ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘ሜዳሊያ ከአሁን በኋላ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ አይደለም” የኬንያ አትሌቲክስ
የኬንያ አትሌቲክስ የስፖርት አበረታች መድሃኒቶች (ዶፒንግ) ችግር በቅድሚያ እልባት መሰጠት እንዳለበት ጠቅሶ ሜዳሊያ ማሸነፍ “ከአሁን በኋላ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ” አይደለም ብሏል።
አገሪቷ በስፖርት አበረታች መድሃኒቶች (ዶፒንግ) እየተፈተነች ትገኛለች።
በባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርመራ ተደርጎላቸው በዶፒንግ ምክንያት 40 በመቶ አትሌቶቿ ታግደዋል።
በእርግጥም ሁኔታው በጣም አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ አገሪቷ ከመላው አለም አቀፍ ውድድር እንድትታገድ የአለም አትሌቲክስ ሃሳብ ሰንዝሯል።
ይህንንም ተከትሎ የኬንያ ስፖርት ሚኒስትር ባለፈው ኅዳር በሮም በተደረገው የምክር ቤቱ ስብሰባ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ተማጽኗል።
ኬንያ ለጊዜው ከአለም አቀፉ ውድድር መታገዱን ብታመልጥም በምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ስመ ጥር የሆነችው አገር አለም አቀፍ ገጽታዋን ለመገንባት ቀላል አይሆንላትም።
“ከአሁን በኋላ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ላይ ብቻ ማተኮር አንችልም”
በአሁኑ ወቅት በነሐሴ ወር ሃንጋሪ ለሚካሄደው የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን የኬንያ አትሌቲክስም በጥንቃቄ እያየው ይገኛል።አገሪቷ ሜዳሊያዎችን የማግኘት ሳይሆን በተለየ መልኩ ትሳተፋለች ብሏል።
“በሻምፒዮናው ላይ ውጤት ቅድሚያ የምንሰጠው አይደለም” በማለት የኬንያ የአትሌቲክስ የወጣቶች ልማት ዳይሬክተር ባርናባስ ኮሪር ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግረዋል።
"ፌዴሬሽኑ በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው አበረታች መድሃኒቶችን የማይጠቀሙ ንፁህ አትሌቶችን በመጠበቅ ላይ ነው። ፍትሃዊና በትክክለኛ መልኩ እያሸነፉ ያሉ አትሌቶች አሉን” ብለዋል።
አክለውም “ደካማ ተብለው የሚታሰቡ ሯጮችን ብንወስድ እንመርጣለን፤ አበረታች ቅመሞችን ሳይወስዱ እስከተወዳደሩ ድረስ ውጤቱ ምንም አይመስለንም” ሲሉ ተናግረዋል።
"ከእንግዲህ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ላይ ብቻ ማተኮር አንችልም።" ብለዋል።
የኬንያ መንግሥት ስፖርቱን ከአበረታች መድሃኒቶች ለማጽዳት 25 ሚሊዮን ዶላር በጀት ይዟል።
የስፖርት ሚኒስትሩ አባቡ ናምዋምባ የኬንያ አትሌቲክስ እና የብሔራዊ ፀረ-አበረታች መድሃኒቶች ኤጀንሲ ለዚህ ተግባር የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ስለማዋላቸው የሚቆጣጠር ኮሚቴ ያቋቁማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ባርናባስ እንደሚሉት ኬንያ ይህንን ችግር መፍታት ካልቻለች አገሪቱን ብዙ ያስከፍላታል።
“አለም አቀፋዊ ገጽታችንን መልሰን ለመገንባት የተወዳዳሪዎችን ቁጥር በእጅጉ መቀነስ አለብን" ሲሉም አክለዋል።
ቀጣዩ ፈታኝ ጊዜዎች
ኬንያ የዶፒንግን ጉዳይ በሚመለከተው በገለልተኛው የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ከፍተኛ የአበረታች መድኃኒት ስጋት ደቅናለች በሚል በፌዴሬሽን ደረጃ ከተፈረጁ ሰባት ሃገራት መካከል አንዷ ነች። ይህም ማለት ከአንድ ትልቅ ውድድር በፊት ባሉት 10 ወራት ውስጥ ቢያንስ ሦስት ብሔራዊ ምርመራዎችን ካደረገች በኋላ ነው አትሌቶችን ለመወዳደር ብቁ የሚሆኑት።
“በከፍተኛ ዶፒንግ ዝርዝር ምድብ ኤ ለአምስት ዓመታት ቆይተናል። እናም ዋነኛ ትኩረታችን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከዚህ ምድብ መውጣት ነው" ሲሉ በርናባስ ተናግረዋል።
"የአለም አትሌቲክስ በዚህ አመት በኬንያ ፀረ አበረታች መድሃኒቶችና ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ በኩል ቢያንስ 3,000 ምርመራዎች እንድናካሂድ አዞናል። ይህ በተቀረው ዓለም በሚደረጉ ውድድሮች እንድንሳተፍ ከፈለግን ነው” ብለዋል።
ኬንያ ከሁለት ሳምንታት በፊት በተደረገው ሁለተኛው የአትሌቲክስ ሩጫ ውድድር ከ1 ሺህ 500 በላይ አትሌቶችን አሳትፋለች።
"በተለመደው ሁኔታ የአገር ውስጥ ውድድሮች ዋና አላማ ተሰጥኦ ያላቸውን መለየት ነው፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እነዚህን ውድድሮች በመጠቀም አትሌቶችን ወደ አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት ምርመራ ዝርዝር ውስጥ እናካትታቸዋለን” ብለዋል በርናባስ።
በርናባስ እንደሚሉት አገሪቷ መጠነ ሰፊ ምርመራ እያደረገችም ትገኛለች።
በጥር ወር የአለም አትሌቲክስ ሊቀ መንበር ሰባስቲን ኮ ስለ ሁኔታው ለመወያየት ኬንያን በጎበኙበት ወቅት በመንግሥት የተደገፈ ሽፋን የመስጠት አዝማሚያ እንደሌለ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በርናባስ አገሪቷ ከዶፒንግ ጋር ከምታደርገው ትግል ወደኋላ እንደማትል ቃል ገብተዋል።
“ስርዓቱን በማጭበርበር እናልፋለን ብለው የሚያስቡ ምርጥ አትሌቶች እንኳን ከአመቱ መጨረሻ በፊት ይባረራሉ” ብለዋል።