የፍልስጤም ደጋፊዎች የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የምረቃ ስነ ስርአትን እንዳያስተጓጉሉ ተከለከሉ

ተቃዋሚዎች በካምብሪጅ ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ አካሂደዋል

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የፍልስጤም ደጋፊዎች የዩናይትድ ኪንግደሙን የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ስነ ስርዓትን እንዳያስተጓጉሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከለከለ።

ዳኛ ፎርድሃም ዩኒቨርሲቲውን ወክለው የቆሙ ጠበቆች ያቀረቡትን ማመልከቻ ተከትሎ ቅዳሜ የሚካሄደውን ሥነ ሥርዓት በሚመለከት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚፈጠረውን መስተጓጎልን በተመለከተ የረዥም ጊዜ ስጋቶችን ቢያነሱም ዳኛው ሰፋ ያለ ክልከላ እንዲጥሉ ማሳመን አልቻሉም።

የዩኒቨርሲቲውን እርምጃ በዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የተፈፀመ "አሳፋሪ" ሲል አንድ ማህበር አውግዞታል።

እአአ በ2023 መገባደጃ ላይ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ በካምብሪጅ የተቃውሞ ካምፖች ተቋቁመዋል።

የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናቸውን ዩኒቨርስቲዎች እንዲያቆሙ እየጠየቁ ይገኛሉ።

እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።

ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከእስራኤል መንግሥት ጋር ከጦር መሣሪያ ጋር በተያያዘ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት ለመገምገም ቀደም ሲል በተደረጉ ስምምነቶች መሠረት እያከበረ አይደለም ሲሉ ተቃዋሚዎቹ ተናግረዋል።

ተቃዋሚዎቹ በርካታ የምርቃት ስነ ስርዓቶችን እንዴት እንዳስተጓጉሉ ጠበቆቹ ለዳኛው ፎርድሃም ገልጸዋል።

እስከ 2030 ድረስ የሚቆይ እና በካምብሪጅ ውስጥ በሚገኙ አራት የዩኒቨርሲቲ ካምፓሶችን የሚሸፍን ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀው ነበር።

ትዕዛዙን የሚተላለፍ ማንኛውም ሰው ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት እና ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ባለማክበር ሊጠየቅ ይችላል

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የዩኒቨርሲቲውን የሕግ ቡድን የመሩት ባሪስተር ያስር ቫንደርማን እንዳሉት አንዳንድ "ተከሳሾች" በጦርነቱ ላይ "ጠንካራ እና ቁርጠኛ" አመለካከትን እንዲሁም "በደንብ የተደራጀ" ቡድን ፈጥረዋል።

ቫንደርማን በየዓመቱ የሚገመገም እና ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የክልከላ ትዕዛዝ ጠይቀዋል። የጋዛ ግጭት "የረጅም ጊዜ" እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ያለው የጊዜ ገደብ ምክንያታዊ ነው ብለውም ተከራክረዋል።

ዳኛው ግን ምንም ዓይነት "የመጨረሻ" ትዕዛዝ ወይም ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ማንኛውንም ትዕዛዝ ለመስጠት ዝግጁ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

በዚህም ቅዳሜ ዕለት በሴኔት ሃውስ በትሪኒቲ ጎዳና ላይ በሚካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ዳኛው እስከ ቅዳሜ ድረስ የሚቆይ የተወሰነ ትዕዛዝ ብቻ መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል። ጉዳዩን በቅርቡ በድጋሚ ለማየት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

በለንደን በተካሄደው ችሎት ላይ አንድም የፍልስጤም ተቃዋሚ ያልነበረ ሲሆን በጠበቃዎችም አልተወከሉም። ዩኒቨርሲቲው ክሱን የመሰረተው "ስማቸው ባልተጠቀሱ" ተማሪዎች ላይ ክስ ነው።

አንድ ጠበቃ ከችሎቱ በኋላ እንዳሉት እገዳው ከአርብ እስከ ቅዳሜ ድረስ እንደሚቆይ እና ከዩኒቨርሲቲ ፈቃድ ውጭ ማንም ሰው ወደ ሴኔት ሃውስ ወይም ወደ ሴኔት ሃውስ ያርድ እንዳይገባ ይከለክላል ብለዋል።

ጠበቆች እንዳሉት ትዕዛዙን የሚተላለፍ ማንኛውም ሰው ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት እና ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ባለማክበር ሊጠየቅ ይችላል።

ውሳኔውን በለንደን የሚገኝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስተላልፏል

የፎቶው ባለመብት, Brian Farmer/BBC

በርካታ ተቋማት የዩኒቨርሲቲውን የእገዳ ማመልከቻ አውግዘዋል።

የዩኒቨርሲቲ እና የኮሌጅ ህብረት (ዩሲዩ)፣ ነጻነት ተባለው የዘመቻ ቡድን እንዲሁም የፍልስጤም የአንድነት ዘመቻ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የዩሲዩ ዋና ጸሐፊ ጆ ግራዲ "በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የተቃጣ አሳፋሪ ጥቃት ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ "ተቃውሞን ለመገደብ" እየሞከረ ነው የሚለው ማንኛውም አስተያየት "አስቂኝ ነው" ከማለት ባለፈ ተማሪዎችን እና ሠራተኞችን ለመጠበቅ እየሞከረ ነው እንደሆነ ገልጿል።