የበይነ መረብ ሚዲያው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢሮ ዘረፋ ተፈጸመበት

ካሜራ እና ላብቶፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በሚል ዜና እና ትንታኔዎችን በበይነ መረብ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሚያቀርበው ሐቅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ቢሮ ላይ ዝርፊያ መፈጸሙ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተባባሪ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ተስፋለም ወልደየስ ለቢቢሲ እንደተናገረው ተቋሙ በከፍተኛ ገንዘብ ሥራውን ለማስፋፋት የገዛቸው መሳሪያዎቹ ተዘርፈዋል።

ዘረፋውን በተመለከተ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ላይ በሚሠራቸው ዘገባዎች ሳቢያ ተደጋጋሚ ጫናዎች ሲደርስበት መቆየቱን አመልክቶ “ይህ ዘረፋም የእነዚህ ተደራራቢ ጫናዎች ተቀጥያ እንደሆነ እንደሚያምን” ገልጿል።

ተስፋለም እንዳለው የተቋሙ ቢሮ ቦሌ መድኅኒዓለም ሸገር ሕንጻ አካባቢ የሚገኝ ሕንጻ አራተኛ ፎቅ ላይ ሲሆን፣ የሕንጻው ጥበቃ ዘረፋው ስለመፈጸሙ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልነበራቸው ገልጿል።

በሕንጻው ላይ የደኅንነት ካሜራዎች ቢኖሩም ሐቅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ቢሮ በሚገኝበት ወለል ላይ የሚገኘው ካሜራ ግን መበላሸቱን ጨምሮ ተናግሯል።

በሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሥር የሚተዳደረው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነመረብ ሚዲያ ቢሮ በሩ እንደተቆለፈ ቢገኝም በቢሮው ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የዜና ክፍሉ ንብረቶች የተቀመጡበት ካዝና በኃይል ተሰብሮ ዘረፋ ተፈጽሞበታል።

እሁድ ለሰኞ አጥቢያ በተፈጸመው ዘረፋም ሦስት አዳዲስ ዘመናዊ ዲጂታል ካሜራዎች፣ የተለያዩ አይነት ሌንሶች፣ አራት ላፕቶፖች እና አንድ ስማርት የሞባይል ስልክ መወሰዳቸውን ተስፋለም ጨምሮ ተናግሯል።

እንዲህ ያለው በመገናኛ ብዙኃን ሥራ ላይ በተሰማሩ ተቋማት ላይ ዘረፋ መፈጸሙ ሲገለጽ ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደምም በበይነ መረብ ላይ እና በፊልም ሙያ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ተመሳሳይ ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው መዘገቡ ይታወሳል።

በተጨማሪም በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ የሚሰራው አገር በቀል የመብት ድርጅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጽሕፈት ቤት ላይም ዘረፋ እንደተፈጸመበት ገልጾ ነበር።

የኢትዮ ኢንሳይደር ባለቤት የሆነው ሐቅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ዘረፋውን “የተቀነባበረ ሳይሆን አይቀርም” የሚል ምክንያታዊ ጥርጣሬ እንዳለው አመልክቶ፣ ለዚህም “በአስቸጋሪው የኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳር ውስጥ በሁለት እግር ለመቆም እየተፍጨረጨሩ ያሉ ታዳጊ ሚዲያዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች” ላይ ያጋጠሙትን በዋቢነት ጠቅሷል።

ዘረፋው ተቋሙ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲያከናውን የነበረውን “ነጻ እና ገለልተኛ፣ ከፍተኛ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን የጠበቁ ዘገባዎችን” የበለጠ በጥራት ለማቅረብ እያደረገ በነበረው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብሏል።

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ከተቋቋመ ሦስት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን 13 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ አሁን የተሰረቁትን የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች እና ካሜራዎች ለማሟላት በርካታ ገንዘብ እና ጊዜ መፍጀቱን ተስፋለም ወልደየስ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጨምሮም ሐቅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን በአሁኑ ወቅት በሚዲያ እና በሲቪክ ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለ ተፅዕኖ እልባት እንዲያገኝ ሁሉም የሚመለከታቸው እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

ዘረፋው መፈጸሙ ከታወቀ በኋላ ፖሊስ በቢሮው ተገኝቶ አሻራ በመውሰድ እና ከሠራተኞች ቃል በመቀበል ምርመራ መጀመሩ ተገልጿል።