ማሌዥያ ከ10 ዓመት በፊት ደብዛው የጠፋባትን የመንገደኞች አውሮፕላን እንደ አዲስ ልትፈልግ ነው

የማሌዥያ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ሚስጥራዊ በተባለ ሁኔታ ከአስር ዓመት በፊት ደብዛው የጠፋውን የመንገደኞች አውሮፕላን ፍለጋ እንደገና ለማስጀመር መስማማቱን የማሌዥያ መንግሥት አስታወቀ።

ንብረትነቱ የማሌዥያ አየር መንገድ የሆነው የበረራ ቁጥር ኤምኤች370፣ 239 ሰዎችን አሳፍሮ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2014 ከኩዋላላምፑር ወደ ቤጂንግ ሲጓዝ ነው ደብዛው የጠፋው።

ድንገት የገባበት ያልታወቀው ቦይንግ 777 አውሮፕላን ስብርባሪዎችን ለማግኘት ለዓመታት የተደረገው ውጤት አልተሳካም።

መጨረሻቸውን ያላወቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች እርማቸውን ማውጣት ሳይችሉ በሰቀቀን እና በመከራ ኑሯቸውን ቀጥለዋል።

አርብ ዕለት የማሌዥያ ትራንስፖርት ሚኒስትር አንቶኒ ሎክ አውሮፕላኑን ለመፈለግ መቀመጫውን አሜሪካ ካደረገው ኦሺን ኢንፊኒቲ ከተሰኘ የባህር አሳሽ ድርጅት ጋር የ70 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በመርህ ደረጃ ምክር ቤቱ አጽድቋል ብለዋል።

ክፍያው ቅድመ ሁኔታ እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትሩ ክፍያው የሚፈጸመው ድርጅቱ የአውሮፕላኑን ስብርባሪ ማግኘት ከቻለ ብቻ ነው ብለዋል። በዚህም "ካልተገኘ ክፍያ የለም" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይሄው ኦሺን ኢንፊኒቲ የተሰኘው ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2018 በተመሳሳይ ስምምነት ፍለጋ ቢያደርግም ከሶስት ወራት በኋላ ሳይሳካ ቀርቷል።

ከዚያ ቀደምም 150 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሰፋፊ ውሃዎች ላይ አሰሳ የሚያደርግ ሁለገብ ጥረት ለሁለት ዓመት ያህል ተካሂዶ በአውሮፓውያኑ 2017 ተጠናቋል።

የማሌዥያ መንግሥት የኦሺን ኢንፊኒቲ ስምምነትን በመርህ ደረጃ ቢቀበልም ሚኒስትሩ በተወሰኑ የስምምነቱ ውሎች ላይ ድርድር አሁንም እንደቀጠለ እና በመጪው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ላይ ይጠናቀቃል ብለዋል።

አዲሱ ፍለጋ በደቡባዊ ህንድ ውቅያኖስ ላይ 15 ሺህ ካሬ ኪሎሜትርን የሚሸፍን ይሆናል።

"የአሁኑ ዙር ፍለጋ አዎንታዊ ውጤት እንደሚኖረው ተስፋ እናደርጋለን" ያሉት ሚኒስትሩ የአውሮፕላኑ ስብርባሪዎች መገኘት ቤተሰቦቻቸውን እየፈለጉ ላሉ እርማቸውን እንዲያወጡ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

የበረራ ቁጥር ኤምኤች370 መነሻውን ከማሌዥያ መዲና ኩዋላላምፑር አድርጎ የካቲት 29/ 2006 ዓ.ም ተነሳ።

አውሮፕላኑ ወደ ቻይና ቤጂንግ ለማቅናት በተነሳ ከአንድ ሰዓት ባነሰ ወቅት ከአየር ትራፊክ ቁጥጥር ጋር ያለው ግንኙነት ተቋረጠ። አውሮፕላኑ ከታቀደለት የበረራ መንገድ ማፈንገጡን የራዳር መረጃዎች አሳይተዋል።

መርማሪዎች አውሮፕላኑ በደቡባዊ ህንድ ውቅያኖስ ተከስክሶ እንደሆነ ይስማማሉ፤ ለምን ተከሰከሰሰ ለሚለው ግን ምላሽ የለም።

የአውሮፕላኑ እንደሆኑ የሚታመኑ ስብርባሪዎች ደብዛው ከጠፋ ከዓመታት በኋላ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ተጠርጎ ተገኝቷል።

አውሮፕላኑ በውጭ ጦር ተመትቷል፣ ራሱ ፓይለቱ ነው የከሰከሰው የሚሉ እና በርካታ የሴራ መላምቶች በአውሮፕላኑ መጥፋት ዙሪያ ተሰምተዋል።

በአውሮፕላኑ ደብዛ መጥፋት ዙሪያ በአውሮፓውያኑ 2018 የተደረገ ምርመራ እንዳረጋገጠው የአውሮፕላኑ መቆጣጠሪያዎች ሆን ተብሎ የጉዞውን አቅጣጫውን እንዲስት ተደርገዋል ቢባልም ከጀርባው ማን እንዳለ ድምዳሜ ላይ አልተደረሰም። መርማሪዎች በወቅቱ እንደተናገሩት ምላሹ ሊገኝ የሚችለው ስብርባሪው ከተገኘ ብቻ ነው ብለዋል።