ሩሲያ እና ዩክሬን ጥቁር ባሕር ላይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ እና ዩክሬን ጥቁር ባሕር ላይ የሚያደርጉትን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርመዋል።

ሀገራቱ ሳዑዲ አራቢያ ውስጥ በየግላቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባደረጉት ስምምነት ነው የተኩስ አቁም ለማድረግ የወሰኑት።

ዋሺንግተን ስምምነቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሁሉም ወገኖች "አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት" ይሠራሉ፤ አስፈላጊ የሆነው የንግድ መተላለፊያም ይከፈታል ብሏል።

ዋይት ሐውስ በመግለጫው ሁለቱ ሀገራት ከዚህ በፊት የገቡትን የኃይል ማመንጫ መሠረት ልማት ላይ ጥቃት ያለማድረስ ስምምነት ለማጠናከርም መስማማታቸውን ገልጿል።

ነገር ግን ሩሲያ የጥቁር ባሕር የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ የሚሆነው የምግብ እና ማዳበሪያ ንግዷ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ሲነሱ መሆኑን አስታውቃለች።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሪያድ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ባለሥልጣናት ጋር በተናጠል ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል። የሩሲያ እና የዩክሬን ተወካዮች ቀጥተኛ ድርድር አላደረጉም።

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በጥቁር ባሕር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ የተገባውን ስምምነት አወድሰዋል።

"ስምምነቱ ተግባራዊ ይሆናል የሚለውን ለማወቅ ጊዜው ገና ቢሆንም ውይይቶቹ መደረጋቸው መልካም ነው። ትክክለኛ እርምጃ ነው" ሲሉ ከኪየቭ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"ከዚህ በኋላ ማንም ዩክሬን ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ወደፊት እየተጓዘች አይደለም ብሎ መውቀስ አይችልም" ሲሉ አክለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ዜሌንስኪ የሰላም ስምምነት እንዳይደረግ አግደዋል ሲሉ ወቅሰው ነበር።

ሩሲያ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የተጣሉባት ማዕቀቦች መነሳት እንዳለባቸው አሳስባለች። የሩሲያ ባንዲራ ያላቸው መርከቦች ምግብና ማዳበሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው ይታወሳል።

ስምምነቱ ከመች ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ዋይት ሐውስ ያወጣው መግለጫ አይጠቁምም።

ሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ስለማንሳት የተጠየቁት ዶናልድ ትራምፕ "ሁሉንም እየተመለክተናቸው ነው" ብለዋል።

ዜሌንስኪ ይህ "ደካማ አቋም ነው" ሲሉ ከኪየቭ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። አክለው ሞስኮ ስምምነቱን የማታከብር ከሆነ ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ለማድረግ እንዲሁም ከአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

ፕሬዝደንቱ ሩሲያ ስምምነቱ ተግባራዊ የሚደረገው ማዕቀብ ሲነሳ ነው ስትል ቀጥፋለች ሲሉ ወቅሰዋል።

ዩክሬን እና ሩሲያ የስንዴና የተለያዩ የምግብ ምርቶች ላኪ ሀገራት ሲሆኑ በጦርነቱ ምክንያት የስንዴ ዋጋ መናሩ ይታወሳል።