ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ እና የሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ግምቶች

ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ

ስምንተኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ ይከናወናሉ።

ሦስት የሊግ ጨዋታዎችን የተሸነፈው ሊቨርፑል እሑድ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ዩናይትድን ያስተናግዳል።

"ይህ ለአርን ስሎት ትልቅ ጨዋታ ነው" ያለው ቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን "ዩናይትድ በመልሶ ማጥቃት ሊቨርፑልን ለመቅጣት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም" ብሏል።

ይህ የሁለቱ ታላላቅ ቡድኖች ጨዋታ በብዙዎች የሚጠበቅ ነው፤ ማን ያሸንፍ ይሆን?

ሱተን ይህንን ተጠባቂ ጨዋታ ጨምሮ የሳምንቱን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብሮች እንደሚከተለው ገምቷል።

ቅዳሜ

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ቼልሲ

የፎረስት ደጋፊዎች አሰልጣኝ አንጅ ፖስትኮግሉ ገና በሰባተኛ ጨዋታቸው እንዲባረሩ እየጠየቁ ነው።

ቡድኑ በኒውካስል ሲሸነፍ የቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ የተሞከረው ነገር በግልጽ ታይቷል።

ቼልሲ በበኩሉ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ሊቨርፑልን አሸንፏል።

በዚህ ጨዋታ አንጅ አሸንፈው ያለባቸው ጫና ይቀንሳል ብዬ አልጠብቅም።

ግምት፡ 1 - 2

ብራይተን ከ ኒውካስል

ኒውካስል ጠንካራ የአማካይ ክፍል እና የተከላካይ መስመር እንዳለው ከፎረስት ጋር አሳይቷል።

ቡድኑ ዘንድሮ ከሜዳው ውጭ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቋል። ጎል አላስቆጠረም፤ በተመሳሳይ አልተቆጠረበትም።

ብራይተን ጥሩ በማይንቀሳቀስባቸው ጨዋታዎችም አደገኛ መሆኑን አሳይቷል።

ቡድኑ በሜዳው ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።

ግምት፡ 1 - 1

በርንሌይ ከ ሊድስ

በርንሌይ ከሜዳ ውጭ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፏል።

ዘንድሮ ሦስት ነጥብ ያሳኩት ከሰንደርላንድ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ብቻ ነው።

እንደ በርንሌይ ሁሉ ሊድስም ከተጋጣሚዎቹ ጋር ተፎካካሪ መሆኑን አሳይቷል።

ይህ ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት ሲሆን ባለፈው ዓመት በሻምፒዮን ሺፑ ላይ ያለምንም ጎል የተጠናቀቀ ጨዋታ ነበር።

ግምት፡ 0 - 0

ክሪስታል ፓላስ ከበርንመዝ

ክሪስታል ፓላስ ከ በርንመዝ

ይህ ለመገመት የሚከብድ ጨዋታ ነው።

ሁለት በደንብ የተደራጁ እና በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኝ መርሐ ግብር ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ዓመት ያደረጓቸው ጨዋታዎችም ያለጎል ተጠናቀዋል።

በዚህ ጨዋታ አንቶኒ ሴሜንዮ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውን የሚያሸንፉ ይመስለኛል።

ግምት፡ 0 - 1

ማንቸስተር ሲቲ ከ ኤቨርተን

ለኤቨርተን ምርጥ ብቃቱን በማሳየት ላይ የሚገኘው ጃክ ግሪሊሽ በውሰት ከሲቲ በመምጣቱ በዚህ ጨዋታ አይሰለፍም።

ኤቨርተን በመልሶ ማጥቃት መጫወትን እንደሚመርጥ አስባለሁ።

ቡድኑ ዕድሎችን መፍጠር ቢችልም ዋናው ጥያቄ ማንው ኧርሊን ሃላንድን የሚያስቆመው የሚለው ነው።

ግምት፡ 2 - 0

ሰንደርላንድ ከ ዎልቭስ

ዎልቭስት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ቢገኝም ሰንደርላንድ አንዳንድ ተጫዋቾቹን በጉዳት አያሰለፍም።

ቡድኑ በማንቸስተር ዩናይትድ ተበልጦ ተሸንፏል።

ይህ ጨዋታም ቀላል አይሆንላቸውም።

ግምት፡ 1- 1

ፉልሃም ከአርሰናል

ፉልሃም ከ አርሰናል

ፉልሃም ባለፈው ዓመት ከአርሰናል ጋር አቻ ቢለያይም አሁን ግን መድፈኞቹን የሚያቆም ቡድን ያለ አይመስለም።

ማርቲን ኦዴጋርድ በጉዳት ባይሰለፍም ያን ያህል ለውጥ አያመጣም።

ስብስቡ ካለው የቡድን ጥልቀት አንጻር ለሊጉ ዋንጫ እንደሚጫወት አምናለሁ።

ግምት፡ 0 - 2

እሑድ

ቶተንሃም ከ አስቶን ቪላ

አስቶን ቪላ አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም ያለፉትን አራት ጨዋታዎች አሸንፏል።

እስካሁን ቡድኑ ያለው አቋም ያላሳመነኝ ከመሆኑ አንጻር ይህ ለኡናይ ኤምሬ ቡድን ጥሩ መፈተኛ ነው።

ቶተንሃም ብዙ ጎሎችን አስቆጥሮ የሚያሽንፍ ቡድን ባይሆንም ቡድኑ ሚዛኑን የጠበቀ ነው።

ግምት፡ 2 - 1

ሊቨርፑል ከ ማንቸስተር ዩናይትድ

ማንቸስተር ዩናይትድ ብዙ ተስፋ የሚያደርግባቸው ምክንያቶች አሉ።

ሊቨርፑል በተከላካይ ክፍል በተለይም በመስመር በኩል ክፍተቶች ስላሉበት ለዩናይትድ ይመቸዋል።

የሩበን አሞሪም ቡድን አንፊልድ ላይ አንድ ነገር ሊያገኝ እንደሚችል ይሰማኛል።

ነገር ግን አቻ ይወጣሉ ብዬ አልገምትም።

ግምት፡ 2 - 1

ሰኞ

ዌስት ሃም ከ ብሬንትፎርድ

ዌስት ሃም በሜዳው ብሬንትፎርድ ደግሞ ከሜዳው ውጭ ሦስት ጨዋታዎችን ተሸንፈዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ይመርጣሉ።

በዚህ ምክንያትን በጨዋታው በርካታ ዕድሎች የሚፈጠሩ አይመስልም።

ግምት፡ 1 - 0