አውስትራሊያዊው መኪናቸውን ከስርቆት ያተረፉበት ያልተጠበቀ ዘዴ

የፎቶው ባለመብት, QUEENSLAND POLICE SERVICE
አንድ አውስትራሊያዊ መኪናቸውን ከስርቆት ያተረፉበት መንገድ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ እንዲሆኑ አድርጓል።
ፖሊስ እንዳለው አንዲት ሴት አውስትራሊያ ውስጥ ከብሪዝበን በስተምዕራብ በምትገኘው ሎጋን በምትባል ስፍራ ነዋሪ ከሆኑት ግለሰብ ቤት መኪና ለመስረቅ ትገባለች።
ነገር ግን መኪናውን አስነስታ ለመሄድ ከመሞከሯ በፊት ወደ ግለሰቡ ቤት ዘልቃ ገላዋን ታጥባ፣ ልብሷን ቀይራ ነበር ወደ ዋናው እቅዷ ያለፈችው።
ቤት ውስጥ ስትንጎዳጎድ ጊዜ ያጠፋችው ዘራፊ ግን አልቀናትም፤ መኪናዋን አስነስታ ልትወጣ ስትቃረብ የቤቱ አባወራ ብሬንዳን ሚልስ እና ቤተሰባቸው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ አንድ ሆነ።
"ከፊት ለፊታችን ምን እየተካሄደ እንደሆነ በቅጽበት ነበር የተገለጠልን" ሲሉ ነበር ሚልስ በአካባቢያቸው ባለ የጠዋት ፕሮግራም ላይ የተናገሩት።
የመኪናዋ በር ተዘግቶ መንቀሳቀስ ስትጀምር አንድ ነገር ለማድረግ ተንቀሳቀሱ።
"ከመኪናዋ እንድትወጣ በተደጋጋሚ ጠየቅኳት። 'አሁን ወደ ቤታችን ተመልስናል፣ ተይዘሻል። በቃሽ ከመኪናው ውረጂ'" በማለት መኪናውን ልትሰርቅ የነበረችውን ግለሰብ በተደጋጋሚ ቢጠይቋትም እሺ አላለችም።
"ግለሰቧ ከመኪናው ለመውረድ አልፈለገችም።"
"ከዚያም 'እሺ፣ እዚያው መቆየት ነው የፈለግሽው፣ እንደዚያ ከሆነ ሃሳብሽ እኔ ሌላ አማራጭ አለኝ' አልኩኝ።"
ብሬንዳን ሚልስ ሥራቸው ከመኪኖች ጋር የተያያዘ ስለሆነ እዚያው በቅርብ የከባድ ቁሶች ማንጠልጠያ መኪና [ፎርክሊፍት] ነበራቸው፤ ስለዚህም መኪናቸው በሴትየዋ ተሰርቃ ከመወሰድ ለመታደግ የነበራቸው ብቸኛው አማራጭ ፎርክሊፍቱን መጠቀም ነበር።
"ይሄ ሁሉ ነገር ሲከናወን ቤተሰቦቼ ቆመው እያዩ ነበር፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የማይረባ ነገር መፈጸም አይቻልም” ስሉ ሚልስ ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
"በጣም ተቆጥጫቻለሁ፣ በአእምሮዬ ውስጥ በርካታ ነገሮች ይመላለሱ ነበር. . . መፍጠን ነበረብኝ፣ ከዚያም ፎርክሊፍቱ መኖሩን አስታወስኩ. . . ‘ታዲያ እዚያ እያለ በእርሱ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ’ አልኩ።”
ከዚያም ልትሰረቅ የነበረችውን መኪናቸውን ሌባዋ ግለሰብን በውስጧ እንደያዘች በፎርክሊፍቱ አንጠልጥለው ወደ ላይ አነሷት። በዚህ ጊዜ ወደ ፊት መሄድ፣ ወደ ኋላ ማፈግፈግ የለ መኪናቸው አየር ላይ ስትልጠለጠል፣ ሌባዋ መኪናዋ ውስጥ ሆና ቁልጭ ቁልጭ ትል ነበር።
ፖሊስም በአጭር ጊዜ ውስጥ ደርሶ መኪናዋ እና ልትሰርቃት የነበረችውን ግለሰብ አየር ላይ እንደተንጠለጠሉ አገኛቸው።
ሚሊስም ልትሰረቅ የነበረችውን መኪናቸውን ከፎርክሊፍቷ ላይ አውርደው ተጠርጣሪዋን ለፖሊስ አስረከቡ።
ግለሰቧም ቤት ሰብሮ በመግባት እና ከሕግ ውጪ ተሽከርካሪን ለመጠቀም በመሞከር ወንጀል ክስ የተመሰረተባት ሲሆን፣ በሚቀጥለው ወር ፍርድ ቤት ትቀርባለች ተብሏል።












