ትራምፕ ከላቲን አሜሪካ አገሮች ጋር በተደረገ ስምምነት ቡና ላይ የጣሉትን ታሪፍ ለማንሳት አቀዱ

ቡና የምትጠጣ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትራምፕ አስተዳደር ከአራት የላቲን አሜሪካ አገሮች ጋር በተደረሱ የንግድ ስምምነቶች መሠረት በቡና እና በሙዝ ላይ የሚጣሉ ቀረጦች እንደሚቀንሱ ሐሙስ ዕለት አስታውቋል።

ከአርጀንቲና፣ ጓቲማላ፣ ኤል ሳልቫዶር እና ኢኳዶር ጋር ስምምነቶች የተደረሱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢኮኖሚውን የያዙበት እና በዋጋ ዙሪያ እየደረሰባቸው ያለው ትችት በበረታበት ወቅት ነው።

የመጀመሪያ ማዕቀፍ አካል የሆነው 10 በመቶ ታሪፍ ከጓቲማላ፣ አርጀንቲና እና ኤል ሳልቫዶር በሚመጡ እቃዎች ላይ የሚቀጥል ሲሆን ከኢኳዶር 15 በመቶ ሆኖ ይቀጥላል። ነገር ግን ስምምነቶቹ እንደ ቡና ባሉ እና "በበቂ መጠን" በአሜሪካ ውስጥ ሊመረቱ የማይችሉ ምርቶችን ከታሪፍ ነፃ ያደርጋል።

የአሜሪካ እና የአርጀንቲና ስምምነት የስጋ አምራቾች ወደ ውጭ ገበያዎች ተደራሽ የሚሆኑበትን ዕድል ይመለከታል።

ትራምፕ ቀደም ሲል የኑሮ ውድነትን በተመለከተ የቀረበውን ስጋት አቅልለው በመግለጽ በዘጠኝ ወራት የሥልጣን ዘመናቸው መሻሻሉን ተናግረዋል። ተመጣጣኝ ዋጋ የሚለው "አዲስ ቃል" እና የዴሞክራቶች "ማጭበርበሪያ" እንደሆነ አስታውቀዋል።

የሪፐብሊካን ፓርቲ ባለፈው ሳምንት በጥቂት ግዛቶች በተካሄደው የግማሽ ዓመት ምርጫ ደካማ አፈጻጸም ካሳየ በኋላ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተዋል።

በዚህ ሳምንት ትራምፕ እና የግምጃ ቤት ኃላፊው ስኮት ቤሴንት የቡና ዋጋን ለመቀነስ ቃል ገብተዋል። ቡና በዚህ ዓመት በአሜሪካ ገበያ 20 በመቶ ያህል ጨምሯል። ቤሴንት በሙዝ እና በሌሎች ፍራፍሬዎች ላይ የታሪፍ እፎይታ መኖሩን ጠቁመዋል።

ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሐሙስ ዕለት ከታሪፍ ነጻ እንዲሆኑ ከተዘጋጁት አራት የላቲን አሜሪካ አገሮች ምርቶች ውስጥ ቡና፣ ካካዋ እና ሙዝን እንደ ምሳሌ አንስተዋል።

ጓቲማላ እና ኢኳዶር ወደ አሜሪካ በብዛት ሙዝ የሚልኩ አገሮች ናቸው።

አሜሪካ ጓቲማላን ጨምሮ ከመካከለኛው አሜሪካ አገሮች ቡና የምታስገባ ቢሆንም፣ ወደ አሜሪካ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና የምትልከው አገር ብራዚል መሆኗን ከግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ቢያመላክትም በስምምነቱ አልተሸፈነችም።

ከባድ የአየር ሁኔታ ለቡና እና ለካካዎ ዋጋ መጨመር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ባለስልጣናት ተናግረዋል። ቸርቻሪዎች እና ጅምላ ሻጮች በተመሳሳይ መንገድ ከተጓዙ ዋጋዎቹ በተወሰነ ደረጃ እንደሚቀንሱ ተስፋ አድርገዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከአርጀንቲና ጋር ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ዋይት ሐውስ የስጋ ገበያዎችን ተደራሽነት በማስፋፋት ላይ ማተኮሯን ገልጻለች።

ሁለቱ አገራት "ለበሬ ንግድ የተሻሻሉ፣ እርስ በርስ የሚደጋገፉ፣ የሁለትዮሽ የገበያ ተደራሽነት ሁኔታዎችን" ለማድረግ ቃል ገብተዋል ሲል መግለጫው ገልጿል።

የስጋ ዋጋ መጨመር ለትራምፕ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኗል። ባለፈው ሳምንት፣ የስጋ ማቀነባበሪያ ኩባንያዎች የስጋ ዋጋን በመጨመር ረገድ ያላቸውን ሚና በተመለከተ የፍትህ መምሪያው እንዲመረምር ጠይቀዋል። በቅርቡ የቀረበው የስጋ ዋጋ ቅነሳ ሃሳቦች በከብት አርቢዎች ዘንድ ተቃውሞ አስነስቷል።

ከላቲን አሜሪካ የንግድ አጋሮች ጋር የተደረጉት አራቱ ስምምነቶች በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደሚፈረሙ ይጠበቃል ሲሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ስምምነቱ የተደረሰው ትራምፕ በሚያዝያ ወር በደርዘን የሚቆጠሩ አገሮች ላይ አዳዲስ ታሪፎችን እንደሚያስወግዱ ከገለጹ በኋላ ነው።