በፍልስጤም ድጋፏ ከአሜሪካ ትባረራለች የተባለችው የኮለምቢያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ትራምፕን ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ገና በሰባት ዓመቷ ወደ አሜሪካ የመጣችው እና በፍልስጤም የድጋፍ ሰልፍ ላይ በመሳተፏ ከአገር ለማባረር ባለስልጣናቱ ሞክረዋል ያለችው የኮለምቢያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የትራምፕን አስተዳደር ከሰሰች።
በአሜሪካ ቋሚ ነዋሪ የሆነችው የደቡብ ኮሪያዋ ተወላጅ የ21 ዓመቷ ዩንሴኦ ቹንግ የኢሚግሬሸን ባለስልጣናት የመኝታ ክፍሏን ጨምሮ በተለያዩ የኮለምቢያ ተቋማት ፍተሻ አካሂደዋል ብላለች።
ተማሪዋ በትራምፕ አስተዳደር ላይ ያቀረበችው ክስ ህገ መንግሥታዊ መብቶቿን በማጣቀስ በቁጥጥር ስር እንዳትውል እና ከአገር እንዳትባረር ማገድን ነው።
በኮለምቢያ ዩኒቨርስቲ ባለስልጣናት እና የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች መካከል የተካሄዱ ድርድሮችን ያሸማገለው ታዋቂው የኮለምቢያ ዩኒቨርስቲ እና የፍልስጤም ደጋፊ ማህሙድ ካሊል በትራምፕ አስተዳደር መታሰሩን ተከትሎ ነው ይህ ክስ የቀረበው።
ዩንሴኦ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ጦርነት በመቃወም በኮለምቢያ ካምፓስ በተደረጉ ሰልፎች ላይ መሳተፏን የገለጹት ጠበቆቿ እንደ ማህሙድ ያለ ትልቅ ሚና ተጫውታ እንደሆነ ያሉት ነገር የለም።
የሃገር ውስጥ ደህንንት ዲፓርትመንት በበኩሉ ዩንሴኦ በአቅራቢያዋ በሚገኘው ባርናርድ ኮሌጅ ከፍልስጤም ድጋፍ ጋር በተያያዘ የተባረረን ተማሪ ተቃውማ ለእስር መዳረጓን ጨምሮ "በሚያሳስቡ ተግባራት" ላይ ተሰማርታለች ማለቱን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ተማሪዋ የካቲት መገባደጃ ላይ በነበረ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ መሳተፏን ተከትሎ የትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣናት ለማሰር እንዲሁም ለማባረር ጥረት መጀመራቸውን ክሱ ያትታል።
ከዚያም አይስ እየተባለ የሚጠራው የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ባለስልጣናት የፈረሙበት የእስር ማዘዣን የያዙ ወኪሎች ወላጆቿ ቤት ድረስ እንደሄዱ ተጠቅሷል።
"የትራምፕ አስተዳደር ለፍልስጤማውያን መብቶች ድጋፋቸውን እያሳዩ ያሉት ላይ በማነጣጠር ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው የኢሚግሬሽን ባለስልጣናትን እንደ ብቀላ መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው" ሲሉም ጠበቆቿ ተናግረዋል።
በፍልስጤም ድጋፋቸው ምክንያት የትራምፕ አስተዳደር አስሮ ከአገር ለማባረር እየሞከረ ካሉት በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል ዩንሴኦ አንዷ ናት።
ክሱ በተጨማሪ ከአገር ሊባረሩ ነው የተባለው የኮርኔል ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ተማሪ ሞሞዱ ታኣል እና ቪዛው የተሰረዘው የኮለምቢያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ራንጃኒ ስሪኒቫሳን ይጠቅሳል።
የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናቸውን ዩኒቨርስቲዎች እንዲያቆሙ እየጠየቁ ይገኛሉ።
እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።
ትራምፕ በነዚህ ተቃውሞዎች ላይ የሚሳተፉ አሜሪካውያን ተማሪዎች እንደሚባረሩ አስጠንቅቀዋል።
ማህሙድ በኢሚግሬሽን ባለስልጣነት የታሰረው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "አሜሪካዊ ባልሆኑ ተግባራት" ይሳተፋሉ ያሏቸውን ተማሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው።
ማህሙድ ምንም አይነት የወንጀል ክስ ያልተመሰረተበት ሲሆን እስሩ አገር አቀፍ ተቃውሞን አስነስቷል።
የማህሙድ ባለቤት የአሜሪካ ዜጋ ስትሆን የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ነች።
በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያንን መደገፉ እና አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ በመቃወም ሃሳቡን በነጻ የመግለጽ መብቱን ተጠቅሟል ሲሉ ጠበቃው ተከራክረዋል።
መንግሥት "በተማሪዎች ላይ ግልጽ ጭቆና እና ፖለቲካዊ ንግግሮቻቸውንም እያፈነ ነው" ሲሉ ከሰዋል።












