በዋሻዎች ውስጥ የቀሩ የሐማስ ተዋጊዎች የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ፊት እንዳይራመድ እንቅፋት መሆናቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP
200 ያህል የሐማስ ተዋጊዎች አሁንም በዋሻ ውስጥ እንደሚገኙ እና ይህም የጋዛ የተኩስ አቁም ወደፊት እንዳይራመድ እንቅፋት መፍጠሩ ተገለፀ።
እነዚህ የሐማስ ተዋጊዎች በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው የራፋህ ከተማ ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ ዋሻ ውስጥ እንዳሉ ይታመናል።
አሸማጋዮች እክል የገጠመው የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ወደሚቀጥለው እና የበለጠ ውስብስብ ምዕራፍ ለማራመድ በሚያደርጉት ጥረት አዲስ እንቅፋት እያጋጠማቸው ባለበት በዚህ ወቅት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አምባሳደር እና አማች ጃሬድ ኩሽነር ሰኞ ዕለት ወደ እስራኤል አምርተዋል።
የሐማስ ትጥቅ መፍታት፣ የጋዛ መልሶ ግንባታ እና የወደፊት አስተዳደር እንዲሁም ዓለም አቀፍ የጸጥታ ኃይል ወደ ግዛቱ ማሰማራትን ጨምሮ ቁልፍ ነጥቦች አልተፈቱም።
ከእስራኤል እና ሐማስ ከፍተኛ የሆነ ስምምነት ሊሆን ይችላል የተባለው የውይይት የጊዜ ሰሌዳ እስካሁን አለመኖር ስምምነቱ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል ወይ የሚል ጥርጣሬ ፈጥሯል።
እነዚህ ያልተፈቱ ችግሮች ባለቡት ወቅት፤ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ያለውን አካባቢ የሚያመለክተውን "ቢጫ መስመር" ከሚባለው ደቡባዊ ከተማ በራፋህ ዋሻዎች ውስጥ እንዳሉ የሚታመኑ በርካታ የሐማስ ተዋጊዎች ጋር በተያያዘ በቅርቡ ሌላ ፈተና ብቅ ብሏል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ትጥቃቸውን ለሚፈቱ ተዋጊዎች ይቅርታ ሊሰጥ እንደሚችል እና ይህ ዋሽንግተን በቀሪው የጋዛ ክፍል ተግባራዊ ለማድረግ ለምትፈልገው "ሞዴል" ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ቁጥሩ በትክክል ባይረጋገጥም ዊትኮፍ 200 ተዋጊዎች አሁንም ድረስ ዋሻ ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።
እንደ ሚዲያ ዘገባዎች ከሆነ ኩሽነር እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሰኞ ዕለት በእየሩሳሌም በተካሄደው ስብሰባ ላይ ጉዳዩን ተወያይተውበታል።
ሐማስ ቀደም ሲል ተዋጊዎቹ እጅ እንደማይሰጡ እና እስካሁን ድረስ በእስራኤል ውድቅ ሲደረግ የቆየው ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ኔታንያሁ እና ኩሽነር የተወያዩባቸው ጉዳዮች "አሁን ባለንበት ምዕራፍ አንድ፣ የቀሩትን ታጋቾቻችንን ለማምጣት፣ እና የዚህ ዕቅድ ምዕራፍ የሆነውን [የጋዛ] የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ ይህም ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት፣ ጋዛን ከጦር ኃይሎች ነፃ ማውጣት እና ሐማስ በጋዛ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ምንም ዓይነት ሚና እንደማይኖረው ማረጋገጥን ያካትታል" ብለዋል።
የጋዛ ጦርነት የተቀሰቀሰው መስከረም 26፤ 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ላይ በሐማስ በተፈፀመ ጥቃት ሲሆን 1,200 የሚያህሉ ሰዎች ሲገደሉ እና 251 ሌሎች ታጋቾች ተወስደዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ እስራኤል በጋዛ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከ69,000 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።
ባለፈው ወር ተግባራዊ የሆነው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ ጦርነቱን ማስቆም፣ ሁሉንም ታጋቾች መመለስ እና ወደ ጋዛ የሰብአዊ እርዳታ መጨመርን በማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነበር።
ሀያ በሕይወት ያሉ ታጋቾች እና የ24 የታጋቾች አስከሬን ለእስራኤል ተላልፈው ሲሰጡ የአራት ታጋቾች አስክሬን አሁንም ድረስ በጋዛ ይገኛል።
በምላሹም እስራኤል ክስ ሳይመሰረትባቸው እና ችሎት ፊት ሳይቀርቡ የታሰሩ 250 ፍልስጤማውያንን እና ከእስር ቤቶቿ፤ 1,718 ፍልስጤማውያንን ደግሞ ከጋዛ ለቅቃለች።
በተጨማሪም የ315 ፍልስጤማውያን አስከሬን ከጋዛ አስረክባለች።
እስራኤልም ሆነ ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እርስ በእርሳቸው ሲካሰሱ ቆይተዋል። ሐማስ የታጋቾችን አስከሬን ሆን ብሎ ማዘግየቱን ስትናገር፣ ሃማስም እስራኤል ቢያንስ 240 ፍልስጤማውያንን እንደገደለች እና የእርዳታ አቅርቦቶችን እንዳላስገባች ገልጿል።















