የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በቁም እስር ላይ መሆናቸውን ፓርቲያቸው አስታወቀ

የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሪክ ማቻር አጋሮች በዚህ ወር መጀመሪያ በጸጥታ ኃይሎች ታስረዋል

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የረጅም ጊዜ ተቀናቃኝ የሆኑት የአገሪቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ ፓርቲያቸው አስታወቀ።

በአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር እና ከፍተኛ የደህነት ኃላፊዎች የተመራ ቡድን ትናንት ረቡዕ በዋና ከተማዋ ጁባ ወደሚገኘው የሪክ ማቻር መኖሪያ ቤት መግባቱን እና የምክትል ፕሬዝዳንቱን ጠባቂዎች ትጥቅ ማስፈታቱን ተቃዋሚው የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ (Sudan People's Liberation Movement In Opposition) ፓርቲ ገልጿል።

"እንደ እውነቱ ከሆነ ዶ/ር ማቻር በቁም እስር ላይ ነው። ነገር ግን መጀመሪያ ላይ የደህንነት ኃላፊዎች ሊወስዱት ሞክረው ነበር" ሲሉ የፓርቲው ውጭ ግንኙት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሪዝ ሙኦች ታንግ ተናግረዋል።

የአገሪቱ መንግሥት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።

ባለፉት ሳምንታት በሪክ ማቻር እና በፕሬዝዳንቱ ሳልቫ ኪር መከካል ያለው ግጭት እየተካረረ መምጣቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት፤ ደቡብ ሱዳን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመመለስ ጫፍ ላይ መሆኗን በመግለጽ አስጠንቅቆ ነበር።

ሁለቱ መሪዎች ለአምስት ዓመት የተካሄደውን እና 400 ሺህ ገደማ ሰዎችን የገደለውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማቆም የተስማሙት ነሐሴ 2010 ዓ.ም. ነበር።

ይኹን እንጂ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተፈጠሩት ብሔር ተኮር ውጥረቶች እና አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ግንኙነታቸው እየሻከረ መጥቷል።

የሪክ ማቻር ፓርቲ፤ ምክትል ፕሬዝዳንቱ የታሰሩት የደቡብ ሱዳን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ከሆኑት ከባለቤታቸው አንጀሊና ቴኒ ጋር እንደሆነ ገልጿል።

ታንግ ባወጡት መግለጫ፤ "ግልጽ ባልሆኑ ክሶች የእስር ማዘዣ ተሰጥቶታል" ብለዋል።

ድርጊቱንም "ግልጽ የሕገ መንግሥት እና የተሻሻለው የሰላም ስምምነት ጥሰት" በማለት ጠርተውታል።

አክለውም፤ "የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሂደቱን ያልጠበቀ እስር የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽር እና የአገሪቱን መረጋጋት ስጋት ላይ የሚጥል ነው" ብለዋል።

የሪክ ማቻር እስር መዘገቡን ተከትሎ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ፤ አገሪቱ "ወደ ጦርነት" የምትመለስ ከሆነ "ባለፉት ሰባት ዓመታት በብዙ ልፋት የተገኙ ውጤቶችን" የማጣት ስጋት ላይ እንደምትወድቅ አስጠንቅቋል።

ተልዕኮው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ "ዛሬ ምሽት የአገሪቱ አመራሮች ወደ ሰፊ ግጭት ለመመለስ ጫፍ ላይ ቆመዋል" ብሏል።

የ2010ሩ ስምምነትን መጣስ "ደቡብ ሱዳንን ማውደም ብቻ ሳይሆን ቀጣናው ላይም ተፅዕኖ ያመጣል" ሲልም አክሏል።

የብሪታንያ እና አሜሪካ ኤምባሲዎች የዲፕሎማቲክ ሠራተኞቻቸውን ቁጥር የቀነሱ ሲሆን ዜጎቻቸውን አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኖርዌ እና ጀርመን ኤምባሲዎች በበኩላቸው በጁባ ያላቸውን ስራ አቋርጠዋል።

በአገሪቱ ውጥረት የተባባሰው፤ በነዳጅ ሀብት በበለጸገው የላይኛው ናይል ግዛት በምትገኘው ሰሜናዊዋ ከተማ ናስር ለሁለቱ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ታማኝ የሆኑ ኃይሎች ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ነው።