አሜሪካ በየመን በሚገኙ የሁቲ ታጣቂዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን ፈፀመች

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሜሪካ በየመን በሚገኙ የሁቲ ታጣቂዎች ላይ እሑድ ዕለት ተጨማሪ ጥቃቶች መፈፀሟን የአሜሪካ ማዕከላዊ ወታደራዊ ዕዝ (ሴንትኮም) አስታወቀ።
ዕዙ በመግለጫው እንዳለው የአሜሪካ ኃይሎች “በቀይ ባሕር ላይ ባሉ መርከቦች ላይ ለመተኮስ ተዘጋጅተው የነበሩ” በሚሳኤል እና አራት ፀረ መርከብ ሚሳኤሎችን መትተዋል።
ይህ ወታደራዊ ጥቃት የተፈፀመው አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በሁቲ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ከፈፀሙ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በኢራን የሚደገፈው የየመን ታጣቂ ቡድን በቀይ ባህር ላይ በወታደራዊ እና በንግድ መርከቦች ላይ የሚፈፅሙትን ተከታታይ ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ እና ዩኬ በቡድኑ ላይ ጥቃት መፈፀም ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ሁቲዎች በቀይ ባህር ላይ የሚፈፅሙት ጥቃት የዓለማችን ግዙፍ የመርከብ ድርጅቶች የባህር ጉዟቸውን እንዲተው በማስገደዱ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።
ግብፅ ጥር ወር ላይ ከስዊዝ ካነል የምታገኘው ገቢ በግማሽ መቀነሱን የገለጸች ሲሆን ባለፈው ወር ቁልፍ በሆነው የንግድ መስመር የሚጓዙ መርከቦች ቁጥርም ከአንድ ሦስተኛ በላይ ወርዷል ብላለች።
ቅዳሜ ዕለት ዩኬ እና አሜሪካ በፈፀሙት ጥምር ጥቃት በደቡባዊ የመን መዲና ሰንዓን የምሽት ሰማይ በእሳት ወጋገን ሞልተውት እንደነበርና ቤቶች ሲንቀጠቀጡ እንደነበር አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሁቲ ባለሥልጣናት በበኩላቸው በአሜሪካ ለሚመራው ጥቃት የአፀፋ ምላሽ ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመፈፀም ዝተዋል።
የቅዳሜ ዕለቱን ጥቃት ተከትሎ የቡድኑ የጦር ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪያ፣ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ “እነዚህ ጥቃቶች በጋዛ ሰርጥ በግጭት ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ለመደገፍ ካለን ሞራል፣ ሃይማኖት እና ሰብአዊ አቋማችን አያግዱንም፤ የእጃቸውን ሳያገኙም አይቀሩም” ብለዋል።
ቀደም ብሎ ዋይት ሃውስ ለኢራን በምትሰጠው ምላሽ፣ በኢራን በሚደገፈው በኢራቅ እና በሶሪያ ላይ ባሉ ኢላማዎች ላይ የሚፈፀመው የአየር ጥቃት ገና መጀመሩ መሆኑን አስጠንቅቆ ነበር።
የብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ጀክ ሱሊቫን ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚኖሩም ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
አሜሪካ ባለፈው ሳምንት በዮርዳኖስ በሚገኘው ወታደራዊ ይዞታዋ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ሦስት ወታደሮቿ ከተገደሉ በኋላ የአፀፋ ምላሽ እየሰጠች ነው።
ኢራን በድሮን ጥቃቱ ተሳትፎ እንደሌላት የገለጸች ሲሆን ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው በኢራቅ የሚገኘው እስላማዊ አማጺ ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።
ይሁን አንጅ አሜሪካ ድሮኑ ኢራን ሰራሽ መሆኑን በመጥቀስ በጥቃቱ እጇ አለበት ስትል ከሳለች።
እሑድ እለት ለኮንግረንስ በቀረበ ደብዳቤ ላይ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን አርብ ዕለት የተፈፀመው የአፀፋ ጥቃት፣ በኢራን ታጣቂ ኃይሎች እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ (አይአርጂሲ) እና ከእርሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች የሚጠቀሙበትን መሠረተ ልማቶች ኢላማ ማድረጉን ገልጸዋል።
የኢራኑ እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ በኢራቅ እንደታጠቀ፣ እንደሚደገፍ እና ሥልጠና እንደወሰደ ይታመናል።
ባይደን እንዳሉት በተፈፀመው የአፀፋ ጥቃት፣ የማዘዣ እና የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች፣ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ፣ የስልጠናና ሎጂስቲክስ ድጋፍ ማድረጊያዎችን ጨምሮ ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉ ቦታዎች ተመትተዋል ብለዋል።
ፕሬዚደንቱ ጨምረውም ጥቃቱ የተፈፀመው ቡድኑ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈፅም ለመከላከል ፣ ግጭቱ በአጭር ለመቅጨት እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስወገድ እንደሆነ አስረድተዋል።
አሜሪካ እየወሰደች ያለችው የአፀፋ ጥቃት በቀጠናው ከሚገኙ ሌሎች አገራት ውግዘት ገጥሞታል።
የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ፋራሃድ ኣላዲን አርብ ዕለት ስተፈፀመው ጥቃት ለቢቢሲ ኒውስ አዎር ሲናገሩ ጥቃቶቹ ሲፈፀሙ ማስጠንቀቂያ አልተሰጠም ነበር ብለዋል።
አማካሪው አክለውም ጉዳዩ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ አለመስጠቱ ሳይሆን ኢራቅ ሉዓላዊ አገር ናት ሲሉ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዘዋል።
በአሜሪካ የአየር ጥቃት የተገደሉ 17 የቴህራን ደጋፊ የሆኑ ታጣቂ ቡድን አባላትን ለማሰብም እሑድ ዕለት በባግዳድ ነዋሪዎች ተሰባስበው በአሜሪካ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሳኢዲንም በኦማን የዜና ወኪል ላይ በተጋራ መግለጫቸው በቀጠናው እየተባባሰ ባለው ግጭት ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ሆኖም ዋሽንግተን ጥቃቶቹ የታጣቂዎችን አቅም በማዳከም ረገድ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል ብላ እንደምታምን የአሜሪካ የደኅንት አማካሪ ሱሊቫን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ አንዳለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒኒ ብሊንከን በእስራኤል ፣ ገብፅ ፣ ኳዓታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዌስት ባንክ ለሚያደርጉት ጉዞ ወደ ቀጠናው አቅንተዋል።
በጋዛ ባለው ግጭት ተቋርጦ የነበረው ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከሃማስ ጋር የተደረገው ስምምነት ቅድሚያ የሚሰጡት ተግባር መሆኑን ሱሊቪያ ተናግረዋል።












