የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ለሩሲያው ቫግነር መስራች ፕሪጎዢን ሃውልት አቆመች

የቫግነሩ መሪ ፕሪጎዢን እንዲሁም ቀኝ እጁ የሚባለው ዲሚትሩ አትኪን የመታሰቢያ ሃውልቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ባለፈው ዓመት ህይወቱ ያለፈው የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር መስራች የቭጌኒ ፕሪጎዢን የመታሰቢያ ሃውልት በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ይፋ ሆነ።

በባለፈው ዓመት በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡት የቫግነሩ መሪ ፕሪጎዢን እንዲሁም ቀኝ እጁ የሚባለው ዲሚትሩ አትኪን የመታሰቢያ ሃውልቶች በመዲናዋ ባንጊ ውስጥ ነው የቆሙት።

በሃውልቶቹ ላይ ፕሪጎዢን የጥይት መከላከያ እና የመልዕክት ማስተላለፊያ (ዋኪ ቶኪ) የያዘ ሲሆን ዲሚትሩ ደግሞ ኤኬ47 ጠመንጃ ይዞ ይታያል።

በዩክሬን፣ በሶሪያ እና በምዕራብ አፍሪካ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን በማሰማራት የእንቅስቃሴ አድማሱን ያስፋፋው ቫግነር ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ሰፍረው ይገኛሉ።

ታጣቂዎቹ የመጡት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፎውስቲን አርቻንድ ቱዋዴራ የአማጺ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት የእርዳታ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው።

ቡድኑ በአገሪቱ ውስጥ የወርቅ እና የአልማዝ ማዕድን ቁፋሮዎችን ለማካሄድ ውሎችን መውሰዳቸው ተዘግቧል።

ቡድኑ በሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ቢገኙም በዋነኝነት በመካከለኛው አፍሪካን ሪፐብሊክ ይገኛሉ።

ሃውልቱ በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፐብሊክ እና በሩሲያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት አካል ነው ሲል የአገሪቱ ብሔራዊ ፖሊስ በመግለጫው አትቷል።

በሃውልቱ የምረቃ ስነ ስርዓት ወቅት የመከላከያ ሚኒስትሩ ራሜው ክላውድ ቢሬው እና ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ አጋማሽ ላይ ፕሪጎዢንን የጫነ የግል ጄት ከሞስኮ በስተሰሜን ተከስክሶ እሱ እና ሌሎች በርካታ የቫግነር አመራሮች መገደላቸው ይታወሳል።

ከግድያው በስተጀርባ የክሬምሊን ባለሥልጣናት አሉበት ቢባልም ይህንን አስተባብለዋል። አመራሮቹ የተገደሉት በሩሲያ ፕሬዚዳንት ላይ ለሰዓታት የቆየ አመጽ ባስነሱ ከሁለት ወራት በኋላ ነው። ከአመራሩ ግድያ በኋላ ታጣቂዎቹ በሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ አፍሪካን ኮርፕስ (የአፍሪካ ጦር ክፍል) የሚል ስያሜ ቢሰጣቸው በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ አሁንም በቫግነር ስም ይንቀሳቀሳሉ። ታጣቂዎቹ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ መገኘታቸውን በተመለከተ ፕሬዚዳንቱ አጥብቀው የሚደግፉት ነው።

“80% የሚሆነው ግዛታችን በአማጺያን ኃይሎች የተያዘ ነበር። ዛሬ ለዚህ ትብብር ምስጋና ይግባው እና እነዚህ አሃዞች ሙሉ በሙሉ ተቀልብሰዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።

የፕሪጎዢን ሃውልት ከመመረቁ በፊትም ቢሆን ሩሲያ በአገሪቱ ውስጥ እየተጫወተችው ያለውን ሚና የሚያመለክት ሃውልት በመዲናዋ ባንጉይ ቆሟል። ይህም ሃውልት የሩሲያ ወታደሮች ሴት እና ልጆቿን ሲከላከሉ የሚያሳይ ነው።