ትራምፕ የአሜሪካ ወታደራዊ በጀት ከ50 በመቶ በላይ አድጎ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር እንዲሆን ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2027 የአሜሪካ ወታደራዊ ወጪ ከ50 በመቶ በላይ አድጎ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር እንዲሆን ጠየቁ።
የአሜሪካ ኮንግረስ ባለፈው ታኅሣሥ ያፀደቀው የመከላከያ በጀት 901 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ትራምፕ ይህ አሃዝ ከእጥፍ በላይ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በማኅበራዊ ሚድያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "ይህን ማድረግ የምናስበው አስደናቂ መከላከያ ሠራዊት ከመገንባት በተጨማሪ ጠላት ቢኖረንም ራሳችን ደኅንነታችን የተጠበቀ እንዲሆን ያስችለናል" ብለዋል።
በተያያዘ ዜና ከአሜሪካ መከላከያ ሠራዊት ጋር የሚሠሩ ኮንትራክተሮች በፍጥነት የጦር መሣሪያ የማያቀርቡ እና የማምረቻ ቦታዎችን የማይገነቡ ከሆነ ለባለቤቶቹ የሚከፍሉትን ገንዘብ እንደሚቀንሱ ዝተዋል።
ትራምፕ ይህንን ካሳወቁ በኋላ በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ግዙፍ የሚባሉት የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች የአክሲዮን ዋጋ ከፍ ብሏል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሜሪካ የምታወጣው ወጪ እና የምታስገባው ገቢ መጠን ልዩነት እየሰፋ ነው ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ነገር ግን ፕሬዝደንቱ "ምስጋና እኔ በታሪፍ ላመጣሁት ገንዘብ ይሁንና" ዋሺንግተን የተጠየቀውን 1.5 ትሪሊዮን ዶላር በጀት በቀላሉ መመደብ ይችላል ብለዋል።
ትራምፕ ከመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ጀምሮ የአሜሪካ እና የሌሎች አጋር ሀገራት ወታደራዊ ወጪ ከፍ ማለት አለበት የሚል ሐሳብ ያነሳሉ።
ትራምፕ የአሜሪካ መከላከያ ሠራዊቱ በጀት ከፍ ይበል የሚል ጥያቄ ያቀረቡት ዓለማችን በቀጣናዊ ፖለቲካ በተናጠችበት ጊዜ ነው።
ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ ኃይል በሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ሥር የምትንቀሳቀስ ነዳጅ ጫኝ መርከብ የአሜሪካን ማዕቀብ ጥሳለች በሚል በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተዘግቧል።
ይህ ዜና የተሰማው የአሜሪካ ልዩ ኮማንዶ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የቬንዙዌላው መሪ ኒኮላስ ማዱሮን ካራካስ ከሚገኘው ቤታቸው ይዞ ወደ አሜሪካ በመውሰድ ክስ ከመሠረተባቸው በኋላ ነው።
ትራምፕ የቬንዙዌላው መሪ ወደ አሜሪካ ለሚመጡ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ከመወቅሳቸው በተጨማሪ ማዱሮ የዕፅ-ሽብርተኝነትን ያራምዳሉ ይላሉ።
አሜሪካ ከራሷ አልፎ ከአጋሮቿ ጋር በቢሊዮኖች ዶላር የሚያጡ የጦር መሳሪያዎችን በመሸጥ የመከላከያ ኢንዱስትሪዋን ለመጠናከር እየሠራች ነው።
ባለፈው ታኅሣሥ ቻይና በታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ ያደረገች ሲሆን፣ ይህ የቤይጂንግ ድርጊት "ለመገንጠል የሚያስቡ ኃይሎችን" ለማስጠንቀቅ የተደረገ ነው ተብሏል።
ታይዋን የመከላከያ ሠራዊቷን ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ራስ ገዟን ደሴት እንደ ግዛቷ የምታየውን ቻይና አስቆጥቷል።
አሜሪካ ለታይዋን ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ለመሸጥ መስማማቷን ተከትሎ ነው ቻይና ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ የጀመረችው።















