አሜሪካዊው ራፐር የግራሚ ሽልማትን ካሸነፈ በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊው ራፐር ኪለር ማይክ ሦስት የግራሚ ሽልማቶችን ከወሰደ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሎስ አንጀለስ ፖሊስ አስታወቀ።
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ቃል አቀባይ ማይክ ሎፔዝ ለአሶሲዬትድ ፕሬስ ሲናገሩ ራፐሩ በቁጥጥር ስር የዋለው የግራሚ ሽልማት ሥነ-ስርዓት በሚካሄድበት አዳራሽ ውስጥ አምባጓሮ ከተነሳ በኋላ ነው።
የ48 ዓመቱ ኪለር ማይክ በቁጥጥር ስር ውሎ በእስራት በማያስቀጣ ጥፋት ክስ ከተመሰረተበት በኋላ ከእስር እንደተለቀቀ ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።
ራፐሩ ሦስት የግራሚ ሽልማቶችን ከወሰደ በኋላ ለእስር የዳረገው አምባጓሮ ምን እንደሆነ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የተሰራጩ ምስሎች ትክክለኛ የመዝገብ ስሙ ማይክል ሬንደር የተባለው ድምጻዊ እጆቹ በካቴና ታስረው የሽልማት ሥነ-ስርዓት ከሚካሄድበት ቦታ በፖሊስ ተይዞ ሲወጣ አሳይተዋል።
ድምጻዊው በፖሊስ ተይዞ ሲወጣ ‘ፍሪ ማይክ’ (ማይክን ልቀቁት) የሚሉ ድምጾች ተሰምተዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባዩ ሎፔዝ ኪለር ማይክ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርባል ብለዋል።
ድምጻዊው በ20 ዓመታት የሙዚቃ ስራው ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይንቲስት & ኢንጂነርስ እና ፊውቸር ኤንደ ኤርይን አለን ኪን በተባሉት ሙዚቃዎቹ ሁለት የግራሚ ሽልማቶችን የወሰደ ሲሆን፤ ማይክል የተሰኘው አልበሙ ደግሞ ምርጥ የራፕ አልበም በሚለው ምድብ አሸናፊ አድርጎታል።
ድምጻዊው ሽልማቶቹን ሲረከብ “ይህ ሽልማት ዕድሜያቸው በመግፋቱ ራፕ መዝፈን አልችልም ብለው ለሚያስቡት ይሁን . . . የሂፕ ሃፕ ሙዚቃን እናስቀጥላለን። ማድረግ የምትፈልጉትን ነገር በሙሉ በፍጹም ከማድረግ ወደ ኋላ አትበሉ” ብሏል።
ማይክ ጥቁር አሜሪካውያን በሚገጥሟቸው ዘረኝነት እና የፖሊስ በደል በተመለከተ አስተያየቱን በይፋ በመናገር ይታወቃል።
በዘንድሮ የግራሚ ሽልማት ቴይለር ስዊፍት ደምቃበታለች። ቴይለር ለአራት ተከታታይ ዓመታት የምርጥ አልበም ሽልማትን በመውሰድ ታሪክ ሰርታለች።












