አውሮፓ ውስጥ ለሩስያ ሲሰልሉ የነበሩ ሁለት ሴቶችን ቢቢሲ በምርመራ አጋለጠ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
በዜግነት ቡልጋሪያዊ ናቸው። ስቪትላና ጌኔችቫ እና ትስቬታንካ ዶንቼቫ ይባላሉ።
የሩስያ የስለላ ሕዋስ አባል ሆነው ከዩናይትድ ኪንግደም ይሠሩ እንደነበር የቢቢሲ ምርመራ አጋልጧል። ሁለቱም ሴቶች ከቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም።
ስቪትላና አየር መንገድ ውስጥ ነው የምትሠራው። ቢቢሲ ስልክ ሲደውልላት ስልኩን ዘግታዋለች። ደብዳቤ ሲላክላት አስተያየት መስጠት አልፈልግም ብላለች።
ትስቬታንካ ኦስትሪያ፣ ቬየና ያለ ቤቷ አቅራቢያ ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ ቆማ ለማናገር ባለመፍቀዷ አልተሳካም።
በለንደን ሌሎች ስድስት ቡልጋሪያውያን ፍርድ እየተጠባበቁ ነው። የሩስያ የስለላ ሕዋስ አባል ናቸው ተብለው ተከስሰዋል።
ፖሊስ ሕዋሳቸውን "በጣም ውስብስብ" ሲል ገልጾታል። ሕይወትን አደጋ ላይ ጥለዋል ብሏል።
ሦስቱ ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል። ለሩስያ መሥራታቸውንም አልካዱም። የተቀሩት ሦስቱ በያዝነው ወር ነው የተፈረደባቸው።
የስለላ ሕዋሱ የተመራው በጀርመን የንግድ ኃላፊ በሆነውና የኦስትሪያ ነዋሪ ጃን ማርሳላክ ነው።
ሩስያን የሚመረምሩ ጋዜጠኞችን ዒላማ ያደርጉ ነበር። ዒላማ ያደረጉት ጋዜጠኛ ሮማን ዶብሮክቶቭ እንዳለው ከዚህ ጀርባ ያሉት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው።
በፍርድ ቤቱ ሁለት ምሥጢራዊ ሴቶች በአውሮፓ ስለላ እንደሚያደርጉ ተሰምቷል።
ቢቢሲ ምንጮቹን በማነጋገርና የበይነ መረብ መረጃ በማመሳከር የሁለቱን ሴቶች ማንነት ደርሶበታል።

የፎቶው ባለመብት, Facebook
ምሥጢራዊቷ የአየር መንገድ ሠራተኛ
ስቪትላና ጌኔችቫ በቡልጋሪያ መዲና ሶፊያ ትኖራለች። የአየር መንገድ ሠራተኛ ስለሆነች የስለላ ሕዋሱ የሚከታተላቸውን ሰዎች የበረራ መረጃ ታቀብላለች።
ሰላዮች ዒላማ ያደረጓቸው ሰዎች አቅራቢያ አውሮፕላን ላይ እንዲቀመጡ ይመቻቻል። ሰላዩቹ ለዒላማቸው ቅርብ ሆነው መረጃ ይጠልፋሉ።
ዒላማ ካደረጓቸው ጋዜጠኞች አንዱ ሮማን ዶብሮክቶቭ ነው።
ስቪትላና ወደ በርሊን ተልከው ጋዜጠኛውን እንዲሰልሉ ከታዘዙ አንዷ ናት። በዩኬ ሆነው ክትትል ከሚያደርጉ ሦስት ሰላዮች ጋር የጋራ የማኅበራዊ ሚዲያ ቡድን አላቸው።
የስቪትላና አጋሮች የሕዋሱ መሪ ኦርሊን ሮውሰቭ፣ ቢሰር ደሀምባዞቭ እና ካትሪን ኢኖቫ ናቸው።
ክሪስቶ ግሮዘቭ ለተባለ ጋዜጠኛ በረራ ስታመቻች ስለ ግለሰቡ መረጃ እየሰበሰበች ነበር። ትውልደ ሩስያዊው ክሪል ካቹርም ዒላማ ተደርጓል።
ስቪትላና፤ 'ስቬቲ' ወይም 'ቺክትቫ' በሚል ስም ነበር የምትታወቀው።
ቢቢሲ ስቪትላናን የደረሰባቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቿ ነው። ፌስቡክ ላይ ከሌሎቹ ሁለት ሰላዮች ጋር ስትነጋገር ነበር።
የአየር መንገድ ሠራተኛ መሆኗን ቢቢሲ ደረሰበት። የሊንክድኢን ገጿ ላይ ለቡልጋሪያ ድርጅት የአውሮፕላን ትኬት እንደምትሸጥና የዓለም አቀፍ አቪዬሽን አማካሪ እንደሆነች ተጽፏል።
የስለላ ሕዋሱ መሪ የበረራ ኢንዱስትሪው ውስጥ መተግበሪያ በመሥራት የሚታወቀው 'አማደስ' ይጠቀም እንደነበር ማስረጃ ተገኝቷል።
ስቪትላናም ይሄንን መተግበሪያ እንደምትጠቀም በሊንክድኢን ገጿ ይነበባል።
የቡልጋሪያ የፀጥታ ኃይል ከስለላ ሕዋስ ጋር ግንኙነት እንዳላት ቢያውቅም እስካሁን አልተከሰሰችም።
ለሪል ስቴት ሥራ በምትጠቀመው ስልክ ቢቢሲ ሲደውል ስልኩን ዘግታለች። ቢቢሲ ለላከላት ደብዳቤ "በዚህ ጉዳይ አስተያየት መስጠት አልሻም" ስትል መልሳለች።
ስሟ እንዲጠቀስ አልፈቀደችም። ምላሽ የሰጠችውም በቡልጋሪያ ቋንቋ ነው። ሆኖም ግን የመጀመሪያ ዲግሪዋን በእንግሊዘኛ እንደተማረችና ቋንቋውን አቀላጥፋ እንደምትናገር በሊንክድኢን ገጿ ጽፋለች።

የፎቶው ባለመብት, Facebook
የቪየናዋ ሴት
ትስቬታንካ ዶንቼቫ በቪየና ጋዜጠኛው ክሪስቶ ላይ ስለላ እንዲደረግ አግዛለች።
ከቤቱ ፊትለፊት ቤት ተከራይታ የቤቱን ፎቶ ስታነሳ ነበር።
ፀረ ዩክሬን ፕሮፓጋንዳ እንድታሰራጭም ተከፍሏታል። በቪየና ውስጥ በሚገኙ የሶቪየት ኅብረት ዘመን የጦርነት መታሰቢያዎች ላይ ጽሑፍ ታስቀምጥ ነበር። ዩክሬንን የሚደግፉ ሰዎች የናዚ ደጋፊ ተደርገው እንዲሳሉም ሠርታለች።
'ትስቬቲ' በሚል የምትታወቅ ሰው በስለላ ሕዋስ ውስጥ እንዳለች ቢቢሲ ከሰማ በኋላ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባደረገው ክትትል ትስቬታንካን ደርሶባታል።
በኦስትሪያ ያሉ የቢቢሲ ምንጮች ማንነቷን አረጋግጠዋል። በቪየና ያገኘቻቸው ሦስት ሰዎች በዩኬ የስለላ ክስ የቀረበባቸው ናቸው።
እነዚህም ቫንያ ጋብሮቫ፣ ቢሰር ደሀምባዞቭ እና ካትሪን ኢኖቫ ናቸው።
የደኅንነት ክፍል ኃላፊ ኦማር ሀጃዊ ፒርቸርን ጨምሮ የኦስትሪያ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች የስለላ ዒላማ ተደርገዋል።
ኦስትሪያዊቷ የምርመራ ጋዜጠኛ አና ታልመርም ዒላማ ተደርጋለች። አና ስለ ሩሲያ ስለላ ዘገባ ሠርታለች።
ትስቬታንካ ሥራ አልነበራትም። በኦስትሪያ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውላለች።
"በኦስትሪያ ከፍተኛ ምሥጢራዊ መረጃ የመሰለል ወንጀል" መፈጸሟ ተገልጿል።
ከጓደኛዋ ቫንያ በቀረበላት ጥያቄ ስለላ መጀመሯን ተናግራለች። ስቪትላና ብዙ ስሞች፣ አድራሻዎችና ምሥሎች እንደሰጠቻትም ትስቬታንካ ተናግራለች።
መጀመሪያ ላይ "የተማሪዎች ፕሮጀክት" እየሠራን ነው በሚል ሰዎች አታለዋት ወደ ነገሩ እንደገባት ለፖሊስ ገልጻ ነበር። ሆኖም ግን የሰጠችው ምስክርነት አጠራጣሪ እንደሆነ በምርመራ ተደርሶበታል።

የስለላው ሕዋስ
ሁለቱ ሴቶች የነበሩበት የስለላ ሕዋስን የሚመራው ጃን ለሩስያ የደኅንነት ተቋም እንደሚሠራ መረጃ ተገኝቷል።
ጃን ዒላማ እንዲያደርግ የተነገረው ጋዜጠኛዋ አናን ነበር።
'ፕሮፊል' የተባለ መጽሔት አርታኢ የሆነችው አና በስለላ ቡድን ክትትል እየተደረገባት እንደሆነ አምና ነበር በፖሊስ የተነገራት።
ትስቬታን ጋዜጠኛዋን ፎቶ እንድታነሳ ትዕዛዝ ተሰጥቷታል።
"ቢሮዬ ያለው የዓሣ ሬስቶራንት ቁጭ ብላ ነበር ፎቶ ስታነሳን የነበረው። ሬስቶራንቱ ውድ ስለሆነ የሚመደብላት ገንዘብ እንዲጨመር ጠይቃለች" ትላለች ጋዜጠኛዋ።
የጋዜጠኛዋን ቤት ሰብረው ለመግባት ሙከራ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
ቪየና የበርካታ ሰላዮች መሰብሰቢያ ናት። ግን በሕግ የተቀጣ ሰላይ የለም።
ጋዜጠኛዋ "በጣም ነው የሚያስፈራው። ከልጄ ጋር ብቻዬን ነው የምኖረው። አገሪቱ ጋዜጠኞችን ከለላ እንደማትሰጥ ማወቅ የበለጠ ያሰጋኛል" ትላለች።
ትስቬታንካ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መረጃ በማጋራት ትታወቃለች። ለድመቷ ሳይቀር የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ አውጥታለች።
በ2022 እና በ2023 ፑቲን የሚታዩበት ካናቴራ ለብሳ የተነሳችውን ፎቶ በፌስቡክ ለቃለች።
ሩስያውያን ሴቶች ከፑቲን ልጅ መውለድ ይፈልጋሉ የሚል አስተያየት ፌስቡክ ላይ ዐይታ ጉጉትን የሚያሳይ ኢሞጂ አስቀምጣለች።
ቢቢሲ ሊያነጋግራት ሲሞክር ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች። ደብዳቤ ቢላክላትም አልመለሰችም።
ሁለቱ ሴቶች ለሩሲያ ሰልለዋል በሚል ፍርድ ቤት ከቀረቡ ስድስት ቡልጋሪያውያን ጋር ሠርተዋል።
የዩኬ ፖሊስ በሰላዩዋና ትዕዛዝ በሚሰጣት ሰው መካከል 80,000 የቴሌግራም መልዕክት ልውውጥ አግኝቷል።
ከ2023 በፊት የስለላ ሕዋሱ ያከናወናቸውን ተልዕኮዎች ይጠቁማሉ።
የኦስትሪያ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠረትባት ለማድረግ ቢሞክርም ስላልተሳካ ከፖሊስ ይዞታ ተለቃለች።
አሁን ላይ ሁለቱን ሴቶች በቁጥጥር ሥር አልዋሉም።
ጋዜጠኛዋ አና "ስትሰልለኝ የነበረችው ሴት እንዴት እንደተፈታች አይገባኝም። እንዴት ፖሊስ ሰላይ የሚለውን አምኖ ይለቃል?" ትላለች።
ስቪትላና አሁንም በአየር መንገድ እየሠራች ነው። ቢቢሲ አስተያየት ከጠየቃት በኋላ ግን ፌስቡክ ላይ ስሟን ለውጣለች።












