በመረጃ መዝባሪዎች የተዘረፉ ወታደራዊ ሰነዶች ለሽያጭ መቅረባቸው ኔቶ ምርመራ እንዲጀምር አደረገ

የጦር መሣሪያ

የፎቶው ባለመብት, MBDA MISSILE SYSTEMS

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) በመረጃ ሰርሳሪዎች ተመዝብረው በበይነ መረብ ለሽያጭ የቀረቡ ወታደራዊ ሰነዶችን ጉዳይ እየመረመረ ይገኛል።

ከተሰረቁት ሰነዶች መካከል የኔቶ አጋሮች በዩክሬን የሚጠቀሙባቸውን የጦር መሣሪያዎች የሚጠቁመው ይገኝበታል።

የመረጃ ሰርሳሪው ቡድን ወታደራዊ ሰነዶች መስረቃቸውን ተከትሎ ኔቶ ዝርፊያው ሊያሳድርበት የሚችለውን ተጽዕኖ እየመረመረ ይገኛል።

መረጃ ሰርሳሪዎቹ ከግዙፍ የአውሮፓ መሲኤሎችን ጨምሮ የተለያዩ መሣሪያዎች አምራች ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ሰርቀው ለሽያጭ አቅርበዋል።

ኤምቢዲኤ ሚሳኤል ሲስተምስ የተባለው የጦር መሣሪያ አምራች ድርጅር መረጃዎቹ እንደተሰረቁ አምኗል።

ነገር ግን ከሰነዶቹ መካከል ምስጢራዊ የሆኑት የዚህ ድርጅት እንዳልሆኑ አሳውቋል።

ድርጅቱ ዋና መቀመጫው ፈረንሳይ ሲሆን፣ ሰነዶቹ የተሰረቁት ከጣልያን እንደሆነና ምርመራ እንደተከፈተ ገልጿል።

የኔቶ ቃል አቀባይ “ከኤምቢዲኤ ተሰረቁ የተባሉትን ሰነዶች እየመረመርን ነው። የኔቶ ኔትወርኮች ላይ ጥቃት ስለመሰንዘሩ የሚጠቁም ነገር አላገኘንም” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተሰረቁት ሰነዶች በዋናነት በሩሲያ ስውር የበይነ መረብ ገጾች በ15 ቢትኮይን (ወደ 18 ሺህ ዩሮ ገደማ) ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን፣ የመረጃው መጠን 80 ጊጋባይት ይጠጋል።

እስካሁን ቢያንስ አንድ ሰው መረጃውን መግዛቱ ተገልጿል።

መረጃ ሰርሳሪዎቹ ያወጡት ማስታወቂያ “በምስጢር የተያዙ ወታደራዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ ስለሚሠሩ ሠራተኞች መረጃ አግኝተናል። ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ስለተደረሱ ስምምነቶች እንዲሁም የዲዛይን ዓይነቶች ምሥልና ተንቀሳቃሽ ምሥልም አግኝተናል” ይላል።

ከሰነዶቹ መካከል 50 ሜጋባይት የሚሆኑትን እንደ ማሳያ በነጻ ለሸማቾች አቅርበዋል።

ቢቢሲ ይህንን ሰነድ የተመለከተ ሲሆን፣ ‘ምስጢራዊ የኔቶ ሰነድ’፣ ‘ለኔቶ ብቻ የተፈቀደ’ የሚሉ ይገኙበታል።

ኔቶ አንድ መረጃ ለማን ይነገራል፣ መረጃው ቢሾልክ በድርጅቱ ላይ ምን ያስከትላል የሚለውን ባገናዘበ ሁኔታ አምስት የሰነድ ምስጢራዊነት ደረጃዎች አሉት።

ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን ካላጣራቸው ሰነዶች አንዱ “በ2020 አሜሪካ በኢስቶንያ ያደረገችው ወታደራዊ ተልዕኮ” የሚለው ይገኝበታል።

የስልክ ልውውጦች፣ የስም ዝርዝር እና የበይነ መረብ ካርታ (ጂፒኤስ) ቁልፍ ቁጥሮች ይዟል።

ኔቶ እንዳለው፣ በኔቶ ውስጥ ብቻ በምስጢር እንዲያዙ የሚፈልጓቸው መረጃዎች ሾልከው መውጣት የለባቸውም።

በሰነዶቹ ውስጥ ከሚገኘው መረጃ አንዱ ስለ አንድ ተወንጫፊ ሚሳኤል መረጃ የሚሰጥ ሲሆን፣ መሣሪያው የት ይቀመጣል የሚለውን ጨምሮ የተለያዩ ዝርዝሮች አሉት።

መረጃው የተመዘበረበት ኤምቢዲኤ እንዳለው፣ ተሰረቁ ከተባሉት ሰነዶች የተወሰኑት “ያን ያህል በከባድ ምስጢር እንዲያዙ የሚጠበቅ አይደሉም።”

ነገር ግን የተወሰኑ ሰነዶች በድርጅቱ ሠራተኞች ብቻ የተያዙ እንደሆኑ ገልጿል።

ድርጅቱ የተመሠረተው በ2001 ሲሆን፣ በፈረንሳይ፣ በጣልያን እና በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚገኙ ሚሳኤል አምራቾች በጥምረት የጀመሩት ነው።

13 ሺህ ሠራተኞች አሉት።

ለኤርባስ፣ ቢኤኢ ሲስተምስ እና ሊዮናርዶ ተቋሞች ጋር በጥምረት ይሠራል።

ባለፈው ዓመት 3.5 ቢሊዮን ዩሮ እንዳተረፈ አስታውቋል።

የዩናየትድ ኪንግደም፣ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ኔቶ ጦር ኃይሎች የድርጅቱ ዋነኛ የጦርመ መሣሪያ ገዢዎቹ ናቸው።