ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በድንገት በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ለሰዓታት የቆየ ጉብኝት አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Zelensky Official/Telegram
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ በመገኘት ድንገተኛ ጉብኝት አደረጉ።
ፕሬዝዳንት ባይደን ዩክሬን በሩሲያ ወረራ ከተፈጸመባት በኋላ አገሪቷን ሲጎበኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ወደ ዩክሬን መዲና ከመጓዛቸው በፊት ከጎረቤት አገር ፖላንድ ፕሬዝዳንት አንድሬዝ ዱዳ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረው ነበር።
ዛሬ ሰኞ ከንጋት ጀምሮ በኪዬቭ ማንነቱ ያልተገለጸ ትልቅ እንግዳ ሲጠበቅ የቆየ ሲሆን፣ ተጠባቂው ፕሬዝዳንት ባይደን መሆናቸው በኋላ ላይ ተገልጿል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ወረራ ከጀመረች አንስቶ በርካታ የውጭ አገር መሪዎች ወደ ኪዬቭ በማቅናት ለአገሪቱ አጋርነታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የፕሬዝዳንት ባይደን ጉብኝት ግን ምዕራባውያኑ ለዩክሬን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለዩክሬን ፕሬዝዳንት እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ይህም ከምዕራባውያኑ ከፍተኛ ውግዘት እና ጫና እየደረሰባት ላለችው እዚያው ጦርነቱ ወደ ሚካሄድበት ቀረብ ብለው ያስተላለፉት ጠንካራ መልዕክት ነው።
ወደ ኪዬቭ ካቀኑ መሪዎች መካከል የአሁኑ እና የቀድሞ የቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትሮች ሪሺ ሱናክ እና ቦሪስ ጆንሰን፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሽልዝ ይገኙበታል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኪዬቭ በነበራቸው ቆይታ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ቀደም ብሎበይፋ ያላተገለጸውን ድንገተኛ ጉብኝታቸውን ለሰዓታት በጦርነት ውስጥ ባለችው ዩክሬን አድርገው ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ መውጣታቸው ተዘግቧል።
የፕሬዝዳንት ባይደንን በኪዬቭ መገኘት ካረጋገጡት የአገሪቱ ባለሥልጣናት መካከል አንዷ የሆኑት ኤሲአ ቫስይሎንኮ ለፕሬዝዳንቱ አቀባበል እየተደረገ በመዲናዋ የአየር ጥቃት ስጋት የማስጠንቀቂያ ደውል ድምጽ ተሰምቶ እንደነበረ ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባሏ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገች ላለችው ውጊያ አሜሪካ ኤፍ-16 ተዋጊ ጀቶችን እንድትሰጣት ልትጠይቅ እንምትችል ጨምረው ገልጸዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ በተለይ አሜሪካ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ድጋፎችን ስታደርግ ቆይታለች።
በቅርቡ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በአሜሪካ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በአገሪቱ ምክር ቤት ውስጥ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።












