የቻይና ፍርድ ቤት በስለላ ጥፋተኛ ባለው አውስትራሊያዊ ላይ የገደብ የሞት ፍርድ አስተላለፈ

የፎቶው ባለመብት, YANG HENGJUN/TWITTER
የቻይና ፍርድ ቤት በስለላ ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው አውስትራሊያዊ ጸሐፊ ያንግ ሄንግጁን ላይ የገደብ የሞት ፍርድ አስተላለፈ።
ሄንግጁን በቀጣይ ሁለት ዓመታት ምንም ጥፋት ካልተገኘበት የተላለፈበት የሞት ፍርድ ወደ የዕድሜ ልክ እስራት ይቀየራል።
ስለ ቻይና መንግሥት በመጻፍ የሚታወቀው ሄንግጁን በቁጥጥር ሥር የዋለው ከአምስት ዓመታት በፊት ሲሆን የሚቀርቡበትን ክሶች ሲከላከል ቆይቷል።
የአውስትራሊያ መንግሥት በቻይና ፍርድ ቤት ውሳኔ መደናገጡን ገልጿል።
ፍርዱ ከተሰማ በኋላም የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ በአገሪቱ ያሉትን የቻይና አምባሳደር ጠርተው ማብራሪያ ጠይቀዋል።
“በዓለም አቀፍ አሰራር እና በቻይና ስርዓት ውስጥ ሄንግጁን መሠረታዊ የሆነ ፍትሕ እና ሰብዓዊ የሆነ አያያዝ እንዲያገኝ ስንጠይቅ ነበር” ብለዋል የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፔኒ ዎንግ።
“ሁሉም አውስትራሊያዊ ያንግ ሄንግጁን ከቤተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ማየትን ይሻል። ለሄንግጁን መሟገታችንን አናቆምም” ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የአውስትራሊያ መንግሥት የእስረኛውን አያያዝ በተመለከተ ስጋቱን ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ቻይና “በአገሪቱ የፍትሕ ሉዓላዊነት” ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን እቃወማለሁ ስትል አውስትራሊያን ነቅፋ ነበር።
የያንግ ደጋፊዎች እስሩ ፖለቲካዊ ነው ይላሉ። “በቻይና ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመተቸቱ፣ በመላው ዓለም ሰብዓዊ መብቶች እና የሕግ የበላይነት እንዲከበሩ እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመታገሉ ነው በቻይና መንግሥት የታሰረው” ሲል የያንግ ጓደኛ ፌንግ ቾንግይ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከዚህ ቀደም ለቻይና የደኅንነት ሚኒስቴር ይሰራ የነበረው ያንግ ሄንግጁን፤ እአአ 2019 ላይ የቻይና ዜግነት ካላቸው ባለቤቱ እና ልጁ ጋር ወደ ጉዋንዡ ከተጓዘ በኋላ ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።
የ58 ዓመቱ ያንግ የፍርድ ሂደት እአአ 2021 ላይ ከተጀመረ በኋላ በዝግ ችሎት ጉዳዩ ሲሰማ ቆይቷል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች የእሲያ ዳይሬክተር የሆኑት ኤሊየን ፒርሰን፣ ያንግ ሄንግጁን የሕግ አማካሪ እንዳያገኝ መደረጉን፣ ፍርዱ በዝግ ችሎት ሲካሄድ መቆየቱን እና ጥፋቱን እንዲያምን ማስቃየቶች እንደተፈፀሙበት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ያንግ ሄንግጁን ላይ የተላለፈው ፍርድ የአውስትራሊያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነትን እንደሚያሻክርም በሎወይ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ሪቻርድ ማክግሬገር ለሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ተናግረዋል።












