አቶ ጌታቸው ረዳ ሦስት የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦችን አገዱ

በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የታገዱት ሦስቱ ጄነራሎች

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, ሜ/ጄነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ፣ብ/ጄነራል ምግበይ ኃይለ፣ ሜ/ጄነራል ማሾ በየነ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት፣አቶ ጌታቸው ረዳ ሦስት የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦችን አገዱ።

በትናንትናው ዕለት በአቶ ጌታቸው ረዳ ፊርማ የተጻፈ ደብዳቤ፣ ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊሰ፣ ሜጀር ጄነራል ማሾ በየነ እና ብርጋዴር ጄነራል ምግበይ ኃይለ ለጊዜው መታገዳቸውን ያስረዳል።

መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. የተጻፈው ይህ የዕግድ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ሦስቱ ከፍተኛ የሠራዊት አመራሮች የታገዱት "ከመንግሥት ውሳኔ ውጪ መላ ሕዝባችንን እና ወጣቱን ወደ ግርግር፤ የፀጥታ ኃይላችንን ወደ እርስ በርስ ግጭት ብሎም ሕዝባችንን ወደማይወጣበት አዘቅት የሚያስገባ አደገኛ እንቅስቃሴ አልቆመም" በሚል ነው።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሦስቱ ከፍተኛ የሠራዊት አመራሮች ላይ የዕግድ ውሳኔውን ያስተላለፈው በዚህ ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል።

ይህ ሁኔታ "ሥርዓት ባለው አካሄድ መግባባት እስኪደርስበት ድረስ" ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ "ከሠራዊት ግንባር የማዘዝ ኃላፊነታቸው ላልተወሰነ ጊዜ" የታገዱ መሆኑን አቶ ጌታቸው በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል።

ለእነዚህ ከሠራዊቱ አዛዥነታቸው ላልተወሰነ ጊዜ የታገዱት መኮንኖች በየግላቸው የተጻፈው ደብዳቤ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ እንዲሁም የትግራይ ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ እንዲያውቁት ግልባጭ ተደርጓል።

እነዚህ ሦስቱን የግንባሩ አዛዦችን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የሠራዊቱ አዛዦች ድጋፋቸውን በደብረፂዮን ገብረሚካኤል ለሚመራው የህወሓት ቡድን ሲገልጹ እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ሲጠይቁ ነበር ተብሏል።

የሦስቱ ከፍተኛ የሠራዊት አመራሮች መታገድ በክልሉ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ከመደረጉ በፊት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህም መግለጫቸው የትግራይ ሠራዊት አዛዦች ለአንድ ቡድን ወግነዋል ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

ባለፈው ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በርካታ የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ካደረጉ በኋላ፣ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ "ለውጦች" እንዲደረጉ በመግለጫ ጠይቀው ነበር።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በአዲስ እንዲዋቀር ወስነናል ያሉትን የትግራይ ሠራዊት አዛዦች "መፈንቅለ መንግሥት አውጀዋል" ሲል የፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጽህፈት ቤት በወቅቱ መክሰሱ ይታወሳል።

የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች በዚሁ የአቋም መግለጫቸው ላይ በዶ/ር ደብረፂዮን ለሚመራው የህወሓት ጎራ ዕውቅና መስጠታቸው ይታወሳል።

በተለይ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ከተካሄደው 14ኛው የድርጅቱ ጉባኤ በኋላ ለሁለት በተከፈሉት የህወሓት አመራሮች መካከል በሊቀ መንበሩ እና በምክትሉ የሚመሩት ሁለት ወገኖች ለወራት በከፍተኛ አለመግባባት እና መካሰስ ውስጥ ቆይተዋል።

ይህ በህወሓት ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል የቆየው ውዝግብ የፌደራል መንግሥቱ ድረስ የደረሰ ነበር።

ለወራት በገለልተኝነት የቆዩት የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች አብዛኞቹ በደብረፂዮን ለሚመራው ወገን ድጋፍ መስጠታቸውን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ስጋት ተፈጥሯል።

አቶ ጌታቸው እና ዶ/ር ደብረፂዮን የሚመሩት የህወሓት ቡድኖች ግንኙነት ሻክሮ ባለፉት ወራት ከፍተኛ ክፍፍል የተከሰተ ሲሆን፣ የደብረፂዮን ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩ በድጋሚ እንዲዋቀር በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር።

ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል "በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል" በማለት ባስጠነቀቁበት ጽሑፍ ላይ፣ በትግራይ አመራሮች መካከል ያለውን ክፍፍል በመጥቀስ "ከቀደመና ከአሁንም ወንጀላቸው ተጠያቂነት ለማምለጥ ከኤርትራ ጋር መወገን የሚመርጡ የትግራይ ልጆች አሉ" ሲሉም ተናግረዋል።

በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው ክፍፍል በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሊያመሩ እንደሚችሉ መሰማት የተጀመረው።

ጄነራል ፃድቃንም ይህንን የህወሓት ክፍፍል በመጥቀስ "ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በመወገን ዐቢይ አሕመድን ከሥልጣን ለመገልበጥ" የሚፈልጉ መኖራቸውን ጠቁመዋል።