማቃጠል ብሎም የሕዝብ መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበት ነበር።

ኑር መሐመድ ዛዴህ ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት ዐይኑን በማሰር ለስቅላት የሚሄዱ ሰዎች በሚቀመጡበት ወንበር ላይ ተቀምጦ እንዲሄድ ተደርጓል ሲሉ ምንጮች ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕግ መርሆዎች መሠረት በእስር ላይ ባሉ ሰዎች ላይ እንዲህ ያለ ጭካኔ የተሞላበት ወይም አዋራጅ አያያዝ የተከለከለ ነው።

የኢራን የፍትህ አካላት ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ እስካሁን በስድስት ተከሳሾች ላይ “በፈጣሪ ላይ በሚፈጸም ጠላትነት” እና “በምድር ላይ በሚፈጸም የሙስና ወንጀል” የሞት እንደተፈረደባቸው አስታውቀዋል።

ምንም እንኳን የፍርደኞቹ ማንነት ባይገለጽም የኑር መሐመድ ጠበቃ ግን ደንበኛቸው እንደሚገኝበት ባለፈው ቅዳሜ በሰጡት የቪዲዮ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የፍትህ አካላት የዜና ወኪል የሆነው ሚዛን ባለፈው ወር እንደዘገበው ኑርመሐመድ “የሕዝብ ንብረት በማውደም፣ የአገሪቱን ሰላም እና ፀጥታ በማደፍረስ እና ከእስላማዊ መንግሥት ጋር በመጋጨት” በሚሉ ክሶች በአብዮታዊ ፍርድ ቤት ፊት ቀርቧል።

እንደ ማስረጃም ኑር መሐመድ ነው ብለው የጠረጠሩትን እና የፊት መሸፈኛ ጭንብል ያጠለቀ ግለሰብ በባቡር መስመሮች መካካል እቃ ሲያስቀምጥ ብሎም የሚነድ የቆሻሻ መጣያ ወደ መንገድ ሲገፋ የሚያሳይ ቪዲዮ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።

ተከሳሹ በፍርድ ቤት ቀርቦ ንፁህ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ጠበቃው ግን ደንበኛቸው በቪዲዮ ላይ የሚታየውን ጭንብል ያጠለቀ ሰው ለመሆኑ ምንም አይነት ማስረጃ የለም ሲሉ መሟገታቸው ተዘግቧል።

የቢቢሲ ፐርሺያን ምንጮች እንደገለጹት ወላጅ እናቱ የልብ ህመም እንዳጋጠማት እና ከመሞቷ በፊት ሊያናግራት ከፈለገ በእምነት ቃሉ ላይ መፈረም እንዳለበት በሐሰት በመርማሪዎች እንደተነገረው ገልጸዋል።

አንድ ቴህራን ውስጥ ያለ ጠበቃ እንዲህ ዓይነቱ ደብዳቤ የጥፋተኝነት ክስን አምኖ እንደመቀበል ይቆጠራል ይላሉ።

የኑር መሐመድን የጥፋተኝነት ውሳኔ ተከትሎ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እሱ እና ሌሎች የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ተከሳሾች “የይስሙላ የፍርድ ሂደት” ውስጥ አልፈዋል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳለው ገልጿል።

ይህ ፍርድ ምንም አንኳን ይግባኝ ሊባል ቢችልም የፍትህ ተርጓሚው ኃላፊ ጎላምሆሴን ሞህሴኒ ኢጄይ ቅጣቱ በቅርቡ እንደሚፈፀም ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።