'ቅብብሎሽ' ትላንት እና ዛሬን ማያያዣ ድልድይ . . .

የዘመናዊ ስነ ጥበብ ቤተ መዘክር ገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል መግቢያ

የፎቶው ባለመብት, Netsanet Gebremichael

የዘመናዊ ሥነ ጥበብ ቤተ መዘክር ገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል ለሁለት ወራት የቆየ ዐውደ ርዕይ፣ ሕዝባዊ ዲስኩር (public lecture) እና ፊልም ማሳየት ሲካሄድበት ነበር።

ማዕከሉ ለዐውደ ርዕዮች እና ለጥበብ ኹነቶች አዲስ አይደለም። በወርሃ ጥቅምት እና ኅዳር የተካሄደው ኹነት ግን በይነ ትውልድ እና በይነ ዲስፕሊናዊ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።

ለዚያም ነው "ቅብብሎሽ" የሚል ርዕስ የተሰጠው።

ቅብብሎሽ ከጥቅምት መጀመሪያ እስከ ኅዳር መጨረሻ ለሁለት ወራት የዘለቀ የተከታታይ ኹነቶች የወል መጠሪያ ነው። ቅብብሎሽ በተለያዩ የሙያ መስኮች፣ ትውልዶች እና ዲስፕሊኖች መካከል የሃሳብ ልውውጦች የሚካሄዱበት መድረክ ነው።

ለሁለት ወራት የቆየው ፕሮግራም ዋና ጉዳይ የካሴት ሽፋኖች ዐውደ ርዕይ መሆኑን የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ዶ/ር ነጻነት ገብረ ሚካኤል ለቢቢሲ ተናግራለች።

'ነበር' የተሰኘው የሙዚቃ ካሴት ሽፋኖች ዐውደ ርዕይ የተዘጋጀው በአንድምታ መጽሔት ነው።

ዐውደ ርዕዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በ'ዘ ቬኑ ዌር ሀውስ' ሲሆን በመቀጠል ደግሞ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ለዕይታ በቅቷል።

'ነበር' የኢትዮጵያ የክር ሙዚቃ ዘመንን ለመዘከር የተዘጋጀ የካሴት ሽፋን እና የድምጽ ቅንብር ዐውደ ርዕይ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዐውደ ርዕዩ 23 ካሴቶችን እና 26 ዘፋኞችን ካሴቱ ላይ ካቀረቧቸው ሥራዎቻቸው ናሙና ጋር በማቀነባበር በምሥል እና በድምጽ ይዘክሯል።

በእያንዳንዱ የካሴት ሽፋን ላይ በተቀመጠ የ'ኪውአር ኮድ' በኩል የዐውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች የዘፋኞቹን ሙዚቃ እና የሙያ ጉዞ ለመስማት ያስችላል።

የክር ዘመን ሙዚቃን ለስፖቲፋይ ዘመን አድማጮች ማሰማት ማለት ነው።

በዐውደ ርዕዩ የተሳተፈችው ዶ/ር ነጻነት "የኪውአር ኮዱ ለተማሪዎቹ ምን ያህል ቀላል መሆኑን አየሁ" ትላለች። "ታሪካዊ የሆኑ ክስተቶችን ለሌላ ትውልድ በጣም ቀላል በሆነ መንገድ እንዴት ማቀበል እንደሚቻል አስተዋልኩ እና እዚህኛው [ቅብብሎሽ] መድረክ ላይ ማምጣት ፈለግኩኝ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ለምሳሌ 60ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ከሸክላ ሙዚቃ ወደ ክር ሙዚቃ እናልፋለን" የምትለው ዶ/ር ነጻነት፤ "በሙዚቃ በኩል ጊዜ አለ ማለት ነው፤ ልክ አሁን በፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጊዜ እንዳለን ሁሉ በሙዚቃ በኩልም ጊዜ አለ። ታሪክን በእንደዚህ ዓይነት ቅደም ተከተል ማየት ይቻላል" ስትል ታብራራለች።

የማኅበራዊ ታሪክ ባለሙያዋ ዶ/ር ነጻነት፤ "ታሪክ የለውጥ እና የቀጣይነት ጉዳይ ነው" ትላለች።

"በሙዚቃ እና ሥነ ሥዕል ብናይ ታሪካችን ምን ይመስላል? በሥነ ሥዕል ውስጥ ያለ የጊዜ አደራደር ለውጥን እና ቀጣይነትን እንዴት ይመዘግባል የሚለውን ለማየት ሞክረናል" ስትል ዶ/ር ነጻነት ታክላለች።

ይህን ተክትሎ የቅብብሎሽ መድረክ በሙዚቃ እና በሥዕል ላይ ያተኮሩ የፊልም ማሳየት እና ሕዝባዊ ዲስኩሮች ተካትተውበት ለሁለት ወራት ተካሂዷል።

ይህ ዐውደ ርዕይ እና ዐውደ ጥናት ሙከራ መሆኑን ዶ/ር ነጻነት ትናገራለች።

"ካሴት ሽፋኑ በኩል የመጣውን የዕይታ እና ሙዚቃዊ የታሪክ ተዋረድ በዲስኩር እና በፊልም ደግሞ ብንደግፈው ምን ይመስላል የሚል ሙከራ ነው" ስትል ትገልጻለች።

"የሙዚቃው እና የሥዕል መዛግብት ቢኖሩም ሁሉም ላያውቀው ይችላል" የምትለው ዶ/ር ነጻነት፤ "ለሁሉ ሰው በሚገባ መልኩ በሕይወት ያሉ ሠዓሊያን እና ሙዚቀኞች ራሳቸው ያለፉበት ያንን ጊዜ እንዲተርኩት አድርገናል። ቅርጹ ሆን ተብሎ የአፈ ታሪክ (Oral History) እንዲሆን ተደርጓል" ስትል ስለ ሕዝባዊ ዲስኩሩ ታብራራለች።

ተማሪዎች የኪው አር ኮድ ተጠቅመው የክር ሙዚቃ ሲያዳምጡ

የፎቶው ባለመብት, Netsanet Gebremichael

የምስሉ መግለጫ, በእያንዳንዱ የካሴት ሽፋን ላይ በተቀመጠ የ'ኪው አር ኮድ' በኩል የዐውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች የዘፋኞቹን ሙዚቃ እና የሙያ ጉዞ ለመስማት ያስችላል

ለሁለት ወራት በቆየው ኹነት በሙዚቃ እና በሥዕል ላይ ያተኮሩ ስድሰት ሕዝባዊ ዲስኩሮች ተደርገዋል። በእነዚህ ዲስኩሮች የባንድ መሥራቾች፣ የአርት ጋለሪ ባለቤቶች፣ ሙዚቀኞች እና ሠዓሊያን ስለ ሙያዊ ሕይወታቸው አውግተዋል።

ከእነዚህ ዲስኩሮች መካከል በዐይነ ስውራን የተመሠረተው የሬንቦ ባንድ አባላት ዘመድ ገብረአምላክ እና አብዱቄ ከፈኒ የሰጡት ዲስኩር አንዱ ነው።

"ብዙ ያልተወከለውን የማኅበረሰብ ክፍል ግን ደግሞ በዚያን ጊዜ ሙዚቃው ውስጥ የነበሩትን ለማምጣት ተሞክሯል" የምትለው ዶ/ር ነጻነት የሬንቦ ባንድ አባላት "ዐይነ ሥውራን ስለሆኑ አይደለም የመጡት በወቅቱ ስለነበራቸው ሥራ ነው" ስትል ትናገራለች።

ከዚህ በተጨማሪም በአርቲስቶች መካከል የተደረገ ወግ ነበር። የአስኒ ጋለሪ መሥራች የሆነችው ቆንጂት ስዩም ከኤልሳቤጥ ሃብተወልድ ጋር ስለ ሥዕል፣ ስፍራ እና ጥበብ አውርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ቅብብሎሽን ማዘጋጀቱ ላይ ሚና ያለው ሠዓሊ እና ቀራጺ በቀለ መኮነን በደርግ ዘመነ መንግሥት ስለ ዕይታ ጥበብ በኢትዮጵያ ከአርቲስት ጌታ መኮንን ጋር አውግተዋል።

ዶ/ር ነጻነት "'ቅብብሎሽ' ይበልጥ ትኩረት ያደረግነው በይነ ዲስፕሊን እና በይነ ትውልድ ላይ ነው" ትላለች።

ሁለት ወራት በቆየው መርሃ ግብር አብዛኛው ተሳታፊዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣቶች ነበሩ።

"'ቅብብሎሽ' የሴቶችንም ሚና እና አበርክቶ እንዲያዩ አድርጓቸዋል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

በ'ቅብብሎሽ' ለዕይታ ከቀረቡት አምስት ፊልሞች መካከል ሦስቱ በኒና ሲሞን፣ በማሪያ ማኬባ እና በአስናቀች ወርቁ ሕይወት እና ሥራዎች ላይ ያተኮሩ ነበሩ።

ዶ/ር ነጻነት "ማሪያ ማኬባን፣ ኒና ሲሞን እና አስኒን ያደረግነው በግድ ሴቶች ይሁኑ ብለን አይደለም። ግን መኖር ነበረባቸው፤ በዚያ ጊዜ እዚያ ሙያ ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው" ስትል ስለ ፊልሞቹ ገልጻለች።

"ማሪያ ማኬባ የነጻነት ታጋይ ነበረች፣ ሙዚቀኛ እና አሰላሳይም ነበረች። አስናቀች ወርቁ የጥበብ መድረኩ ላይ ትልቅ ስፍራ ነበራት፣ ለሴቶች ነጻነት ታገለች የምትባል ዓይነት ናት" ስትል ታክላለች።

ዶ/ር ነጻነት ፊልሞቹ የተመረጡበት ሁኔታን ስታብራራ "በሆነ ዘመን ውስጥ ስለነበረ ሥነ ጥበብ እና ሙዚቃ ስናበጥረው የነበሩትን ነው ያነሳነው። የነበሩትን ማንሳት ምንም ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ አልነበረም፤ ግን ሆን ብሎ መሥራት ይፈልጋል። የነበረውን ነገር አልተውን ይሆናል እንጂ ሆን ብለን ፈልፍለን ያወጣነው ነገር ያለ አይመስለኝም" ትላለች።

ዶ/ር ነጻነት ገብረሚካኤል በ'ቅብብሎሽ' ኹነት ላይ ንግግር እያደረገች

የፎቶው ባለመብት, Netsanet Gebremichael

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ነጻነት ገብረሚካኤል በ'ቅብብሎሽ' ኹነት ላይ ንግግር እያደረገች

በመጪው የካቲት በተመሳሳይ ይዘት በሙያቸው 20 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከሠሩ ሰዎች ጋር ሕዝባዊ ዲስኩር ለማድረግ መታቀዱን ዶ/ር ነጻነት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ስለመጪው መርሃ ግብር ስታወራ፤ "ባለሙያዎቹ ዘንድ የትውልድ ዕውቀቶች አሉ፤ ያንን ዕውቀት ከተለያየ ሙያ አንጻር በሙያው ስላለፉበት መንገድ ይተርኩልናል" ትላለች።

ከዚህ በተጨመሪም "አንዱ ስለዚያ ዘመን የማናውቃቸውን እውነታዎችን እና ልማዶችን ይዞ ይመጣል፣ ሁለተኛው ደግሞ ለሁሉም ሰው በሚገባ መንገድ ስለዚያ ሙያ ያስተምራል። ዋናው ነገር ግን የበይነ ትውልዶችን እውቀት ይሰንዳል። ለአሁኑ ትውልድ ያስተላልፋል። ያለፈውን ነገር የሚመጣው ትውልድ እያየው ይሄዳል ማለት ነው" ስትል የመጪውን ኹነት ዓላማ አብራርታለች።

'ቅብብሎሽ' ከሦስት ዓመታት በፊትም በተለየ ጭብጥ እና ርዕስ ተካሂዶ ነበር።

ከሦስት ዓመታት በፊት የተካሄደው መድረክ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሴቶች ጥያቄ ላይ ያተኮረ የበይነ ትውልድ ውይይት ነው።

ዶ/ር ነጻነት ከሦስት ዓመት በፊት የነበረው መድረክ "በጨዋታ መልክ ነው የመጣው" ትላለች።

"ሦስት ዓመታትን ከፈጀ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጊዜ የሴቶች ጥያቄ እንደ ብሔር እና መሬት ጥያቄዎች በሥርዓተ መንግሥቱም በአካዳሚያዊ ውይይቱም በኩል ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም በሚል መነሻ ወስዶ የመዛግብት ጥናት" ማድረጓን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከሦስት ዓመቱ ጥናት መጠናቀቅ በኋላ ነው ዐውደ ጥናቱ እና ዐውደ ርዕዩ የተካሄደው። በዐውደ ጥናቱ ላይ ሁለት ትውልዶች መካከል ውይይት ተደርጓል። ሁለቱም ትውልዶች ከትላንት እስከ ዛሬ የሴቶች ጥያቄ ላይ አውግተዋል።

ታደለች ኃይለሚካኤል፣ ነጻነት መንግሥቱ እና አስቴር ዘውዴ በተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት የነበረውን የሴቶችን ጥያቄ አቅርበዋል። በፍቃዱ ኃይሉ እና ሩት ይትባረክ ደግሞ የዘመናቸውን የሴቶች ጥያቄ አቅርበዋል።

ይህም የበይነ ትውልዶች ንግግር መድረኩ 'ቅብብሎሽ' የሚለውን ስም እንዲይዝ እንዳደረገው ዶ/ር ነጻነት ትገልጻለች።

"ከዐውደ ጥናቱ በኋላ የተካሄደው ዐውደ ርዕይ የሴቶች ጥያቄ ላይ የተደረገው የመዛግብት ጥናት ለዕይታ ቀርቦ ነበር።

ዐውደ ርዕዩ የግለሰቦችን ፎቶግራፎች ጨምሮ፣ ጽሑፎችን እና መጽሐፎችን፣ ቃለ መጠይቆች፣ ዘጋቢ ፊልሞች የተካተቱበት የመልቲሚዲያ መድረክ ነበር።

ዶ/ር ነጻነት ከአርቲስት ሄለን ዘሩ ጋር ባዘጋጀችው አውደ ርዕይ ከአፈ ታሪክ፣ በወቅቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ከነበሩ ሰዎች ጋር ከተደረጉ ቃለ መጠይቆች በተማሪዎችን ንቅናቄ ወቅት የሴቶችን ተሳትፎ ይፈትሻል።

ከሦስት ዓመት በፊት የነበረው ዐውደ ርዕይ፤ የሴቶችን ንቃት ህሊና እና የትግሉን ዕድገት እና መለወጥ በጊዜ ቅደም ተከተል ያሳያል።

የመጀመሪያው ዐውደ ርዕይ ክፍል ከኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት የተሰበሰቡ ማኅደሮችን እና በአፈ ታሪክ ባለሙያዎች የተቀረፀ የድምፅ ቅጂ ያያዘ ነበር።

ሁለተኛው ክፍል በሴቶች እና በወንዶች መካከል በሴቶች ጉዳይ እና በንቅናቄው ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ የተለያዩ የተማሪዎች ህትመቶች ላይ የተደረጉ ክርክሮች እና ሙግቶችን የያዘ ነው።

ሦስተኛው ክፍል ፎቶግራፎች እና የደንብ ልብስ እንዲሁም በዚያ ወቅት የታተሙ መጽሔቶችን ጨምሮ የግል ማስታወሻዎችን፤ አራተኛው ክፍል ደግሞ የሴቶችን ሕይወት እና ተጋድሎ ለማስታወስ በድጋሚ የታተሙ የመጽሔት ሽፋኖች እና ጽሑፎች የሚታዩበት የመታሰቢያ ክፍል ነው።