ስለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ለማስገንዘብ ሳትሞት “ሞቻለሁ” ያለችው ሕንዳዊት ተዋናይ ቁጣ ቀሰቀሰች

ህንዳዊቷ ተዋናይት ፑናም ፓንዴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምክንያት “ሞታለች” የሚል መልዕክት ከለጠፈች በኋላ በሕይወት አለሁ የሚል ቪድዮ የለቀቀችው ሕንዳዊት ተዋናይት ብዙዎችን ግራ አጋብታለች።

በርካቶች ከዚህ መልዕክት በኋላ የበይነ መረብ ዘመቻዎችን የተመለከተ ክርክር ውስጥ ገብተዋል።

ባለፈው አርብ ነው የ32 ዓመቷ ሕንዳዊት ተዋናይት ፑናም ፓንዴ በኦፊሴላዊ የኢንስታግራም ገጿ “ከበሽታው ጋር ከታለገለች በኋላ” ሞታለች የሚል መልዕክት የፃፈችው።

በርካቶች መልዕክቱ እውነት መስሏቸው የሐዘን መግለጫ ሲያስተላልፉም ነበር።

ይህ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃንም የተዋናይቷን ሞት በሐዘን ተሞልተው ዘግበዋል።

ፑናም የተወሰነ ፊልሞች ላይ በትወና ብትሳተፍም እውቅና ያገኘቸው ግን ማኅበራዊ ሚድያ ላይ በምትለጥፋቸው አከራካሪ መልዕክቶች እና በምታካሂዳቸው ዘመቻዎቿ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2011 የሕንድ ክሪኬት ቡድን የዋንጫ አሸናፊ ከሆነ ራቁቴን ፎቶ እነሳለሁ ብላ ነበር። ነገር ግን ይህንን አላደረገችም።

ሞተች ከመባሉ ከአንድ ቀን በኋላ ፑናም “የውሸት እንደሞተች” የሚተነትን ቪድዮ ለ1.3 ሚሊዮን የኢንስታግራም ተከታዮቿ ለቃለች።

“የሐሰት የሞተችው” ስለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ግንዛቤ ለማስፋፋት እንደሆነም ገልጻለች።

“ይኸው ድንገት ሳናስበው ስለማህፀን በር ጫፍ ካንሳር እያወራን ነው። አይደለም እንዴ?” ስትል የምትደመተው ተዋናይቷ “የሐሰት ሞቷ ባመጣው ለውጥ ኩራት” እንደሚሰማት ገልጻለች።

የማህፀን በር ጫር ካንሰር “በዝምታ ገዳይ” የተሰኘ ቅፅል የተሰጠው በሽታው በመጀመሪያዎቹ ወራት ምንም ዓይነት ምልክት ስለማያሳይ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሕንድ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ሴቶችን በማጥቃት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ነው።

በየዓመቱ 77 ሺህ ሴቶች በዚህ የካንሰር ዓይነት ምክንያት ይሞታሉ።

ቢሆንም በሽታው ከሌሎች ካንሰሮች በላቀ ሊከላከሉት የሚችል ሲሆን፣ ኤችፒቪ የተባለው ክትባት በበሽታው ከመያዝ ሊጠብቅ ይችላል።

ሴቶች የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራን በየጊዜ እንዲያደርጉ ይመከራሉ።

ፑናም “የሐሰት ከመሞቷ” አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሕንድ የገንዘብ ሚኒስትር ኒርማላ ሲታርማን አገሪቱ ከ9 እስከ 14 ዓመት ያሉ ታዳጊ ሴቶችን ለመከተብ እንደተዘጋጀች አሳውቀው ነበር።

በርካታ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች መንግሥት እና ፑናም ተባብረው ያደረጉት ዘመቻ ነው ቢሉም የሕንድ መንግሥትም ሆነ ተዋናይቷ ስለዚህ ጉዳይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በርካቶች ከተዋናይቷ “ሞት” በኋላ መሰል የማስታወቂያ ዘዴ መጠቀም አስፈላጊ ነውን? የሚል ጥያቄ አንስተው ሲከራከሩ ነበር።

ጥቂቶች የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻዎች “አስደንጋጭ” መሆን አለባቸው ቢሉም፣ ሌሎች ደግሞ ተዋናይቷ የተጠቀመችው መንገድ የማህፀን በር ጫፍ ተጠቂዎችን ግምት ውስጥ ያለስገባ እና ስሜትን የሚጎዳ ነው ብለዋል።

በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ላይ መልዕክታቸውን ካሰፈሩ መካከል አንዱ “እንዴት በሞት ይቀለዳል?” ሲል፣ ሌላኛው አባቱን በልጅነቱ በካንሰር ምክንያት አጣሁ ያለ ግለሰብ ደግሞ ያለፈ ታሪኬን አስታወሰችኝ ሲል ተዋናይቷን ወቅሷል።

ሌሎች ደግሞ መገናኛ ብዙኃን እንዴት የተዋናይቷን ሞት ሳያጣሩ ይዘግባሉ የሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል።

ነገር ግን አንዳንድ ጋዜጠኞች ተዋናይቷ በኦፊሴላዊ የኢንስታግራም ገጿ ያጋራችው ዜና ነው ሲሉ ዘገባቸውን ተከላክለዋል።

የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻውን የሚመራው ሽባንግ የተሰኘ ድርጅት በመልዕክቱ “ግራ ለተጋቡ” የይቅርታ መለግጫ አውጥቷል።