አሜሪካ አዲሱን የሶሪያ መሪ ለመያዝ መድባ የነበረውን የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሰረዘች

አህመድ አል-ሻራ በደማስቆ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አህመድ አል-ሻራ በደማስቆ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል

አሜሪካ የሶርያውን መሪ አህመድ አል-ሻራ በቁጥጥር ስር ለማዋል ለመያዝ መድባው የነበረውን የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ከከፍተኛ ዲፕሎማቶች እና ከሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) ተወካዮች ጋር ውይይት ካደረገች በኋላ ሰረዘች።

ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባርባራ ሌፍ ከሻራ ጋር የተደረገው ውይይት "በጣም ውጤታማ ነበር" ካሉ በኋላ እርሱም "ለመወያየት ዝግጁ" ሆኗል ብለዋል።

የአሜሪካ ልዑካን ቡድን ዋና ከተማዋ ደማስቆ የደረሰው የኤች ቲ ኤስ ታጣቂዎች የበሽር አል አሳድን መንግሥት ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ካስወገዱ በኋላ ነዉ።

ዋሽንግተን አሁንም አማፂ ቡድኑን በአሸባሪነት እንደ ፈረጀች ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ዲፕሎማቶቹ በአሜሪካ የሚደገፍ "የሽግግር መርሆዎች" ላይ፣ ቀጠናዊ ሁኔታዎች እንዲሁም አይኤስን የመዋጋት አስፈላጊነት ላይ መወያየታቸውን አረጋግጠዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም፣ ባለሥልጣናቱ በአሳድ አገዛዝ ዘመን ስለጠፉት አሜሪካውያን ዜጎች፣ በ2012 በደማስቆ የተጠለፈውን ጋዜጠኛ ኦስቲን ቲስ ፣ እና በ2017 የጠፋውን ሳይኮቴራፒስት ማጅድ ካልማዝ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን አስታውቀዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲ ቃል አቀባይ ቀደም ሲል ሌፍን ይሳተፉበታል የተባለ ጋዜጣዊ መግለጫ በ"ደህንነት ስጋት" ምክንያት መሰረዙን አስታውቋል።

በኋላ ላይ ግን በተሰጠው አጭር መግለጫ ላይ፣ "በጎዳና ላይ የነበረው ከበራ" ለመዘግየቱ መንስኤ መሆኑን በመግለጽ፣ የደህንነት ስጋት የተባለውን አስተባብለዋል።

ጉብኝቱ ከአስር ዓመታት ወዲህ በደማስቆ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ መደበኛ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ነው።

ይህ ጉብኝት በሶሪያ የአሳድ ከስልጣን መወገድን ተከትሎ የታየ ድንገታዊ ለውጥ ሲሆን፣ አዲስ ስልጣን የሚረከበውን መንግሥት የአረብ አገራት ድጋፍ ተጨምሮበት አሜሪካ እና አውሮፓ ተጽዕኖ ለማሳረፍ የወሰዱት እርምጃ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጉብኝቱ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ እንግሊዝ፣ፈረንሳይ እና ጀርመንን ጨምሮ ከሌሎች አገራት የመጡ ልዑካንን ተከትሎ የተካሄደ ነው።

በጉብኝቱ የከፍተኛ ባለስልጣናት ልዑካን ቡድን ባርባራ ሌፍ፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መልዕክተኛ የሆኑት ሮጀር ካርስተንስ እና በቅርብ ምሥራቅ ጉዳዮች ቢሮ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዳንኤል ሩቢንስታይን ተሳትፈውበታል።

ቃል አቀባዩ አክለውም የልዑካን ቡድኑ በሶርያ ከሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች እና ከተለያዩ ማህበረሰቦች አባላት ጋር "ስለ አገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ እና አሜሪካ እንዴት ልትረዳቸው እንደምትችል" መወያየታቸውን ተናግረዋል።

ስብሰባው አሜሪካ ምንም እንኳ ኤችቲኤስን አሁንም በአሸባሪነት እንደ ፈረጀችው ቢሆንም፣ ለመነጋገር ያላትን ዝግጁነት የሚያሳይ ነው የተባለ ሲሆን፣ ሽግግሩ አካታችና የሲቪል አስተዳደር እንዲመሰረት ግፊት ለማድረግም ያለመ ነው።

ዋሽንግተን ቡድኑን ከአሸባሪነት ለመሰረዝ ከማሰቧ በፊት፣ደማስቆ አጥብቃ የምትፈልገውን ማዕቀብ የሌለበት እና የምታደርገውን ሽግግር ቀለል የሚያደርግላትን ሁኔታ፣ የሚጠይቅ ቅድመ ሁኔታዎችን በተሳካ ሁኔታ እያዘጋጀች ነው።

በሌላ በኩል የዩኤስ ሴንትራል ኮማንድ የአይኤስ መሪ አቡ ዩሲፍ እና ሁለት ግብረ አበሮቻቸው በሰሜን ምሥራቅ ሶርያ በዴር አልዙር ግዛት በደረሰ የአየር ጥቃት መገደላቸውን አረጋግጧል።

አርብ እለት በሰጠው መግለጫ የአየር ጥቃቱ የተካሄደው ሐሙስ እለት ሲሆን ቀደም ሲል በአሳድ መንግሥት ቁጥጥር ስር በነበረውአካባቢ ነው ብሏል።

የሴንትራል ኮማንድ አዛዥ ጄኔራል ማይክል ኤሪክ ኩሪላ አሜሪካ አይኤስ "በአሁኑ ጊዜ በሶርያ ያለውን ሁኔታ ተጠቅሞ እንደገና እንዲደራጅ አትፈቅድም" ካሉ በኋላ፣ ቡድኑ በሶርያ በእስር ላይ የሚገኙትን ከ8,000 በላይ የአይኤስ ታጣቂዎችን ለማስፈታት አስቧል ብለዋል።