የትራምፕ አስተዳደር ከአሜሪካ እንዲባረር የወሰነበት ፍልስጤማዊው ተሟጋች ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ስመ ጥር ከሆኑ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ ኮሎምቢያ ተማሪዎች ለፍልስጤማውያን ያላቸውን አጋርነት በጽናት ካሳዩበት ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
ተማሪዎቹ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ድንኳኖች ዘርግተው እያደሩ ነው እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጦርነት እንድታቆም የጠየቁት።
በእነዚህ ተቃውሞዎች መካከል ስሙ የሚጠራው ማህሙድ ካሊል ነው።
የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ምሩቁ ማህሙድ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ባለሥልጣናት እና የፍልስጤም ደጋፊ በሆኑ ተማሪዎች መካከል የተካሄዱ ድርድሮችን በማሸማገል እንዲሁም ለፍልስጤም ባለው የጸና ድጋፍ ታዋቂ ሆኗል።
የትራምፕ አስተዳደር ማህሙድን በቁጥጥጥር ስር አውሎ ከአገር ሊያባርረው ውሳኔ ላይ መድረሱ በመላው ዓለም ባሉ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ሆኗል።
የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናቸውን ዩኒቨርስቲዎች እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።
የትራምፕ አስተዳደር ማህሙድን ከአገር አባርረዋለሁ ማለቱ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ያለውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲሁም በአሜሪካ ቋሚ ነዋሪ የሆነ ሰው እንዴት ሊባረር ይችላል? የሚል የሕግ ጥያቄን አስነስቷል።
ማህሙድ ለሦስት ወራት ያህል በሉዊዚያና በሚገኘው የኢሚግሬሽን ማዕከል በእስር አሳልፏል።
ሆኖም የፌደራል ዳኛ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማህመድን ከሀገር ማስወጣትም ሆነ ማሰር አይችሉም የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል።
በዚህ ውሳኔ ላይ የትራምፕ አስተዳደር ይግባኝ ለማቅረብ ዕድል አለው።
ሶሪያ ውስጥ የተወለደው ማህሙድ በኢሚግሬሽን መኮንኖች የታሰረው ትራምፕ "ፀረ- አሜሪካ እንቅስቃሴዎች" እያካሄዱ ነው በሚል በከሰሷቸው ተቃዋሚ ተማሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከገቡት ቃል ጋር በተያያዘ ነው።
ትራምፕ ማህሙድን ጨምሮ የፍልስጤም ተሟጋቾችን አሜሪካ በአሸባሪነት የፈረጀችውን ሐማስን ይደግፋሉ ሲሉ በተደጋጋሚ ይከሷቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎቹ ከአሜሪካ ሊባረሩ ይገባሉ ይላሉ። የማህሙድን መታሰር አስመልክቶ ትራምፕ "የመጀመሪያ" ነው ካሉ በኋላ በርካቶች ይከተላሉ ብለዋል።
የ30 ዓመቱ ማህሙድ ጠበቃዎች በበኩላቸው ደንበኛቸው በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያንን መደገፍ እንዲሁም አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ የመቃወም ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብቱን ነው የተጠቀመው ይላሉ።
የአሜሪካ መንግሥት "የተማሪዎችን የመሟገት እንቅስቃሴ እንዲሁም ፖለቲካዊ ንግግሮችን በግልጽ እያፈነ ነው" ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል።
ማህሙድ ሲታሰር የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሰፊው የተጋሩ ሲሆን፣ እንዲሁም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከመጀመሪያ ልጁ መወለድ ጋር ተያይዞ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበውታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማህሙድ ማን ነው?
ከፍልስጤማውያን ስደተኞች በሶሪያ የተወለደው ማህሙድ የመጀመሪያ ዲግሪውን በኮምፒውተር ሳይንስ ከ'ሌባኒስ አሜሪካን ዩኒቨርስቲ' አግኝቷል።
ከዚያም ለትርፍ ባልተቋቋመው የሶሪያ-አሜሪካ ድርጅት በሆነው ጁሶር አገልግሏል።
በቅርብ ጊዜ ቤይሩት በሚገኘው የብሪታንያ ኤምባሲ የሶሪያ ቼቭኒንንግ ፕሮግራምን ያስተዳድር ነበር።
ይህ ፕሮግራም በዩናይትድ ኪንግደም የትምህርት ዕድልን የሚያመቻች ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ማህሙድ በዚህ ፕሮግራም መሥራት ካቆመ ሁለት ዓመት እንዳለፈው ገልጿል።
ማህሙድ ወደ አሜሪካ ካቀና ሦስት ዓመትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ እና የሕዝብ ጉዳዮች ትምህርት ቤት የማስተርስ ዲግሪውን አግኝቷል።
ከዚያ በኋላ አሜሪካዊት ሴት ያገባ ሲሆን፣ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር እያለች እሷም የእስር ዛቻ ገጥሟት እንደነበር ጠበቃው ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማህሙድ በተማሪዎች ተቃውሞ ውስጥ ያለው ሚና
ማህሙድ ከጋዛ ጦርነት ጋር ተያይዞ ባለፈው ዓመት በኮሎምቢያ የተነሱት ተቃውሞዎች ዓይን ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል።
በዩኒቨርስቲው ባለሥልጣናት እና በተቃሚዎች መካከል የማሸማገል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
እስራኤልን የሚደግፉ አክቲቪስቶች በበኩላቸው ማህሙድ 'ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ አፓርታይድ ዳይቨስት' (ኩዓድ) የተሰኘው እና ዩኒቨርስቲው ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ከእስራኤል ጋር ያለውን የንግድ ሽርክና እንዲያቆም የሚጠይቀው ቡድን መሪ ነው ሲሉ ይከሱታል።
ማህሙድ በበኩሉ ይህንን የማይቀበል ሲሆን፤ በዩኒቨርስቲው እና በተቃዋሚዎቹ መካከል የቃል አቀባይነት እና የአሸማጋይ ሚና እንደነበር ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግሯል።
ማህሙድ ከታሰረ በኋላ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት "ከሐማስ ጋር የሚሄዱ እንቅስቃሴዎችን" እየመራ ነው ሲል ከሶታል።
ነገር ግን መሥሪያ ቤቱ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
በተጨማሪም ዋይት ሐውስ የሐማስ ድጋፍ ያላቸው ፕሮፖጋንዳዎች የሚሠራጩበትን የተቃውሞ ሰልፎች አዘጋጅቷል ሲል ከስሶታል።
ጠበቆቹ በበኩላቸው ደንበኛቸው አሜሪካ በሽብርተኝነት ለፈረጀቻቸው ቡድኖች ድጋፍ መስጠቱን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ሌሎች በተመሳሳይ መልኩ ሃሳባቸውን እንዳይገልጹ ለማስፈራራት እሱን ምሳሌ ለማድረግ እየሞከሩ ነው" ሲሉ ጠበቃው ሳማህ ሲሳይ ለአሶሺየትድ ፕሬስ ገልጸዋል።
በኮሎምቢያ የሚገኙ አንዳንድ አይሁዳውያን ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው የነበረው ተቃውሞ ፀረ-ሴማዊነት የተንጸባረቀበት እና በግቢው ውስጥ የደኅንነት ስጋት እንዲፈጠርባቸው ማድረጉን ገልጸዋል።
የትራምፕ አስተዳደር "በአይሁድ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ቀጣይነተ ያለው ትንኮሳ" ለመከላከል በሚል ለኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የሚሰጠውን 400 ሚሊዮን ዶላር አግዷል።
ከ'ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ አፓርታይድ ዳይቨስት' (ኩዓድ) እና ተቃውሞው ጋር ግንኙነት ያላቸው ተማሪዎች የትራምፕ አስተዳደር 'በአይሁድ ተማሪዎች ላይ ትንኮሳ' ሲል የገለጸበትን መንገድ አይቀበሉትም።
በርካታ የአይሁድ ተማሪዎች እና ቡድኖች በዩኒቨርስቲው ግቢዎች ውስጥ በተካሄዱ ተቃውሞዎች ላይ መሳተፋቸውን ይገልጻሉ።
ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በጋዛ ጦርነት ምክንያት በርካታ የተማሪዎችን ተቃውሞዎች ካስተናገዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት ተሟጋቾች የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ዜጋ ባልሆኑት ተቃዋሚዎች ላይ ማነጣጠሩን ይቀጥላል ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል።
የሕግ ባለሙያዎች የአሜሪካ ቋሚ የመኖሪያ ካርድ ያላቸው ግለሰቦች እንኳን በብሔራዊ ደኅንነት ምክንያት ከሀገር ሊባረሩ እንደሚችሉ ቢናገሩም በማህሙድ ላይ የተደረገው ግን ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነው ይላሉ።
"ስለተቃወሙ ብቻ ግለሰቦች ላይ ማነጣጠር ያልተለመደ እና በመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር እንኳን አይተነው የማናውቀው ጉዳይ ነው" ሲሉ በኮርኔል ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ጃኮብ ሃምበርገር ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማህሙድ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ለአጭር ጊዜ ታግዶ ነበር
ባለፈው ዓመት በነበረው ተቃውሞ ሰልፈኞች የዩኒቨርስቲውን ሕንጻ መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ፖሊስ ግቢው ውስጥ የገባ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ ማህሙድ ከዩኒቨርስቲው ለአጭር ጊዜ ታግዶ ነበር።
ማህሙድ በወቅቱ ለቢቢሲ እንደገለጸው ተማሪዎች በድንኳን በሚያድሩበት ተቃውሞ በቪዛው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል በሚል ስጋት በቀጥታ እንዳልተሳተፈ እና ቁልፍ ተደራዳሪ እንደነበረ ተናግሯል።
ማህሙድ ግሪን ካርድ ወይም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አለው።
"ማስረጃውን ከገመገሙ በኋላ እኔን ለማገድ ምንም ዓይነት መረጃ የላቸውም ብለዋል። ይህም እገዳው ምን ያህል በዘፈደቀ እና ያለ አግባብ እንደተደረገ የሚያሳይ ነው" ብሏል።
በቅርቡ ማህሙድ ጥቃቶች እየተሰነዘሩበት በመሆኑ ልባረር እችላለሁ የሚል ስጋት እንዳደረበት ባለቤቱ ተናግራ ነበር። የኢሚግሬሽን መኮንኖች ማህሙድን በቁጥጥር ስር ከማዋላቸው ከአንድ ቀን በፊት አስቸኳይ የሕግ ድጋፍ ለማግኘት ለኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ኢሜይል እንደላከ ተናግራለች።
የማህሙድ እስር ያስነሳው ተቃውሞ
የማህሙድን እስር ተከትሎ ተቃውሞዎች ተባብሰዋል።
እስሩን ተከትሎ ኮሎምቢያ በምትገኝበት በኒውዮርክ ከተማ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በቅርቡ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ ተማሪዎች እና ፕሮፌሰሮችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ በማንሃተን ተቃውሞ አድርገው ነበር።
የኒው ዮርክ ሲቪል ነጻነቶች ኅብረት ፕሬዚዳንት ዶና ሊበርማን ማህሙድን ከአገር ማባረር የተደረገውን ሙከራ "የበቀል እርምጃ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ ላይ የተፈጸመ ጥቃት" ብለውታል። የኒው ዮርክ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሌቲታ ጄምስ በበኩላቸው ሁኔታው "በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሰጋቸው" ገልጸዋል።















