በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይል የአይኤስ መሪን ሶሪያ ውስጥ መያዙ ተነገረ

የአሜሪካ መራሽ ኃይሎች ኢላማ የነበረውን ቤት የሚመለከት አንድ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ መራሹ ኃይል ኢላማ የነበረውን ቤት የሚመለከት አንድ ልጅ

በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይል የጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን አይኤስ ከፍተኛ መሪን ሰሜን ሶሪያ ውስጥ ባካሄዱት አሰሳ በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተነገረ።

ጥምር ኃይሉ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው፣ በቁጥጥር ስር የዋለው የእስላማዊው መንግሥት ቡድን መሪው "ከፍተኛ ልምድ ያለው ቦምብ ሰሪ እና የቡድኑ ዘመቻዎች አስተባባሪ” ነበር።

ባለሥልጣናት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የአይኤስ ቡድን ባለሥልጣን ነው የተባለው ግለሰብ ሃኒ አሕመድ አል-ኩርዲ በሚል ስም ይታወቃል።

ግለሰቡን ለመያዝ የተደረገውን ዘመቻ ሲከታተል የነበረ ቡድን እንዳመለከተው በሁለት ሄሊኮፕተሮች የተጫኑ ወታደሮች ሶሪያ ከቱርክ ጋር በምትዋሰንበትና በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር በምትገኘው አሌፖ አቅራቢያ ባለችው አል-ሁማይራ ውስጥ ተሰማርተው ነበር።

በአሰሳው ወቅት በጥምር ኃይሉ ወታደሮችና በታጣቂዎች መካከል ለሰባት ደቂቃ የቆየ የተኩስ ልውውጥ መደረጉንና የአይኤስ መሪውን ይዘው መሄዳቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መቀመጫውን ያደረገው የሶሪያን ጉዳይ የሚከተታለው ቡድን አመልክቷል።

ወታደሮቹ የጽንፈኛውን ቡድን መሪ ከያዙ በኋላ በምሥራቃዊ አሌፖ ክልል ውስጥ በቱርክ የሚደገፉ አማጺያን ወዳሉበት ካምፕ እንደወሰዱትም ተገልጿል።

አንድ የአል-ሁማያር መንደር ነዋሪ እንደተናገረው ወታደሮቹ ከአሌፖ ከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች ይኖሩበታል ተብሎ ይታመን የነበረን አንድ ቤት ወረው ፈትሸዋል።

"ሄሊኮፕተሮቹ ከአካባቢው ከሄዱ በኋላ ወደ ቤቱ ሄደን ስንመለከት የታሰሩ ሴቶችና ህጻናት ሜዳ ላይ አገኘን" ሲል ግለሰቡ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጿል።

"ወታደሮቹ አንድ ሰው ይዘው የሄዱ ሲሆን፣ ሌሎቹ ወንዶች ግን የት እንደሄዱ አላወቅንም። ሴቶቹን ባገኘናቸው ጊዜም 'ፋዋዝን ይዘውት ሄደዋል' ሲሉ ሰምተናቸዋል።" ብሏል።

አሰሳው በጥንቃቄ የታቀደና የተፈጸመ በመሆኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ የጥምር ኃይሉ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

ዋሽንግተን ፖስት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው የተያዘው የአይኤስ መሪ አሕመድ ኩርዲ የተባለና "ዋሊ" ወይም የራቃ አስተዳዳሪ በሚልም ይታወቃል።

ራቃ ከአሌፖ በስተ ምሥራቅ የምትገኝ ሲሆን እስላማዊ መንግሥት ወይም አይኤስ ከስምንት ዓመት በፊት ሰፊ ግዛትን ከሶሪያና ከኢራቅ ተቆጣጥሮ የራሱን ግዛት ሲያውጅ ራቃን ዋና ከተማው እንደሆነች አውጆ ነበር።

ቡድኑ ከሦስት ዓመት በፊት በጥምር ኃይሉ እና በሶሪያ ተቃዋሚ ኃይሎች ተገፍቶ አብዛኛውን ግዛቱን ተነጥቆ ተዳክሟል። ነገር ግን አሁንም በሁለቱ አገራት ውስጥ በ6,000 እና በ10,000 የሚቆጠሩ ተዋጊ ኃይሎች እንዳሉትና የደፈጣ እንዲሁም የቦምብ ጥቃቶችን እንደሚፈጽም የተባበሩት መንግሥታት አመልክቷል።

ባለፈው የካቲት ወር የአሜሪካ ልዩ ኃይሎች ተመሳሳይ ዘመቻ ኢድሊብ ግዛት ውስጥ አድርገው የአጠቃላዩ የአይኤስ ቡድን መሪ የሆነውን አቡ ኢብራሂም አል-ሐሺሚ አል-ቁራይሺን መግደላቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ አይኤስ ምንም አይነት ዝርዝር ሳይሰጥ የተገደለበትን መሪውን የሚተካ ሌላ ግለሰብ መሰየሙን ገልጾ ነበር።