ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሱዳኑ መሪ ጄኔራል አል ቡርሐን ጋር ተወያዩ

የፎቶው ባለመብት, pm office
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳኑ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ጋር ኬንያ ውስጥ ተገናኝተው ተወያዩ።
ሁለቱ መሪዎች ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ በሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በሄዱበት ነው የተገናኙት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ከጄኔራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን ጋር ባደረግኩት ውይይት ሁለቱ አገራት በሰላማዊ መንገድ ለመስራት በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል” በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
አክለውም “ሁለቱን አገራት የሚያስተሳስሩን ጉዳዮች ከሚከፋፍለን ይበልጣል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱም አገራት ያላቸውን ልዩነት በሰላማዊ መንገዶች ለመፍታት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።
በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት እየተወዛገቡ ያሉት ኢትዮጵያና ሱዳን፣ በአባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው የሕዳሴው ግድብ ምክንያት ግንኙነታቸው ሻክሮ ቆይቷል።
ከአንድ ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ሠራዊት ወታደሮቼን ገድሎብኛል ብላ ክስ ያቀረበችው ሱዳን፣ ከድንበር ባሻገር ያሉ የኢትዮጵያ ይዞታዎችን በከባድ መሳሪያ መደብደቧ ይታወሳል።
አልፋሽካ ተብሎ የሚጠራውን እና በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ስር የነበረውን ሰፊ ለም የእርሻ አካባቢውን የሱዳን ኃይሎች ከአንድ ዓመት በፊት በኃይል ከተቆጣጠሩ በኋላ በድንበር አካባቢ ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን የተካረረ ውዝግብን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሱዳን ሽግግር ሉዐላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ዛሬ ናይሮቢ ላይ ለኢጋድ ስብሰባ ወቅት መገናኘታቸው ተገልጿል።
የሁለቱ አገራት መሪዎች በተገናኙበት ጊዜ የሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮችን አንስተው መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጽህፈት ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስፍሯል።
ኬንያ ውስጥ ዛሬ የሚካሄደው 39ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ልዩ የመሪዎች ጉባኤ የአባል አገራቱ “የጋራ ጉዳዮች” ላይ እንደሚወያይ ተገልጿል።
ይህ የኢጋድ ስብሰባ ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ውዝግብ ምክንያት ወደ ግልጽ ግጭት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ባንዣበበበት ወቅት ነው።
በዚህም ሳቢያ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት ወደ ሱዳን አቅንተው ከጄኔራል አል ቡርሐን ጋር በመነጋገር፣ ሁለቱ አገራት ለድንበር ውዝግቡ ዘላቂ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ልዩ ጉባኤው “በጣም አስፈላጊና ሁሉም የአባል አገራት መሪዎች የሚሳተፉበት እንደሆነ’ ዋና ፀሐፊው ቀድመው ገልጸዋል።
ባለፈው ጥቅምት ሱዳን ውስጥ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ጄኔራል አል ቡርሐን ያጋጠማቸውን ተከታታይ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በምርጫ ለሚመሰረት መንግሥት ሥልጣን ለማስረከብ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል።












