የዩኬን የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ጥሶ የገባው የፍልስጤም ደጋፊ ቡድን በሽብር ሊፈረጅ ነው

በፓለስታይን አክሽን ቀለም የተረጨው የጦር ጄት

የዩናይትድ ኪንግደምን አየር ኃይል ሰፈር ጥሶ የገባው የዩኬው የፍልስጤም ደጋፊ ቡድን 'ፓለስታይን አክሽን' በሽብርተኝነት ሊፈረጅ መሆኑን የአገር ውስጥ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የአገር ውስጥ ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሯ ይቬት ኩፐር በመጪው ሰኞ በፓርላማ ቡድኑን አስመልክቶ ጽሑፍ የሚያቀርቡ ሲሆን ይህም ከጸደቀ የቡድኑ አባል መሆን ሕገወጥ ይሆናል።

የፍልስጤም ደጋፊ ተሟጋቾች ኦክስፎርድሻየር ግዛት በሚገኘው ብራይዝ ኖርተን በተሰኘው የዩኬ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ጥሰው በመግባት ሁለት የጦር ጄቶችን ቀይ ቀለም ረጭተውባቸዋል።

ቡድኑን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ እንቅስቃሴ የተጀመረው በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ የጸጥታ ግምገማ መደረጉን ተከትሎ እንደሆነ ተጠቅሷል።

የ'ፓለስታይን አክሽን' ቃል አቀባይ በበኩላቸው "መንግሥታችን ሞራላዊ እና ሕጋዊ ግዴታውን መወጣት ሲያቅተው ቀጥተኛ እርምጃ መውሰድ የዜጎች ኃላፊነት ነው" ብለዋል።

ቡድኑ በኤክስ ላይ ባወጣው ጽሑፉ "ቡድኑ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ እርምጃ የሚቃወም እያንዳንዱን ግለሰብ የሚወክል ነው። እኛን ለማገድ ከፈለጉ፤ እያንዳንዳችንን ያግዱ" ብሏል።

በዩናይትድ ኪንግደም የሽብር ሕግ መሰረት የሃገር ውስጥ ጽሕፈት ቤት አንድን ድርጅት "ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ" ነው ብሎ ካመነ በሽብር የመፈረጅ ሥልጣን አለው።

ሆኖም ይህን ውሳኔ የፓርላማ አባላት ተወያይተውበት ሊያጸድቁት ይገባል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም በሽብርተኝነት የተፈረጁ 81 ቡድኖች አሉ።

የቀድሞ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ሱኤላ ብራቨርማን ቡድኑን ለማገድ የተወሰደው እርምጃ "ፍጹም ትክክለኛ ውሳኔ ነው" ብለዋል።

የቀድሞዋ ሚኒስትር በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "ሽብርተኝነትን ልንታገስ አይገባም" ብለዋል።

ነገር ግን አምነስቲ ኢንተናሽናል ዩኬ "ተቃዋሚ ቡድኖችን ኢላማ ለማድረግ ሽብርተኝነትን መጠቀም በጣም አሳሳቢ ነው" ብሏል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር አርብ የተፈጠረውን ክስተት "አሳፋሪ" ሲሉ አውግዘዋል።

የቡድኑ ድርጊት አንዳንድ የፓርላማ አባላትን ያስቆጣ ሲሆን ቡድኑ እንዲታገድ የጠየቁም አሉ።

የደቡብ ምስራቅ ጸረ ሽብር ፖሊስ ባለሙያዎቹ ከቴምዝ ቫሊ ፖሊስ እና ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጉዳዩን እየመረመሩ መሆናቸውን ቀደም ብሎ ገልጾ ነበር።

በፓለስታይን አክሽን የተለጠፈ ቪዲዮ እንደሚያሳየው ሁለት አባሎቻቸው በኦክስፎርድ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ገብተው አንደኛው በጦር ጄቱ ላይ ቀለም ሲረጭ ያሳያል።

የቡድኑ ቃል አቀባይ "ዩናይትድ ኪንግደም አሁንም ወታደራዊ ጭነቶችን ለእስራኤል እየላከች ነው። በጋዛ ላይ የስለላ አውሮፕላኖችን እያበረረች ነው፤ እንዲሁም የአሜሪካ እና የእስራኤል ተዋጊ ጄቶችን ነዳጅ መሙላት ቀጥላለች" ብለዋል።

የፓለስታይን አክሽን የአሁኑ የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስራኤልን ያግዛሉ የሚባሉ የጦር መሳሪያ ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠሩ ተግባራትን ሲሰራ ቆይቷል።

ከዚህ ቀደምም በአየርላንድ ውስጥ አንድ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን ላይ ቀለም በመርጨት ኃላፊነቱን ወስዷል።

ብራይዝ ኖርተን የአየር ኃይል የጦር ሰፈር በቆጵሮስ የሚደረጉ በረራዎችን ጨምሮ የዩኬ ስትራቴጂካዊ የአየር ትራንስፖርት እና የነዳጅ መሙያ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።

አየር ኃይሉ ከቆጵሮስ ጦር ሰፈር በመነሳት በጋዛ ላይ የስለላ በረራዎችን አድርጓል።