ሩሲያ ሆን ብላ የጋዝ ዋጋ እንዲጨምር እያደረገች ነው ስትል ጀርመን ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጋዝፕሮ የተሰኘው በሩሲያ መንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኘው ግዙፍ ነዳጅ አቅራቢ ድንገተኛ የአቅርቦት መቀነስ በመፍጠር የጋዝ ዋጋ እንዲንር እያደረገ ነው ስትል ጀርመን ወቅሳለች።
ጋዝፕሮም በበኩሉ ለጀርመን በየቀኑ ሲልክ የነበረውን የጋዝ መጠን በ 70 ኪዩቢክ ሜትር ዝቅ እያደረገ ሲሆን ይህም አሁን ከካለው በግማሽ ያነሰ ነው
ነዳጅ አቅራቢው ለዚህም በምክንያትነት ያስቀመጠው ጋዙ በሚላክበት ኖርድ ስትሪሚ የተሰኘው ማስተላለፊያ ላይ እየተደረገ ባለው ፍትሻ ነው ብሏል።
ጀርመን ግን ይህ ምክንያት አላሳመነኝም ብላለች። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሃቢክ ውሳኔው “ፖለቲካዊ” እንጂ ቴክኒካዊ አይደልም ብለዋል።
“የአቅርቦት አለመረጋጋት ለመፍጠር እና የነዳጅ ዋጋን ለማናር የሚደረግ ዘዴ መሆኑ ግልጽ ነው“ ሲሉም አክለዋል።
ጋዝፕሮም ባለፈው ማክሰኞ በኖርድ ስትሪም አንድ አማካኝነት ወደ ጀርመን በየቀኑ የሚልከውን ጋዝ ከ167 ሜትር ኪዩብ ወደ 100 ዝቅ አድርጎ ነበር። ሆኖም ከአንድ ቀን በኋላ ማለትም ረቡዕ አቅርቦቱን ወደ 67 ሜትር ኪዩብ ዝቅ አድርጎታል።
ጋዝ ፕሮም ወደ ጣልያን ሲልክ የነበረውን ጋዝ ትላንት በ15 በመቶ ቀንሷል። ልክ እንደ ጀርመን ሁሉ ጣልያንም በሩሲያ የጋዝ አቅርቦት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተመረኮዘች ሲሆን 40 በመቶ የሚሆነውን የምታስገባው ከሩሲያ ነው።
ይህ የሩሲያ ነዳጅ አቅራቢ እያደረገ ያለው የአቅርቦት እየቀነሰ እንደሆነ የተሰማው የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ሞስኮ ኪዩቭን በመውረሯ ለመቅጣት በሚል በፈረንጆች 2022 ማገባደጃ ላይ ከሩሲያ የሚያስገቡትን ነዳጅ ለማቆም ከወሰኑ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነው።
ፖላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ፊላንድ ዴንማርክ እና ኔዘርላንድ በሩሲያ ሩብል ለመክፈል ባለመስማማታቸው የጋዝ አቅቦት ተቋርጦባቸዋል።
ሩሲያ በሩብል እንዲከፈላት እያቀረበች ያለችው ጥያቄ በምዕራባውያን ከተጣለናት ማዕቀብ በኋላ የራሷን መገበያያ ገንዘብ ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ነው።
ሚኒስትሩ ሃቢክ ይህ የሩሲያ ተግባር የአውሮፓ ሀገራት ከሩሲያ የነዳጅ ጥገኝነት በፍጥነት መውጣት እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ከወራት በፊት የዩክሬን ጦርነት ከመቀስቀሱ ጥቂት ጊዜ በፊት ጀርመን ኖርድ ስትሪም 2 የነዳጅ ማስተላለፊያ ወደ ስራ እንዳይገባ አግዳ ነበር።
ሚኒስትሩ የሩሲያ ነዳጅ አቅራቢ ተግባር የአውሮፓ ሀገራትን እና የጀርመንን የጋዝ ገበያ ላይ ያለውን ተጽዕኖ የምናየው ይሆናል ያሉ ሲሆን አቅርቡቱ እንዳይስተጓጎል ሁልጊዜም ሌላ አማራጭ እንፈልጋለን ብለዋል።
“የነዳጅ አቅርቦት ችግር የለብንም። የጋዝ ክምችታችንን ማሳደጋችንን እንቀጥላን። ባለፉት ቀናት እና ሳምንታት በዚህ በኩል ጥሩ መሻሻል አሳይተናል” ሲሉም አክለዋል።
“ነገር ግን ነገሮች እንዴት እየተለወጡ እንዳለ ጠቅለል አድርጎ ለመረዳት ግን ሁለት ሶስት ቀናት የግድ መጠበቅ አለብን” ሲሉም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ትላንት የአውሮፓ ህብረት ከእስራኤል እና ግብጽ ጋር የመነሻ ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱ እስራኤል ወደ አውሮፓ የምትልከውን ጋዝ ለማሳደግ ያለመ ነው።












