ዩክሬን በድብቅ ሚሳዔል የምታመርትበት ፋብሪካ

ፋላሚንጎ የተሰኘውን አዲሱ ረዥም ርቀት የሚጓዝ የዩክሬን የጦር መሣሪያ ዩክሬናዊያን ሲያመርቱ

የፎቶው ባለመብት, Moose Campbell/BBC

የምስሉ መግለጫ, ፋላሚንጎ አዲሱ ረዥም ርቀት የሚጓዝ የዩክሬን የጦር መሣሪያ ነው

ዐይናችን በጨርቅ ተሸፍኖ ዩክሬን በድብቅ የረቀቁ የጦር መሣሪያዎችን ወደምታመርትበት ስውር ቦታ ተወሰድን።

ስልካችንን እንድናጠፋ ተነግሮናል።

ይህ ድብቁ የዩክሬን ፋላሚንጎ ክሩዝ ሚሳዔል ማምረቻ ስፍራ ነው።

ዩክሬን መሰል የጦር መሣሪያ ማምረቻ ስፍራዎቿን በድብቅ መያዟ ለህልውናዋ ወሳኝ ነው። ፋይር ፖይንት የተባለው ኩባንያ ሁለት ፋብሪካዎች ከዚህ ቀደም ተመትተዋል።

እኛ በጎበኘነው ፋብሪካ ውስጥ መስኮት፣ ቋሚ ብረቶችና ጣራውን እንዳንቀርፅ ተነግሮናል። ምክንያቱም እነዚህን ተጠቅሞ አድራሻውን መለየት ስለሚቻል።

በጦር መሣሪያ ማምራቻው ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችንም ፊት እንዳንቀርፅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።

በፋብሪካው ውስጥ የተጠናቀቁ እና እየተጠናቀቁ ያሉ ፋላሚንጎ ሚሳኤሎች ይታያሉ።

ምንም እንኳ ዩክሬን ከባድ ጦርነት ቢገጥማትም የጦር መሣሪያ ማምረቷን ቀጥላለች። ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እንደሚሉት በጦር ግንባር ጥቅም ላይ ከሚለው መሣሪያ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው በአገር ውስጥ የሚመረት ነው። አብዛኛው ረዥም ርቀት የጦር መሣሪያም የዩክሬን ምርት ነው።

ጦርነት ሲጀመር ዩክሬን በሶቪየት ዘመን የተመረቱ ያረጁ መሣሪያዎች ላይ ጥገኛ ነበረች። የምዕራባዊያን ወታደራዊ እርዳታ አገሪቱ የጦር ኃይሏ እንዲዘመን እርዳታ አድርጓል።

ነገር ግን አሁን ሰው አልባ የሚባሉ የሮቦት እና የድሮን መሣሪያዎችን በማምረት ቀዳሚ መሆን ችላለች።

አገር ውስጥ የሚመረቱ ክሩዝ ሚሳዔሎች የዩክሬን የረዥም ርቀት ጦር መሣሪያ አቅም እንዲጎለብት አድርገዋል።

ፋለሚንጎ ሲመረት

የፎቶው ባለመብት, Moose Campbell/BBC

የምስሉ መግለጫ, የቢቢሲ የዘገባ ቡድን ዩክሬን በድብቅ ክሩዝ ሚሳዔል ወደምታመርትበት ስፍራ ተወስዷል

ኢሪና ቴሬክ የፋየር ፖይንት ዋና ቴክኒካል መኮንን ናት። ኩባንያው ከዩክሬን ግዙፍ መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች አንዱ ነው።

የ33 ዓመቷ ኢሪና የሥነ-ሕንፃ ትምህርት ብትከታተልም አሁን ግን የሩሲያን የጦር ማሺን ለማውደም የበኩሏን እያበረከተች ትገኛለች።

ፍላሚንጎ ሚሳዔል ላይ የሚገጠሙ ጥቁር ብረቶችን እየቆረጠች አገኘናት። ቀድሞ ሮዝ ቀለም ነበረው አሁን ግን ጥቁር የሆነው "የሩሲያን ነዳጅ ስለሚበላ ነው" ትላለች።

ሚሳዔል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመን ትጠቀምበት የነበረውን ቪ1 ሮኬት ይመስላል። ሁለት ግዙፍ የጄት ሞተሮች ተገጥመውበታል። ግዝፈቱ ከታዋቂዎች የለንደን ባሶች ይስተካከላል።

ሚሳዔሉ በጦርነቱ ጥቅም ላይ ውሎ ያውቃል። ነገር ግን ኩባንያው የትኞቹ ዒላማዎች እንደተመቱ ከማሳወቅ ተቆጥቧል።

ኢሪና ቴሬክ

የፎቶው ባለመብት, Moose Campbell/BBC

የምስሉ መግለጫ, ኢሪና ዩክሬን የራሷን የጦር መሣሪያ ማምረቷ ለደኅንነቷ ወሳኝ ነው ትላለች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፋላሚንጎ ምዕራባዊያን ለዩክሬን ከመስጠት ከተቆጠቡት የጦር መሣሪያ ጋር የሚመሳሰል ነገር አለው።

ክሩዝ ሚሳዔሉ 3 ሺህ ኪሎ ሜትር ይመዝገዘጋል። ይህም እጅግ ዘመናዊ እና ውድ ከሆነው የአሜሪካው ቶማሃውክ ጋር እኩል ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን መሣሪያ ለዩክሬን አልሰጠም ማለታቸው ይታወሳል።

ረዥም ርቀት ሚሳዔሎች በጦርነቱ ትልቅ ቦታ አላቸው። ዩክሬን ብዙውን ጊዜ ከባድ ጉዳት ለማድረስ የምትጠቀመው ድሮኖችን ነው።

ዩክሬን በጦርነት 1 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ በሩሲያ ተይዞባታል። ይህንን ግስጋሴ ለመግታት የሩሲያን የጦር ኢኮኖሚ ዒላማ ለማድረግ ስትሞክር ይታያል።

የዩክሬን ጦር ኃይል ኃላፊ ጄነራል ኦሌክሳንደር ሲሪስኪ እንደሚሉት እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያኑ ዓመት የዩክሬን ረዥም ርቀት ጥቃቶች የሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ የ21.5 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አድርሰዋል።

የዩክሬን ልዩ ኃይል መኮንን የሆነው ራስላን ስትራቴጂው "የጠላትን አቅም ማዳከም እና ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ማድረስ ነው" ይላል።

እሱ እንደሚለው የዩክሬን ልዩ ኃይል በጠላት ቀጣና ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የነዳጅ ማጣሪያዎች፣ የመሣሪያ ማምረቻዎች እና ማስወገጃዎች ላይ ጥቃት አድርሷል።

እርግጥ ነው ሩሲያም ተመሳሳይ እና ከዩክሬን እጥፍ የሆነ እርምጃ እየወሰደች ነው። በአማካይ በየቀኑ 200 ድሮኖች ታስወነጭፋለች። ዩክሬን የዚህን ግማሽ ያህል ጥቃት ነው የምታደርሰው።

የሩሲያ ረዥም ርቀት ሚሳዔሎች እና ድሮኖች በዩክሬን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርገዋል። ይህም በሚሊዮን ለሚቆጦሩ ሰላማዊ ዜጎች ፈተና ሆኗል።

"ሩሲያ የምትተኩሰውን ያክል ድሮን መተኮስ እፈልጋለሁ" የሚለው ራስላን "በጣም በፍጥነት እያደግን ነው" የሚል አስተያየት ይሰጣል።

የፋየር ፖይንቷ ኢሪና ደግሞ ዩክሬን የሩሲያን አቅም መገዳደር ባትችልም "አእምራችንን እና ታክቲክ ተጠቅመን ለመዋጋት እየሞከርን ነው" ትላለች።

ዴኒስ ሽቲለርማን የኩባንያው ጥምር መሥራች እና ዋና ዲዛይነር ሲሆን፣ ተዓምራዊ የሆነ መሣሪያ እንዳልሆነ ያምናል።

"ጨዋታውን የሚቀይረው ለማሸነፍ ያለን ቁርጠኝነት ነው" ይላል።

የዩክሬን ልዩ ኃይል አባል የሆነው ራስላን ማንነቱ እንዳይታወቅ በጨርቅ ተሸፍኖ

የፎቶው ባለመብት, Kevin McGregor/BBC

የምስሉ መግለጫ, ራስላን ዩክሬን የጦር መሣሪያ ምርቷ በፍጥነት እያደገ ነው ይላል

ፋየር ፖይንት ከሩሲያ ወረራ በኋላ የተቋቋመ ኩባንያ ነው። አሁን በቀን 200 ድሮኖች ያመርታል። አነስተኛ አውሮፕላን የሚያክሉት ኤፍኢፒ1 እና ኤፍፒ2 የተባሉት ድሮኖች 60 በመቶ የዩክሬን ረዥም ርቀት ጥቃቶችን ለማድረስ ጥቅም ላይ ይውላሉ።

እያንዳንዱን ድሮን ለማምረት 50 ሺህ ዶላር ያወጣል። ከሩሲያው ድሮን አንድ ሦስተኛ ዋጋ ማለት ነው። ሩሲያ በወር 3 ሺህ ድሮኖችን ታመርታለች።

ዩክሬን አሁንም የውጭ እርዳታ ያሻታል። ነገር ግን በጦር መሣሪያ ራሷን ለመቻል ጥረት እያደረች ነው።

ኢሪና እንደምትለው የሚሳዔሉ አብዛኛውን ክፍል ሆነ ተብሎ በአገር ውስጥ ምርት የሚሠራ ነው።

"እኛ እየተከትልን ያለነው መመሪያ የምናመርተው የጦር መሣሪያ ላይ ማንም ተፅዕኖ ማሳደር አይችልም የሚል ነው" ትላለች። በተለይ ከቻይና እና ከዩናይትድ ስቴትስ የሚመጡ ክፍሎችን መጠቀም አይፈልጉም።

የአሜሪካ ግብዐቶችን መጠቀም ለምን አልፈለጋችሁም ተብላ የተጠየቀችው ኢሪና "ከአሜሪካ ጋር ያለን ግንኙነት ወጣ ገባ ነው። ነገ አንዱ ተነስቶ ሊዘጋው ቢሞክር የራሳችንን የጦር መሣሪያ ማምረት አንችልም ማለት ነው" የሚል ምላሽ ትሰጣለች።

ፋየርፓይንት የሚያመርተው ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Matthew Goddard/BBC

የምስሉ መግለጫ, ፋየርፓይንት በቀን 200 ድሮኖች ያመርታል

በፕሬዝዳንት ባይደን ዘመነ መንግሥት አሜሪካ ለዩክሬን 70 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ወታደራዊ እርዳታ አድርጋለች። ትራምፕ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ይህን እርዳታ አቁመው የአውሮፓው ኔቶ የአሜሪካን የጦር መሣሪያ እንዲገዛ አድርገዋል።

አሁን አሜሪካ ትልቋ የዩክሬን ደጋፊ አይደለችም። ይህን ተከትሎ አውሮፓ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ትግል ላይ ናት።

ኢሪና እየተካሄደ ያለውን የሰላም ውይይት ወደጎን በመተው ዩክሬን የራሷን የጦር መሣሪያ ማምረቷ "ብቸኛው የደኅንነቷ ማረጋገጫ ነው" ትላለች።

የቀድሞዋ የኪነ-ሕንፃ ተማሪ የአውሮፓ አገራት ከዩክሬን ብዙ ሊማሩ ይገባል ባይ ናት።

"በጦርነት ዝግጁነት እኛ ትልቅ ምሳሌ ነን።"

ሌላ አገር ዩክሬን የገጠማት ዓይነት ጥቃት ቢገጥማት "እስካሁን በቁጥጥር ስር ውላ ነበር" የሚል እምነት አላት።