ኡጋንዳ ውጥረት ወደ ነገሰባት ደቡብ ሱዳን ልዩ ጦር ማሰማራቷን አስታወቀች

ኡጋንዳ ጦር ሠራዊቷ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኡጋንዳ ጦር ሠራዊቷ የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማን እና ፕሬዝዳንቱን አንዲጠብቅ ማሰማራቷን ገልጻለች (ፎቶ ፋይል)

ኡጋንዳ የአገሪቱን ጦር የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማን ጁባን እንዲሁም የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን "እንዲጠብቅ" ልዩ ኃይል መላኳን የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ገለፁ።

ይህ የኡጋንዳ መንግሥት እርምጃ የተሰማው በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል ውጥረት መንገሱን ተከትሎ፣ የተደረሰው የሠላም ስምምነት ፈርሶ ዳግም ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ማየሉን ተከትሎ ነው።

ጄነራል ካይኔሩጋባ የአገሪቱ ጦር ለምን ወደ ጎረቤት አገር እንደተሰማራ ባይገልፁም የፕሬዝዳንት ኪር መንግሥትን ተቃውሞ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ "ኡጋንዳ ላይ ጦርነት እንደማወጅ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ጄነራሉ "የደቡብ ሱዳንን አጠቃላይ ግዛት እንደራሳችን ግዛት መከላከል አለብን" ሲሉ በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ አስተያየቱን አልሰጠም።

በደቡብ ሱዳን ያለውን የደኅንነት ስጋት ተከትሎ ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አስፈላጊ ሠራተኞች ያልሆኑ ዜጎቿ በሙሉ አገሪቱን ለቅቀው አንዲወጡ አዝዛለች።

ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ ጦር ምክትል አዛዥ እና የማቻር ደጋፊ የሆኑ ሁለት ሚኒስትሮች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ የተዋቃሚ ፓርቲ ቃል አቀባይ እስሩን የሠላም ስምምነቱ የሚጻረር "ከባድ የመብት ጥሰት" ሲሉ ኮንነውታል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አንዱ ሚኒስትር መለቀቃቸው ተሰምቷል።

ባለሥልጣናቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአፐር ናይል ግዛት፣ ዋይት አርሚ በመባል የሚታወቁት ታጣቂዎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ከተጋጩ በኋላ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2013 በማቻር እና ኪር መካከል በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ለማቻር ወግነው ተዋግተው ነበር።

በወቅቱ ኪር፣ ማቻርን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ለማካሄድ አሲረዋል በማለት ወንጅለዋቸው ነበር።

በወቅቱ ማቻር ውንጀላውን ውድቅ ያደረጉ ቢሆንም ደቡብ ሱዳን 400 ሺህ በላይ ዜጎችን ሕይወት ወደ ቀጠፈ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከትቷታል።

በ2018 በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል በተደረገ ሥልጣን የመጋራት ስምምነት ጦርነቱ ቢያበቃም፣ነገር ግን አዲስ ሕገ መንግሥት፣ ምርጫ እንዲሁም ታጣቂዎችን ወደ አንድ ጦር ማዋሀድ የሚሉት የስምምነቱ አካላት እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አልሆኑም።