ሄዝቦላህ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው የሮኬት ጥቃት ሰባት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸማቸው ሁለት የተለያዩ የሮኬት ጥቃቶች ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ከሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው መቱላ ከተማ አቅራቢያ ሮኬቶቹ ወድቀው አንድ እስራኤላዊ ገበሬ እና አራት የውጭ አገር የግብርና ሠራተኞች መሞታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትስ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት እስራኤላዊት ሴት እና ጎልማሳ ልጇ ከባሕር ዳርቻ ከተማዋ ሃይፋ ወጣ ብሎ በሚገኘው ኪቡዝ አፌክ አቅራቢያ በሚገኝ የወይራ አርሻ ውስጥ ተገድለዋል።
ሄዝቦላህ ከሃይፋ በስተሰሜን ወደ ክራዮት አካባቢ እና ከሊባኖስ ኪያም ከተማ በስተደቡብ በሚገኘው የእስራኤል ጦር ላይ ሮኬቶችን ማስወንጨፉን ተናግሯል።
የእስራኤል ጦር ሐሙስ ጠዋት ከሊባኖስ የተሻገሩ ሁለት ሮኬቶች መቱላ አቅራቢያ በሚገኝ ክፍት ቦታ ላይ መውደቃቸውን አሳውቋል።
በጥቃቱ የተገደለው እስራኤላዊ ገበሬ ኦሜር ዌይንስቴይን የተባለ በኪቡትዝ ዳፍና የሚኖር የ46 ዓመት ጎልማሳ እና የአራት ልጆች አባት መሆኑን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የተገደሉት አራት የውጭ አገር ሠራተኞች በሙሉ የታይላንድ ዜጎች መሆናቸው ሃሬትዝ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
አንድ የውጭ አገር ሠራተኛ በሮኬት ስለታማ ፍንጣሪዎች ክፉኛ ቆስሏል። ተጎጂዎች በሄሊኮፕተር ወደ ሃይፋ ራምባም ሆስፒታል መዘዋወራቸውን በበይነ መረብ ላይ የተለጠፉት ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
ዌይንስታይን እና የውጭ አገር ሠራተኞቹ ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ከድንበር አጥር አቅራቢያ በሚገኝ መስክ ውስጥ ሲሠሩ እንደነበር ሃሬትዝ ዘግቧል።
የአካባቢው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቡድን አባልን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ መቱላ በወታደራዊ ዞን ውስጥ ብትገኝም የእስራኤል ጦር ወደ ስፍራው እንዲገቡ ፈቅዶላቸዋል ብሏል።
ጦሩ ዞኑን የመሠረተው በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ የሄዝቦላህ መሣሪያዎችን እና መሠረተ ልማቶችን በማውደም በሊባኖስ ላይ የምድር ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሐሙስ የተፈጸመው ሁለተኛው የሮኬት ጥቃት ኪቡትስ አፈክ አቅራቢያ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ላይ ማረፉ ተዘግቧል።
ከሰዓት በኋላ በአጠቃላይ 55 ሮኬቶች ወደ ምዕራባዊ ገሊላ መወንጨፋቸውን ጦሩ አክሎ ገልጿል። ከሮኬቶቹ መካከል የተወሰኑት እንዲከሽፉ ሲደረግ ቀሪዎቹ ክፍት ቦታዎች ላይ ወድቀዋል ብሏል።
እንደ ሃሬትዝ ዘገባ ከሆነ የ60 ዓመቷ ሚና ሐሰን እና የ30 ዓመቱ ልጇ ካርሚ የወይራ ፍሬ በሚለቅሙበት የወይራ እርሻ ውስጥ በሮኬት ጥቃት ተገድለዋል።
የማጅን ዴቪድ አዶም የአምቡላንስ አገልግሎት እንደገለጸው ከሆነ የ70 ዓመቱ ግለሰብ በፍንጣሪ ቀላል ጉዳት ደርሶበት ወደ ራምባም ሆስፒታል ተወስዷል።
“ወደ ወይራ እርሻው ተጠርተን ስንደርስ አንድ በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው መሬት ላይ ወድቆ አየን" ሲሉ የኤምዲኤ ፓራሜዲክ አባል ሆኑት ማዞር እና ይሻይ ሌቪ ለጄሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ ተናግረዋል።
“ግለሰቡን ለማዳን እየሞከርን ሌሎች ተጎጂዎችን ስንፈልግ በአደገኛ ሁኔታ የተጎዳ ሌላ ሰው አግኝተናል። የሕክምና ድጋፍ አያድረግን የነበረ ቢሆንም በሚያሳዝን ሁኔታ ሁለቱም ሕይወታቸው አልፏል ብለን ለመናገር ተገደናል" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኘው እና የአየርላንድ ወታደሮች ያሉበት የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦር ሰፈር ረቡዕ ምሽት ወደ እስራኤል በተተኮሰ ሮኬት ተመትቷል ሲሉ የአየርላንድ ጦር ኃይል ኃላፊ ተናግረዋል።
ሮኬቱ ያረፈው ከእስራኤል ድንበር በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ካምፕ ሻምሮክ በተባለው ቦታ ላይ ቢሆንም፣ መሬቱ ላይ አነስተኛ ጉዳት ከማድረስ ውጪ ምንም ዓይነት አደጋ አላደረሰም ሲሉ ሌተናል ጄኔራል ሴን ክላንሲ ተናግረዋል።
የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሞን ሃሪስ በበኩላቸው “ሁሉም ደህና ናቸው። ይህ ክስተት ግን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለውም። ሰላም አስከባሪዎች በዓለም አቀፍ ሕግ የተጠበቁ በመሆናቸው ይህንን ለማረጋገጥ ሁሉም ወገን ኃላፊነት አለበት” ብለዋል።
በሰሜናዊ እስራኤል የተፈጸመው አደገኛ የሮኬት ጥቃት የደረሰው ሁለት የአሜሪካ ልዩ ልዑካን ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በእየሩሳሌም ተገናኝተው ከሄዝቦላህ ጋር ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሚያስችል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በተወያየበት ወቅት ነው።
ኔታንያሁ ለአሜሪካ ልዑካን እንደተናገሩት ከሆነ ዋናው ጉዳይ እስራኤል “ከሊባኖስ የሚመጣ ማንኛውንም የደኅንነት ስጋት ለመቀልበስ መቻል እና ነዋሪዎቻችንን ወደ ቤታቸው መመለስ ነው” ማለታቸውን ጽህፈት ቤታቸው ባወጣው በመግለጫው ገልጿል።
የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ እስራኤል በሄዝቦላህ ላይ ከምትፈጽመው የአየር ድብደባ በተጨማሪ የቀጥታ ጥቃት ከፍታ ወደ ሊባኖስ ወታደሮቿን አሰማርታለች።
ሂዝቦላህ ለፍልስጤሙ ሐማስ አጋርነቱን በማሳየት ከመስከረም 26ቱ ጥቃት ማግስት በሰሜን እስራኤል ድንበር አካባቢ በከፈተው የሮኬት ጥቃት የተፈናቀሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በሰላም እንዲመለሱ ለማድረግ እንደሚፈልግ ጽሕፈት ቤቱ ተናግሯል።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሊባኖስ ከ2800 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። 2200 ያህሉ የተገደሉት ባለፉት አምስት ሳምንታት ነው። 1.2 ሚሊዮን ነዋሪዎች ደግሞ መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በሰሜን እስራኤል እና በወረራ ስር ባለው የጎላን ተራሮች ላይ በተፈጸመ የሄዝቦላህ የሮኬት፣ የሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የሚሳዔል ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የእስራኤል ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የእስራኤል ጦር ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው ወታደሮቹ በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መቀጠላቸውን እና አውሮፕላኖቹ በመላ አገሪቱ የሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ዒላማዎችን መምታታቸውን አስታውቋል።
የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ እስራኤል በሦስት የደቡብ ከተሞች በፈጸመችው ጥቃት ስድስት የሕክምና ባለሙያዎች መገደላቸውን ገልጿል።
የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ከሚሰጠው እና ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ካለው ኢስላሚክ ሄልዝ ሶሳይቲ ቅርንጫፍ አባላት የሆኑት አራቱ ሰዎች የተገደሉት የእስራኤል ወታደሮች በዴርድጋያ በሚገኝ የመሰብሰቢያ ቦታ ላይ ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት ነው ብሏል።
አምስተኛው የሕክምና ባለሙያ በዲር አል-ዛህራኒ በተሽከርካሪ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት የተገደለ ሲሆን፣ በዜፍታ በተፈጸመ ጥቃትም ሌላ የጤና ባለሙያ ተገድሏል ሲል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከእስራኤል ጦር በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም። ጦሩ ከአምስት ሳምንታት በፊት ጀምሮ በሄዝቦላህ ላይ የአየር ዘመቻውን ካጠናከረ በኋላ በደርዘን የሚቆጠሩ የሕክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል።
ሄዝቦላህ መሣሪያ እና ተዋጊዎችን ለማጓጓዝ አምቡላንሶችን ይጠቀማል ሲል ጦሩ ቀደም ሲል ከሷል። ሚኒስቴሩ ግን ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ግንኙነት እንደሌለው ተናግሯል።
የእስራኤል ጦር በምሥራቃዊ የቤካ ሸለቆ በምትገኘው ባአልቤክ ጥቃቶችን ሰንዝሯል። ጦሩ ነዋሪዎች ከተማዋን እና ሁለቱን አጎራባች ከተሞች ለቀው እንዲወጡ ከአንድ ቀን በፊት አስጠንቅቆ ነበር።
በሊባኖስ መንግሥት የሚተዳደረው ብሔራዊ የዜና አገልግሎት (ኤንኤንኤ) እንደዘገበው ከሆነ አንዲት ሴት በካያል አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት ተገድላለች።
ከበአልቤክ ሰሜናዊ ምሥራቅ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ማቅና በተፈጸመ ጥቃት ሌሎች 6 ሰዎች መሞታቸውን ገልጾ አካባቢው ግን ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት አልነበረም ብሏል።












