ደቡብ አፍሪካ ፍልስጤማውያንን የጫነ አውሮፕላን ስለመጣበት "ምሥጢራዊ" መንገድ ምርመራ እንደምታካሂድ አስታወቀች

ፍልስጤማውያኑ አውሮፕላን ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Gift of the Givers

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ 153 ፍልስጤማውያንን ጭኖ ከጋዛ ወደ አገሪቱ የገባውን የኪራይ አውሮፕላን "ምሥጢራዊ" አመጣጥ በተመለከተ ምርመራ እንደሚካሄድ ተናገሩ።

ፍልስጤማውያኑን የጫነው አውሮፕላን ኦአር ታምቦ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ እንዳይገባ ተከልክሎ የነበረ ሲሆን ተሳፋሪዎቹም ለ10 ሰዓት ያህል መውረድ ሳይችሉ ቆይተዋል። ይህ እርምጃ ተወስዶ የነበረው ተሳፋሪዎቹ "ፓስፖርታቸው ላይ የጉምሩክ የመውጫ ማህተም ስላልነበራቸው" እንደሆነ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

በአገር ውስጥ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በመንግሥት "ርህራሄ" የተነሳ ኋላላይ አብዛኛዎቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲገቡ እንደተፈቀደላቸው ፕሬዝዳንቱ ራማፎሳ ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን ግን ከጋዛ የተነሱበት እና ደቡብ አፍሪካ የደረሱበት ሁኔታ ግልጽ አይደለም።

እስራኤል እና ሐማስ በጋዛ ጦርነት ላይ በነበሩበት ወቅት ደቡብ አፍሪካ ለፍልስጤማውያን ጥያቄ አጋርነቷን አሳይታለች።

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ፤ ተሳፋሪዎቹ "በሆነ ምሥጢራዊ መንገድም በናይሮቢ በኩል አልፎ" ወደ ደቡብ ሱዳን በበረረ "አውሮፕላን ላይ ተጭነዋል" ሲሉ መናገራቸውን ኒውስ24 ድረ ገጽ ዘግቧል።

የጋዛ መተላለፊያዎችን የሚቆጣጠረው እና የእስራኤል ጦር አካል የሆነው 'ኮጋት' ባወጣው መግለጫ፤ "ነዋሪዎቹ የጋዛ ሰርጥን ጥለው የወጡት ኮጋት ከሚቀበላቸው ሦስተኛ አገር ፈቃድ ካገኘ በኋላ ነው" ብሏል። ተቀባይ የተባለው አገር የቱ እንደሆነ ግን አልጠቀሰም።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የፍልስጤም ኤምባሲ እንደሚገልጸው፤ የተሳፋሪዎች ቡድኑ ከእስራኤል ራሞን አየር ማረፊያ ተነስቶ በኬንያ መዲና ናይሮቢ በኩል በርሯል። ደቡብ አፍሪካ የደረሰውም "ምንም ዓይነት መልዕክት አስቀድሞ ሳይላክ እና ዝግጅት ሳይደረግ" ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ፤ ያልተመዘገበ እና አሳሳች ድርጅት በጋዛ የሚገኙ ሰዎቻችንን አሳዛኝ ሰብአዊ ሁኔታ መዝብሯል፣ ቤተሰቦችን አታልሏል፣ ከእነርሱ ገንዘብ ሰብስቧል እንዲሁም ኢመደበኛ በሆነ እና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ጉዟቸውን አመቻችቷል" ብሏል።

ቢቢሲ የአውሮፕላኑን በረራ በተመለከተ የኬንያ መንግሥትን አስተያየት ጠይቋል።

የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት ከተሳፈሩት 153 ሰዎች ውስጥ 23 ያህሉ ወደ ሌላ መዳረሻ በርረዋል። ቀሪዎቹ 130 ሰዎች ደግሞ ደቡብ አፍሪካ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል።

ራማፎሳ በጆሃንስበርግ በተካሄደ አንድ ኹነት ላይ "ልንመልሳቸው አንችልም" ሲሉ መናገራቸውን ኒውስ24 ዘግቧል።

"ምንም እንኳ አስፈላጊው ሰነድ እና ወረቀት ባይኖራቸውም እነዚህ ሰዎች በጦርነት ከታመሰች አገር የመጡ ናቸው" ብለዋል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ መንግሥታቸው ስለጉዳዩ "ተገቢውን ምዘና" አድርጎ "የተፈጠረው ምንድነው? እንዲሁም ጉዳዩ እንዴት አሁን ያለበት ሁኔታ ደረሰ?" የሚለውን ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ መግለጻቸውን የደቡብ አፍሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤስኤቢሲ ዘግቧል።

የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ሊዮን ሽራይበር በበኩላቸው "ሁሉም ተጓዦች ትክክለኛ ፓስፖርት አላቸው። አሁን ላይ አንዳቸውም የጥገኝነት ጥያቄ አላቀረቡም" ብለዋል። 'ጊፍት ኦፍ ዘ ጊቨርስ' የተሰኘው የደቡብ አፍሪካ የበጎ አድራጎት ድርጅት ደግሞ ለፍልስጤማውያኑ መጠለያ እና ምግብ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

የአገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፍልስጤማውያኑ ከጋዛ የተነሱበት ሁኔታ እና የአውሮፕላኑን የጉዞ መስመር በመተለከተ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

ከተጓዦቹ አንዱ የሆነ ፍልስጤማዊ 'ኢኤንሲኤ ቲቪ' ከተሰኘ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረገው ቆይታ "ሰላም፣ ሕግ እና ፍትሕ" አለባት ሲል ወደገለጻት ደቡብ አፍሪካ በመምጣቱ እረፍት እንደተሰማው ተናግሯል።

ከባለቤቱ እና ሁለት ልጆቹ ጋር የተጓዘ አንድ ሰው ደግሞ "የመጣነው በየዕለቱ ሞት ከምንጋፈጥባት ጋዛ ነው። ከሁለት ዓመቱን ጦርነት ተርፈናል፤ እዚህ በመሆናችን እድለኛ ነን" ብሏል።