የአሜሪካ እና የቻይና የንግድ ጦርነትን ያባባሰው ቻይና በማዕድናት ገበያ ላይ የጣለችው ገደብ

የቻይና ማዕድን ማውጫ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ባለፈው ሳምንት የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ሰነድ ከአሜሪካ ጋር ያለው የንግድ ውዝግብ መባባሱን ይጠቁማል።

ቻይና በቀላሉ የማይገኙ ማዕድናት ላይ ገደብ መጣሏ በዚህ ሰነድ ተመልክቷል።

ይህም በቻይና እና አሜሪካ የንግድ ጦርነት ውስጥ ቻይና ሊኖራት የሚችለውን የበላይነት ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሳይቷል።

"አናውንስመንት 62/2025" የተባለው ሰነድ የተጣለውን ገደብ ያስቀምጣል።

ከተንቀሳቃሽ ስልክ እስከ ጄት ድረስ ለማምረት የሚውሉ ልዩ ወይም ብርቅ ማዕድናትን ቻይና በብቸኛነት ታመርታለች።

የቴክኖሎጂ ምርቶች የጀርባ አጥንት ከሆኑ 17 ተመሳሳይ ይዘት ካላቸው ልዩ ማዕድናት አንዱ ነው።

አብዛኞቹ ማዕድናት በተፈጥሮ የሚገኙ ቢሆንም ከሌላ ኬሚካል ጋር ሳይደባለቁ ለማግኘት ቀላል አይደለም።

ማዕድናቱን ማውጣት አደገኛም ነው።

ቻይና አዲስ ባወጣችው ሕግ መሠረት የውጭ አገራት ባለሃብቶች ጥቂት መጠን ያለው ማዕድንም ቢሆን ኤክስፖርት ለማድረግ የቻይናን መንግሥት ፈቃድ ማግኘት አለባቸው።

ለቻይና ውሳኔ ምላሽ ትራምፕ ተጨማሪ 100 በመቶ ታሪፍ በቻይና ሸቀጦች ላይ ጥለዋል።

ዋነኛ መተግበሪያዎች ላይም ገደብ እንዲጣል ትራምፕ ወስነዋል።

በአውስትራሊያ ኤዲት ዶውን ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ኖይስ ማክዶንጋ እንደሚሉት፤ ቻይና የጣለችው ገደብ "የአሜሪካን የአቅርቦት ሰንሰለት የሚያዳክም" ይሆናል።

"ውሳኔው የወጣበት ወቅት አሜሪካ የምትፈልገውን ድርድር እንዳታደርገም ይገድባል" ብለዋል።

ከፀሐይ ኤሌክትሪክ የሚያመነጨውን መሣሪያ ጨምሮ የኤሌክትሪክ መኪኖች እና የጦር መሳሪያ ለመሥራትም ልዩ ማዕድናት አስፈላጊ ናቸው።

የጦር ጄት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማዕድናቱ ለጦር ጄቶች መሥሪያነት ጭምር ይውላሉ

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ፀሐፊ ስኮት ቤንሴት "ቻይና እየተላተመች ያለው ከዓለም ጋር ነው። በዓለም ሸቀጣሸቀጥ እና የኢንዱስትሪ ምርት ላይ አነጣጥረዋል። ይሄንን አንቀበልም" ብለዋል።

የቻይና ንግድ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው አስተያየቱን አጣጥለዋል።

አሜሪካ እና ቻይና በማድሪድ የምጣኔ ሃብት እና ንግድ ውይይት ካደረጉ በኋላ አሜሪካ የቻይናን ንግድ ለመጨቆን 20 እርምጃዎች መውሰዷን ጠቅሰዋል።

የዓለም ትልቅ ምጣኔ ሃብት ያላቸው አገራት አንዳቸው በሌላቸው ላይ የወደብ ቀረጥ ጥለዋል።

የቻይና እና አሜሪካ ባለሥልጣናት ድርድርን ተከትሎ ላለፉት ወራት የአገራቱ የንግድ ጦርነት ረገብ ብሎ ቆይቶ ነበር።

ፕሬዝዳንት ዢ ጂን ፒንግ እና ዶናልድ ትራምፕ ከውጭ ንግድ ባለሃብቶች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቻይና ልዩ ማዕድናት ላይ ገደብ መጣሏ በውይይቱ ላይ ጫና የማሳደር አቅሟን እንደሚያጎለባት ይታመናል።

ኒዮዳይሚየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተፈላጊ ከሆኑት ማዕድናት መካከል አንዱ ኒዮዳይሚየም የሚባለው

ኤፍ-35 ተዋጊ ጄትም ጨምሮ ሌሎችም የጦር መሳሪያዎች የሚሠሩት በእነዚህ ልዩ ማዕድናት ነው።

የቻይና የልዩ ማዕድናት ንግድ በኤሌክትሪክ መኪና ዘርፍ ከዓለም ገበያ 70 በመቶውን እንደሚሸፍን የኒውላንድ ግሎባል ግሩፕ አማካሪ ናታሻ ጃ ባካር ይናገራሉ።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ ሲድኒ በቀላሉ የማይገኙ ማዕድናት አጥኚ ማሪና ዢንግ እንደሚሉት፤ ቻይና በቀላሉ የማይገኙ ማዕድናት የዓለም ንግድን ለመቆጣጠር ያለመታከት ሠርታለች።

ቻይና በዘርፉ ባለሙያዎችን በብዛት ታሠለጥናለች። በዘርፉ የተሠሩ ጥናት እና ምርምሮችም ከተፎካካሪ አገራት የቀደሙ ናቸው።

ቻይና ለምታቀርባቸው ማዕድናት ተለዋጭ አማራጭ ለማግኘት እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።

በተወሰነ ደረጃ ስኬታማ ሆነዋል።

ቻይናን በዋናነት የምትገዳደረው አውስትራሊያ ናት። ሆኖም በዘርፉ ያላት መሠረተ ልማት አጥጋቢ አይደለም።

"አሜሪካ እና አጋሮቿ ማዕድናቱን ማውጣት ብሔራዊ ፕሮጀክት ቢያደርጉም እንኳን ቻይና ላይ ለመድረስ ቢያንስ አምስት ዓመት ይወስድባቸዋል" ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት እና የንግድ ተወካዩ ጄሚሰን ግሪር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይናን እምነት የማይጣልባት በማለት የከሰሱት የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት እና የንግድ ተወካዩ ጄሚሰን ግሪር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቻይና ከወራት በፊት የወሰደችው እርምጃ ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስር ላይ ጫና ማሳደሩ አይዘነጋም።

በአውሮፓ እና በአሜሪካ የተፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት ለማስተካከል ስምምነቶች ተፈርመውም ነበር።

የቻይና ወደ ውጭ አገራት የምትልከው ማዕድን መጠን ከአምና ጋር ሲነጻጸር ባሳለፍነው መስከረም ወር በ30 በመቶ ቀንሷል።

ቻይና ወደ ውጭ አገራት የምትልከው ማዕድን መጠን ቢቀንስም ምጣኔ ሃብቷን እንደማይጎዳው ተንታኞች ያስረዳሉ።

የኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ መምህር ፕሮፌሰር ሶፊያ ካላንዛኮስ እንደሚሉት፤ ከቻይና ምጣኔ ሃብት ውስጥ በቀላሉ የማይገኙ ማዕድናት ያላቸው ድርሻ 18.7 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ነው።

ከቻይና አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ከ0.1 በመቶ በታች እንደሆነ ይገመታል።

ምጣኔ ሃብታዊ ሚናው አነስተኛ ቢሆንም እንኳን ከአሜሪካ ጋር ካለው የንግድ ትስስር አንጻር "ስትራቴጂያዊ ቦታው" ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያው ይገልጻሉ።

አሜሪካ ቻይናን "በክህደት" የከሰሰችውም ለዚህ ነው።

"ነገሩ ሳይካረር በፊት ቻይና ለውይይት ዝግጁ ናት ብዬ አምናለሁ" ይላሉ ባለሙያው።

ቻይና ከአሜሪካ ጋር ከመነጋገሯ በፊት የንግድ ውሳኔዎችን ታሳልፋለች።

በሲንጋፖር ማኔጅመንት ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ጂዎ ያንግ እንደሚሉት፤ ከቻይና አንጻር አሜሪካ ለመደራደሪያ የሚሆኑ ነጥቦች ላይኖሯት ይችላሉ።

አሜሪካ ታሪፍ ለመቀነስ ሐሳብ ታቀርብ ይሆናል። ከአሜሪካ ጋር ያለው የንግድ ጦርነት የምርት ዘርፏን የጎዳባት ቻይና ሐሳቡን ልትቀበል ትችላለች።

የቻይና ምጣኔ ሃብት በዋነኛነት ወደ ውጭ በሚላኩ ሸቀጦች ይዘወራል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ ቻይና ለአሜሪካ የላከችው ምርት መጠን በ27 በመቶ ዝቅ ብሏል።

አሜሪካ ቻይና ላይ ተጨማሪ ታሪፎች ለመጣል ዝታለች። ይህም በቴክኖሎጂው ዘርፍ ጫና ያሳድራል።

አሜሪካ ገደብ ከጣለችባቸው የቻይና ምርቶች መካከል የኒቪዲያ ቺፕ ይጠቀሳል።

የቻይና ቴክኖሎጂ ላይ ያነጣጠረ እርምጃ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ባለሙያው ይናገራሉ።

"ቻይና በዚህ ተጽዕኖ ሥር ሆናም መቀጠል ትችላለች። ነገር ግን በቀላሉ የማይገኙ ማዕድናት ላይ ገደብ ስትጥል መላው ኢንዱስሪውን ያናጋል" ይላሉ።