የትራምፕ 'የወርቅ ካርድ ቪዛ' ምንድን ነው? በዓለማችን ሌሎች ተመሳሳይ ቪዛዎች አሉ?

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ 'የወርቅ ካርድ' ቪዛን ይፋ ለማድረግ ዕቅድ አለኝ ብለዋል።

በሚሊዮኖች ዶላር የሚያወጣው የወርቅ ካርድ ቪዛ ቋሚ የመኖሪያ ካርድን ያካተተ ሲሆን፣ ለወደፊቱም ዜግነትን ያስገኛል።

የወርቅ ካርድ ቪዛው ያነጣጠረው ቱጃር ለሆኑ እና መኖሪያቸውን በአሜሪካ ማድረግ በሚሹ የውጭ አገር ዜጎች ላይ ነው።

"ሃብታም፣ ስኬታማ ይሆናሉ። ብዙ ገንዘብ [በአሜሪካ] ያፈሳሉ፣ ግብር ይከፍላሉ እንዲሁም በርካታ ሰዎችን ይቀጥራሉ። እጅግ ውጤታማ ይሆናል ብለን እናስባለን" ሲሉ ትራምፕ ይህንን የቪዛ ፕሮግራም አስመልክተው ከሰሞኑ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ሐዋርድ ሉትኒክ በበኩላቸው ይህ የወርቅ ካርድ ቪዛ አገራቸው ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች የምትሰጠውን ኢቢ-5 የተሰኘውን የኢንቨስተር ቪዛ የሚተካ ይሆናል።

ትራምፕ ያቀረቡት ሃሳብ ምን ይዟል?

ትራምፕ አዲሱን ቪዛ ለመውሰድ የሚፈልጉ ባለሃብቶች ማሟላት ያለባቸውን እንደ የሥራ ዕድል ፈጠራዎች ያሉ መስፈርቶችን አላነሱም።

እሳቸው የጠቆሙት መስፈርቱ "ባለሃብት ወይም ገንዘብ ይዞ መገኘትን" ብቻ ነው።

ባለው አሰራር አሜሪካ የምትሰጠው የኢቢ-5 ቪዛዎች ቁጥር የተገደበ ነው። ይህንን ጉድለት ለመሙላት የፌደራል መንግሥቱ 10 ሚሊዮን የወርቅ ካርዶች ቪዛ መሸጥ እንደሚችል ትራምፕ ጠቁመዋል።

"በጣም ጥሩ ሊሆን ይችላል፤ እንዲያውም ድንቅ ይሆናል" ብለዋል።

"ለግለሰቦች፣ በተለይም ለቱጃሮች እና በዕውቀት ለላቁ ሰዎች ዜግነት የሚያገኙበት መንገድ ነው። ሃብታም የሆኑ ሰዎች፣ ወይም ኩባንያዎች በዕውቀት የላቁ ሰዎች ወደ አገሪቱ ለመግባት ይህንን ገንዘብ ይከፍላሉ" ሲሉም ተደምጠዋል።

በዚህ የቪዛ ፕሮግራም ሩሲያውያን ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተጠየቁት ትራምፕ "አዎ፣ በጣም ጥሩ ሰዎች የሆኑ አንዳንድ የሩሲያ ቱጃሮችን አውቃለሁ" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገር ግን የንግድ ሚኒስትሩ ሉትኒክ ለዚህ ቪዛ የሚያመለክቱ "መልካም፣ ዓለም አቀፍ ዜጎች" መሆናቸውን ለማረጋገጥ የማጣራት እና ምርመራ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ሆኖም የወርቅ ካርድ ቪዛ የሚሰጣቸው ሰዎች ዜግነት ለማግኘት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚጠብቁ ግልጽ አይደለም።

የኢቢ-5 ቪዛን ጨምሮ ቋሚ የመኖሪያ (ግሪን ካርድ) ያላቸው ሰዎች ዜግነት ከማግኘታቸው በፊት በአሜሪካ በሕጋዊ ነዋሪነት ለአምስት ዓመታት መቀመጥ አለባቸው።

የአሜሪካ ምክር ቤት ለአሜሪካ ዜግነት ማሟላት የሚገባቸውን መመዘኛዎችን ይወስናል። ነገር ግን ትራምፕ "የወርቅ ካርድ" ቪዛዎችን የሚያገኙ ሰዎች የምክር ቤቱ ይሁንታ አያስፈልጋቸውም ብለዋል።

የአዲሱ ቪዛ ዕቅድ ዝርዝር በሁለት ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚሆን ተገልጿል።

የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ሐዋርድ ሉትኒክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ሐዋርድ ሉትኒክ

ኢቢ-5ን (የኢንቨስተር ቪዛ) መተካት ለምን አስፈለገ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ ሚኒስትሩ ገለጸ ከሆነ "የኢቢ-5 ቪዛ የማይረባ እና በማጭበርበር የተሞላ ነበር። ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ (ግሪን ካርድ) የሚገኘው በርካሽ ዋጋ ነበር። እናም ፕሬዚዳንቱ በእንደዚህ ዓይነት አስቂኝ ፕሮግራም ከመቀጠል ይልቅ መቋረጥ አለበት ብለው ወሰኑ" ብለዋል።

የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ነበር ኢቢ-5 የተሰኘውን የቪዛ ፕሮግራም በአውሮፓውያኑ 1990 የጀመረው።

ይህንን ቪዛ ለማግኘት ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንዲሁም ቢያንስ አስር አሜሪካውያንን መቅጠር ያስፈልጋል።

በዚህ የቪዛ ፕሮግራም ኢንቨስተሮች ወዲያውኑ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ (ግሪን ካርድ) የሚሰጣቸው ሲሆን፤ በዓመታት ውስጥም ዜግነታቸውን ያረጋግጣሉ። በአንጻሩ ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ (ግሪን ካርድ) ለማግኘት የሚያመለክቱ ሰዎች ከበርካታ ወራት እስከ በርካታ ዓመታት መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ኢቢ-5 ቪዛ በየዓመቱ ለአስር ሺህ ግለሰቦች ይሰጣል። ከእነዚህም ውስጥ 3 ሺህ የሚሆኑት የሚሰጠው ከፍተኛ ሥራ አጥነት ባለባቸው አካባቢዎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች እንደሆነ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ያስረዳል።

በአውሮፓውያኑ 2022 በአስራ ሁለት ወራት ውስጥ ወደ 8 ሺህ የሚጠጉ ባለሃብቶች የኢንቨስተር ቪዛ ማግኘታቸውን የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ያወጣው መረጃ አመልክቷል።

ከአራት ዓመታት በፊት የአሜሪካ ምክር ቤት የምርምር ክፍል ኢቢ-5 ከሌሎች የስደተኛ ቪዛዎች ጋር ሲወዳደር "የማጭበርበር አደጋዎች ያሉበት" ነው ብሏል።

"ባለሃብቶች ገንዘባቸውን በሕጋዊ መንገድ የተገኘ መሆኑን ከማጣራት ችግር ጋር የተያያዙ ስጋቶች አሉበት። እንዲሁም ቪዛው ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ግለሰቦች ባለሃብቶችን መጠቀሚያ የሚያደርጉበት መንገድ የሚከፍት እንዲሁም ለአድልዎ የሚያጋልጥ ነው" ሲል ሪፖርቱ አክሏል።

የአውሮፓ ህብረት ፓስፖርቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሌሎች አገራት ያሉ ተመሳሳይ የቪዛ ፕሮግራሞች እንዴት ይሰራሉ?

ተመሳሳይ የቪዛ ፕሮግራሞች በዓለማችን ዙሪያ የተለመዱ ናቸው።

"ወርቃማው ቪዛ" ሃብታም የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው በምላሹ በሌላ አገር የመኖር እንዲሁም የመሥራት መብታቸውን ያገኛሉ።

በአንዳንድ የካሪቢያን አገራት "ወርቃማ ፓስፖርት" የተሰኙ የቪዛ ፕሮግራሞች አሉ። በዚህም ሃብታሞች በሚያመለክቱባቸው አገራት ዜጎች የሚያገኙዋቸውን የመምረጥ መብትን ጨምሮ ሁሉንም መብቶች የሚጎናጸፉበት ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም እንደሚገኘው ሄንሊ ኤንድ ፓርትነርስ የተሰኘው አማካሪ ድርጅት መረጃ ከሆነ ከ100 በላይ አገራት ለናጠጡ ሃብታሞች "ወርቃማ ቪዛዎችን" ይሰጣሉ።

ከእነዚህም መካከል አሜሪካ፣ ስፔን፣ ግሪክ፣ ማልታ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ጣሊያን ተጠቃሽ ናቸው።

ሆኖም እነዚህ ፕሮግራሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ ትችት እና ወቀሳ እየቀረበባቸው ይገኛል።

"የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማምጣት የምጣኔ ኃብት እድገትን ያበረታታሉ። ነገር ግን ፍትህን ለማምለጥ እና ከወንጀል የሚገኝ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማሸሽ ለሚፈልጉ ወንጀለኞች እና ሙሰኛ ባለሥልጣናትን ይማርካል" ሲል ከሁለት ዓመት በፊት የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ጠቅሷል።

ከ100 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ሙስናን ለመቅረፍ የሚታገለው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በአውሮፓ ኅብረት ውሰጥ እየተተገበሩ ያሉት እነዚህ የቪዛ ዕቅዶች "እውነተኛ ኢንቨስትመንት ወይም ስደት ላይ ያተኮሩ ሳይሆኑ ከሙስና ጋር የተያያዙ ናቸው" ሲል ያስጠነቅቃል።

በተለያዩ የአውሮፓ ኅብረት አካላትም ይኸው ትችት ሲዘነዘር ቆይቷል። ከሦስት ዓመታት በፊት የአውሮፓ የሲቪል ነጻነት፣ የፍትህ እና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚቴ ወርቃማ ፓስፖርት እንዲታገድ ድምጽ ሰጥቷል።

በእነዚህ ስጋቶች የተነሳ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስፔን፣ ኔዘርላንድስ እና ግሪክን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገራት በቅርብ ዓመታት ወርቃማ ቪዛ ፕሮግራሞቻቸውን እንዲያጥፉ አድርጓቸዋል።

ስፔን በአውሮፓውያኑ 2013 የጀመረችውን እና 525 ሺህ ዶላር ለሚያመጡ ባለሃብቶች የምትሰጠውን ወርቃማ ቪዛ ሰርዛለች።

ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ኔትወርክ የሆነው የተደራጀ ወንጀል እና የሙስና ሪፖርት ፕሮጀክት ከሁለት ዓመታት በፊት በጦር ወንጀሎች የተከሰሱ የቀድሞ የሊቢያ ኮሎኔል እና እስር የተፈረደባቸው ቱርካዊ ነጋዴ እንዲህ ዓይነት ፕሮግራሞችን በመጠቀም የዶሚኒካን ፓስፖርት መግዛት መቻላቸውን አረጋግጧል።