ናይጄሪያዊቷ ሼፍ በትልቅ ድስት ምግብ በማብሰል የዓለምን ክብረ ወሰን ልትይዝ ነው

ለረጅም ሰዓት ምግብ በማብሰል የዓለም የክብረ ወሰን መዝገብ ላይ ሰፍራ የነበረችው ናይጄሪያዊቷ ሼፍ ሄልዳ ባቺ ሌላ ክብረ ወሰን ለመያዝ እየጣረች ነው።
ሼፏ በጊነስ ዎርልድ ሪከርድ ላይ በአዲስ ሥራ ለመስፈር በግዙፍ ድስት በምዕራብ አፍሪካ ተወዳጅ የሆነውን ከሩዝ የሚዘጋጀውን ጆሎፍ የተባለውን ምግብ አብስላለች።
ሄልዳ ሌጎስ ውስጥ ይህንን ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ የምግብ ማብሰል ሥራውን ስታከናውን ለመመልከት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ተመልክተዋታል። ሼፏ በአውሮፓውያኑ 2023 አራት ቀናት ለሚጠጋ ጊዜ ያለማቋረጥ ለ93 ሰዓታት ከ11 ደቂቃ አድካሚ በሆነ ሁኔታ ምግብ በማብሰል በዓለም ለረጅም ሰዓታት ምግብ ያበሰለች ሼፍ ተብላ ተመዝግባ ነበር።
አሁን በጣም ትልቅ በሆነ ድስት ላበሰለችው ከሩዝ ለሚዘጋጅ ምግብ አራት ሺህ ኪሎ ግራም ሩዝ፣ 500 ካርቶን ቲማቲም እና 600 ኪሎ ግራም ሽንኩርት የተጠቀመች ሲሆን፣ ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀው ድስት ወደ 23 ሺህ የሚጠጋ ሊትር የመያዝ አቅም እንዳለው ተነግሯል።
የምግብ ማብሰሉ ሥራ በርካታ ሰዓታትን የፈጀ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የሚቀርቡ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ከተረጋገጡ በኋላ ጊነስ ዎርልድ ሪከርድ በክብረ ወሰንነት የሚመዘግብበት ውሳኔ ይጠበቃል።
የ28 ዓመቷ ወጣት ሼፍ ሄልዳ ባቺ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ይህንን ግዙፍ ሥራ በማከናወን ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ የአንድ ዓመት የዕቅድ እና ዝግጅት ጊዜ ወስዶባታል።
"እኛ [ናይጄሪያወያን] በአፍሪካ ግዙፍ ነን እናም ምግባችን ጆሎፍ ደግሞ እንደ የአፍሪካውያን ምግብነት ይታወቃል" በማለት በትልቅ ድስት ጆሎፍ ለማብሰል ለምን እንደመረጠች ገልጻለች።
"ጆሎፍ የተሰራበት ትልቁ ድስት በእኛ ስም መመዝገቡ ትርጉም ይሰጣል፣ ለአገራችንም ጥሩ ነገር ነው።" ብላለች ሄልዳ።
ምግቡ የበሰለበት ግዙፉን የብረት ድስት ለመሥራት 300 የሚደርሱ ሠራተኞች እና ሁለት ወራት አስፈልጎታል።
ሄልዳ በትላልቅ ማማሰያዎች እና በበርካታ ረዳቶቿ በመታገዝ ክብረ ወሰን ለመያዝ ያበሰለችው ከሩዝ የተዘጋጀው ባህላዊ ምግብ ከበሰለ በኋላ በስፍራው ለተሰበሰቡ ተመልካቾች ታድሏል።
ጆሎፍ በናይጄሪያ በስፋት የሚበላ ምግብ ሲሆን፣ የበሰለ ሩዝ ከቲማቲም ስጎ ጋር የሚበስል፣ በአብዛኛው ከሥጋ ወይም ከዓሳ ጋር የሚቀርብ ነው።
ሄልዳ ባቺ በአውሮፓውያኑ 2021 በአገሪቱ የተካሄደውን የምግብ ዝግጅት ያሸነፈች ሲሆን በ2023 ደግሞ ለረጅም ሰዓት በማብሰል ክብረ ወሰን ስትይዝ በናይጄሪያ ውስጥ ታዋቂ ለመሆን በቅታለች።















